>
5:09 pm - Saturday March 3, 7060

የቅዱሳን ፓትርያርኮቹ ህይወት አደጋ ላይ ነው...!?! (ዘመድኩን በቀለ)

የቅዱሳን ፓትርያርኮቹ ህይወት አደጋ ላይ ነው…!?!

ዘመድኩን በቀለ

  *… ብር ከፈሎ መሾም የለመደ ሁሉ እንደልማዱ ገድሎ ከመሾም ወድኋላ አይልም…!!!
 
*…. የደከሙ አባት በቃሬዛ ተሸክሞ ቤተ መንግሥት ወስዶ ፖለቲካ አይሠራበትም። እነ አቡነ ዮሴፍ፣ እነ አቡነ ሩፋኤል በእውነት እፈሩ። በዚህ ሥራችሁ የሚደሰት ዐማራም፣ ብልፅግናም፣ የሚናደድ ትግሬም የለም። 
 
… አዎ እውነት ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በትናንትናው ዕለት ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በመሄድ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ጋር ረዘም ላሉ ሰዓታት መክረዋል፣ ጊዜ ወስደውም ተወያይተዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ራሳቸው ናቸው ወደ ቅዱስ ፓትርያርኩ የሄዱት። ቀደም ሲል እነ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ እነ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል፣ ዲያቆን ዳንኤልና እነ አባ ህፃን በፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስን በሳንሳ ተሸክመው ቤተ መንግሥት ድረስ ወስደው በሠሩት የእጅ መንሻ ሥራ ብዙም ምቾት የተሰማቸው አይመስልም።
… ያለፈው ሐሙስ ዕለት በኢትዮ ቤተሰብ ሚድያ ላይ ትናንት ዐርብም በመረጃ ቴሌቭዥን መርሀ ግብሬ ላይ እኔም አጠንክሬና ደጋግሜ የተናገርኩትም ይሄንኑ ነበር። ልጅ ወደ አባቱ ዘንድ መጥቶ ይባረካል እንጂ አባትን ያውም የደከመ አባት… ሳል የሚያሰቃየውን፣ መጻፍ መናገርና መቀመጥ የማይችሉትን አባት፣ የደከሙ አባት በቃሬዛ ተሸክሞ ቤተ መንግሥት ወስዶ ፖለቲካ አይሠራበትም። እነ አቡነ ዮሴፍ፣ እነ አቡነ ሩፋኤል በእውነት እፈሩ። በዚህ ሥራችሁ የሚደሰት ዐማራም፣ ብልፅግናም፣ የሚናደድ ትግሬም የለም።
…ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ቤተ መንግሥታቸው ከተመለሱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በጠቅላይ ሚንስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪና የፓርላማ አባል በሆኑት በተከበሩት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተመራና የደኅንነት ሚንስትሩን አቶ ተመስገን ጥሩነህንና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል አቶ ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ያካተተ ቡድን ወደ መንበረ ፓትርያርክ በመሄድ ከቅዱስነታቸው ጋር ረዘም ላሉ ሰዓታት መወያየታቸው ተሰምቷል።
…ልዑካኑ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ዘንድ መላካቸውንና ቅዱስነታቸው ከጠቅላዩ ጋር በነበራቸው ቆይታ የተሰማቸውን ቅሬታ በሙሉ ሳይደብቁ ስለነገሩትና ይሄንኑ የቅዱስነታቸውን ቅሬታ ያዳመጡት ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድም መልእክተኞቹን “ቅዱስነታቸው የተከፉበት ነገር አለና በአሰቸኳይ አሁኑኑ ሂዳችሁ አድምጣችሁኋቸው እንዲታረም አድርጉላቸው”በማለት እንደላኳቸውና የቅዱስነታቸውንም ቅሬታ ለማዳመጥ እንደመጡ በመንገር ሦስቱ ልዑካን ቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር ውይይታቸውን አድርገዋል።
… ሌላሌላው የውይይት አጀንዳቸው ለጊዜው ይቆየንና ለጊዜው አንዱን ብቻ እንመልከት። “… እንዴት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ሰብስባችሁ ታስራላችሁ? በዚህ በከፋ የበሽታ ጊዜ አረጋውያን አባቶችን አስራችሁስ ምን ትጠቀማላችሁ? (በሙሉ የታሰሩት ደግሞ ጥፋታቸው ትግሬና ትግራይ መወለዳቸው ብቻ ነው።) በማለት የጠየቁ ሲሆን… ልዑካኑም ሲመልሱ “… ሊቃውንቱን ያስረናቸው የመስቀል በዓል ላይ ይበጠብጣሉ የሚል መረጃ ስለደረሰን ነው ቢሉም ቅዱስነታቸው መልሰው ከመቼ ጀምሮ ነው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያውም አረጋውያን አባቶች በመስቀል በዓል ላይ የሚበጠብጡት? በማለት ልዑካኑን በመሞገት ቅሬታቸውን ማቅረባቸው ነው የተሰማው። ውይይታቸው ይሄ ብቻ አልነበረም። ዝርዝሩን በሰፊው እመለስበታለሁ።
… በሌላ በኩል ሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያሪኮች ስላረጁ በአስቸኳይ እንደራሴ ይሾምባቸው በሚል የቤተ ክህነቱ የጎልማሳ ጳጳሳት ስብስብና “የፀረ ትግሬ ንቅናቄ” ቡድን አባላት በሰፊው ንቅናቄ መጀመራቸው ተሰምቷል። ተራው የኦሮሞ ነው መሆን ያለበት በሚል በኦሮሞዎቹ ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ ፉክክሩ የቀለጠ ሲሆን የወጣቶቹ ጳጳሳትና ከአሜሪካ የመጡቱ ከአንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ጋር በመሆን “ብፁዕ አቡነ ናትናኤል” ቢሆኑ ይሻላል በሚል ከውሳኔ ላይ እንደደረሱም ለመረዳት ተችሏል።
… የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ሥራ አስኪያጅነት ለቄስ በላይ መኮንን ለመስጠት የጨረሱ እንደሆነ ሲነገር ለእንደራሴነት ግን ፍትጊያው ደም እስከማፋሰስ እንደሚደርስ ሁሉ እየተነገረ ነው። የእነ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ቡድን በኢዜማ በኩል ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን እንደያዘና ብፁዕ አቡነ ናትናኤል እንደራሴ ቢሆኑ የሚል ፍላጎት ያሳየ ሲሆን በኦሮሚያ ቤተ ክህነት ትግል ወቅት ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገናል የሚሉት እነ ቀሲስ በላይ ደግሞ ከእነ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስን ለእንደራሴነት ካልሆነም ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስነት ለማሾም ብቻ ከኦሮሞ ነገድ አባላት መካከል ግን አንዳቸውን እናሾማለን የሚል ሃሳብ ይዘው በኦቦ ሽመልስ አብዲሳ በኩል ትግል መጀመራቸው ነው የሚነገረው።
…ትንቅንቁ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የሥልጣን ፍትጊያው እና የሥልጣን ጥሙ “የሁለቱንም ቅዱሳን ፓትሪያርኮች ህይወት” አደጋ ላይ እንዳይጥል የብዙዎች ስጋት መሆኑም ነው የሚነገረው። በተለይ ትግሬ ናቸው በሚል በአፍቃሬ መንግሥቱ ካድሬ የቤተ ክህነቱ ሰዎች የተጠመዱት ቅዱስ ፓትርያርክ አባ ማትያስ በዙሪያቸው የሚገኙትን በሙሉ ወደ ወኅኒ ጥለው ሞራላቸውን በመንካት ቅዱስነታቸው በንዴትና በብስጭት እንዲሞቱ ለማድረግ በብዙ ቢለፋም የቅዱስነታቸው የሃይማኖት ፅናት፣ እንዲሁም ፈቃደ እግዚአብሔርም ስላልሆነ እስከአሁን አንዳች ነገር ሊሆኑላቸው አልቻሉም።
…የሰላም ሚንስትር የነበረችው ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ባለፈው ዓመት ለወርሀ ግንቦት እንደራሴ ለመሾም ከጫፍ ደርሰው የነበሩትን የቤተ ክህነቶቹን ጳጳሳት “ምርጫው እስኪያልፍ ታገሱ” በማለት ያስቀሩ የነበረ ሲሆን ከፊታችን በሚመጣው በመጪው የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ግን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን አውርደው እንደራሴ ለመሾም በተለይ ከአሜሪካ ጠሚ ዐቢይ አሕመድን ተከትለው የመጡት አባቶች ኢትዮጵያ ከሚገኙትና አንዳንድ ቅዱስነታቸውን በዘራቸው ምክንያት ትግሬ በመሆናቸው ብቻ ከህወሓት ጋር አዳብለው ከሚጠሉት ጥቂት አባቶች ጋር በመሆን ሊያወርዷቸው ዶልተው መጨረሳቸው ነው የሚሰማው። በጥቅምቱ ጉባኤ በምልአተ ጉባኤው እምቢተኝነት ምክንያት ካልተሳካ ግን የማፍያው ቡድን ልክ እንደ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ለመንግሥት አሳስሮ በገመድ አሳንቆ መግደል ባይሆንለትም እንኳ ራሱ ግን አረጋውያኑን ከመግደል እንደማይመለስ የሚናገሩም አሉ።
… ዝርዝሩን በሰፊው የምመለስበት ቢሆንም ወንድሜ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ግን እጅህን ከእነዚህ ቆሻሻ ሃሳብ ካላቸው ሰዎች መካከል ብታርቅ ደስስ ይለኛል። ቤተ ክርስቲያንን አንድ በማድረጉ በኩል የደከምከውን ድካም እኔ በግሌ አውቃለሁ። አሁን ደግሞ ሁሉን ነገር በአንተ እያሳበቡ፣ በአንተ ስም እያስፈራሩ፣ ከምስኪን አባቶች በሰፊው ገንዘብ የሚሰበስቡ አውሬዎች መኖራቸው ሳያንስ ይባስ ብለው አሁን ደግሞ የአንተንና የጠቅላይ ሚንስትሩን ግኑኝነት ሽፋን አድርገው በስምህ የሚያደርጉትን ሕገወጥ እንቅስቃሴ ልታስቆም ይገባል። እንቅስቃሴውን አንተም የማትደግፈው ከሆነ ማስቆሙ ለአንተ ብዙም ከባድ አይሆንም ብዬም አምናለሁ።
… ወዳጄ አባቴ ብፁዕ አቡነ ናትናኤልም እንደራሴነት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ከፈቀደ ለፓትርያርክነትም ለመድረስ ሰፊ ጊዜ ስላሎት አሁን ላይ ትግሬን አውርደን ኦሮሞ እንሾማለን ከሚለው የማፍያ ስብስብ ቢያርቁ… ከምክረ አይሁድ ከሸንጎውም ራስዎን ገለል ቢያደርጉ መልካም ነው ብዬ ወደላይ አንጋጥጬ ሃሳቤን አቀርባለሁ። እርስዎ ትግሬ ዐማራ ጨዋታ ላይ መግባቱ አያምርብዎትም። ሌሎቹ ግን እንደፈቃዳቸው እንዳሻቸው ቢሆኑም ብዙም ግድ አይሰጠኝም።
… አረጋውያኑ የማረፊያ ጊዜያቸው ደርሶ ሲያርፉ ለሚደርስ ሹመት ከወዲሁ እነሱን አስወግዶ ገድሎ በዚህ መንፈሳዊ ስፍራ ላይ ለመሾም እንዲህ መራወጥን ምን ይሉታል? ብር ከፈሎ መሾም የለመደ ሁሉ አሁን ገድሎ ከመሾም እንደማይመለስ እየገባኝ መጥቷል። እነ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ሁሉም ነገር በቃን ብለው ከገዳም በገቡበት ዘመን ምን ደስስ የሚያሰኝ ነገር አለና ነው እንዲህ ለሥልጣን መሻኮት?
… ይቆየን እመለስበታለሁ።
Filed in: Amharic