– አቶ ሙስጠፌ መሀመድ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር
(ኢ ፕ ድ)
አሸባሪው ህወሓት የበላይነቴን አስቀጥላለሁ ካልሆነም ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ የሚል የሞኝ ዘፈን እየዘፈነ ነው ሲሉ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ።
አቶ ሙስጠፌ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አሸባሪው ህወሓት ሁለት ግልጽ ዓላማዎች አሉት። አንደኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ለእኔ ጥቅም የቆመ መንግሥት መምጣት አለበት የሚል ነው። እንደአለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን እንደፈለኳት የማልዘውራት ካልሆነ ደግሞ ትግራይ ትገነጠላለች የሚል ሁለተኛ አቋም ያራምዳል።
ይህንንም የሽብር ቡድኑ አላማ ከአዘጋጃቸው ዶክሜንቶችና ከተግባሩ መረዳት ይቻላል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ እነዚህ የአሸባሪ ቡድን ዓላማዎችን ደግሞ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት የሚቀበላቸው አይደለም።ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆና ሰላሟ ሰፍኖ እንድትቀጥል ከተፈለገ በእኔ እምነት አሸባሪው ህወሓት መወገድ አለበት ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ የህወሓት 27 ዓመታት የግፍ አገዛዝ ስርዓት እንዲቀጥል የሚፈልግ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሌለ ገልጸው፤ትግራይን እገነጥላለሁ የሚለው ዓላማውም ከውጭ ኃይል ጋር ተባብሮ ኢትዮጵያን የማፍረስ ተላላኪነቱን የሚያረጋግጥ ማሳያ በመሆኑ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት እንደማይፈቅድለት ተናግረዋል።
ሁለቱም ዓላማዎቹ በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት በኩል ተቀባይነት ማግኘት ስለማይችሉና ከኢትዮጵያውያን ፍላጎት ውጪ ስለሆነ አሸባሪው ህወሓት ቡድን መወገድ አለበት ብለዋል።