>

የመጋረጃ ጀርባና የዉሸት ምስክርነት በ"አዲሱ ምዕራፍ" ይቀጠል ይሆን ?!? (ግርማ ካሳ)

የመጋረጃ ጀርባና የዉሸት ምስክርነት በ”አዲሱ ምዕራፍ” ይቀጠል ይሆን ?!?

ግርማካሳ

    የባልደራስ አመራር አባላት፣ እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም፣ አስካለ ደምሌና ሌሎች ይኸው ከታሰሩ አንድ አመት ከአራት ወር ሊሆናቸው ነው፡፡ የታሰሩት “ሳናጣራ አናስራም” ባሉት የዶር አብይ አህመድ የብልጽግና መንግስት ነው፡፡
    ከብዙ መንገላታትና መጉላላት በኋላ የኦህዴድ/ብልጽግና አቃቤ ሕግ ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ/ም አስራ ሶስት ገጽ ያለበት፣ ከአንድ አገር አቃቤ ሕግ የማይጠበቅ እጅግ በጣም የወረደ፣ ክስ መሰረተ፡፡ ( እዚህ ጋር የኦህዴድ አቃቤ ሕግ የምለው የአቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ለአገር ጥቅም፣ ለፍትህ መስፈን ሳይሆን ለኦህዴድ/ኦሮሞ ብልጽግና የሚሰራ ነው ብዬ ስለማምን ነው)
   ክሱ ሁለት ክሶችን ያካተተ ነው። በአንደኛው ክስ እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም ፣ አስካለ ደምሌ ተካተዉበታል። ከ”ሽብርተኝነት” ጋር በተገናኘ የቀረበው 2ኛ ክስ ደግሞ እስክንድር ነጋንና ሌሎች የማይታወቁ፣ ያልተያዙ ሁለት ተከሳሾችን ያካተተ ነው።
   የመጀመሪያው ክስ በሁለት የሚከፈል ነው። አንደኛው ክፍል ከሃጫሉ ግድያ በፊት ተፈጸሙ የተባሉትን ያካተተ ሲሆን፣ ሁለተኛ ክፍል ከሃጫሉ ግድያ በኋላ ተፈጸመ ያሉትን ያካተተ ነው። ሁለተኛ ክስ የሽብርተኝነት ክስ ነው
    በክሱ ምንም አይነት የሰነድ፣ የፎረንሲክ፣ እንደ ኦዲዮ፣ ቪዲዮ ኤሜል፣ የፌስ ቡክና የትዊተር ፖስቶች የመሳሰሉ የኤሌክቶሮኒክስ መረጃዎች አልቀረቡም፡፡ ኢንሳ የነ እስክንድር ስልክ እየጠለፈ እንደሚሰማ የሚታወቅ ነው፡፡ እንደ ማስረጃ የተጠለፈ ንግግር እንኳን አልቀረበም፡፡ “ምክንያቱ ምንድን ነው ?” ቢባል መልሱ ቀላል፡፡ ምንም አይነት የከሰሱበትን ክስ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ባለማግኘታቸው ነው፡፡
    ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ/ም ክስ እስኪመሰረትባቸው ጊዜ የባልደራስ አመራሮች በርካታ ጊዜ ፍርድ ቤት ተመላልሰዋል፡፡ ለመስከረም 7 2013 ዓ/ም ይቀጠራሉ፡፡
    መስከረም 7 ቀን 2012 ዓ/ም ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡  የቀረቡ ክሶችን መርምሮ የዋስትና መብት ይሰጥ ወይንም አይሰጥ በሚለው ዙሪያ የተደረጉ ክርክሮችን ያደመጠው የልደታ ችሎት ፍርድ ቤት፣ ውሳኔ ለመስጠት ለመስከረም 12 ቀጠሮ ሰጠ፡፡
     መስከረም 12 ቀን 2012 ዓ/ም ፣ የዋስትና  መብት መከበርን በተመለከተ ውሳኔ እሰጣለሁ ያለው ፍርድ ቤት፣  አቃቤ ህግ የመሰረተውን ክስ ግልፅነት ይጎድለዋልና ከሱ ተሻሽሎ ይምጣና በሚቀጥለው ሳምንት እወስናለሁ ብሎ ከሳምንት በኋላ ለመክሰረም 19 ቀጠሮ ሰጠ፡፡እስከ መስክረም 12 ድረስ የባልደራስ እስረኞች ከአስር ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት ተመላልሰዋል፡፡
    መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ/ም አቃቤ ህግ ክሱን አሻሽሎ አቀረበ፡፡ በቀረበው ክስ ላይ መቃወሚያ የተከሳሽ ጠበቆች፣ መሰከረም 29 በፁሁፍ እንዲያቀርቡ፤ እነ እስክንድር ደግሞ ጥቅምት 12 ፍ/ቤት እንዲገኙ ፍርድ ቤቱ ወሰነ፡፡
    ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ/ም ፣ አቃቤ ህግ ፣ በክሱ ያቀረበው ምንም አይነት ሌላ ማስረጃ የለም፡፡ የሰዎች ምስክርነትን ብቻ ነበር፡፡ በመሆኑ ያለውን ብቸኛ ማስረጃ ፣ ምስክሮቹን የሚያሰማበት ጊዜ ነበር፡፡ አቃቤ ሕግ፣ “አሻፈረኝ፣ ምስክሮቼን በዝግ ችሎትና ከመጋረጃ በስተጀርባ ነው የማሰማው” አለ፡፡ እነ እስክንድርና ጠበቆቻቸው፣ “ምስክር መደመጥ ያለበት በግልጽ በህዝብና በሚዲያ ፊት ነው እንጅ ከመጋረጃ በስተጀርባ መሆን የለበትም፡፡ ማንና እንዴት በኛ ላይ እንደሚመሰክር ስለማናውቅ፣ ምስክሮች የሚሰጡት ቃል ታአማኒንት በጅጉ ስለሚያሳስበን፣ ምስክሮቹ በግልፅ መቅርብ አለባቸው” በሚል ተቃውሞ አሰሙ፡፡ ፍ/ቤቱ  ምስክሮቹ በምን መልኩ ይቅረቡ የሚለውን ለመወሰን ፣ ለህዳር 29 ቀን የ50 ቀን  ረጅም ቀጠሮ ሰጠ፡፡
    ምን አለፋችሁ አቃቤ ሕግ አሉኝ የሚላቸውን ምስክሮች በግልጽ ችሎት ለማሰማት ስላልፈለገ ፣ አንዴ ከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ ሌላ ጊዜ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ክለዚያ ሰበር ችሎት እያለ፣  ፍርድ ቤቶች የባልደራስ እስረኞችን ጉዳይ እንደ ኳስ ተቀባበሉት፡፡ ፍትህን ማስፈን ተስኗቸው፣ የተቀመጡበትን የዳኝነት ክብር አዋርደው፣ ዜጎችን ያለ ወንጀላቸው በግፍ እንዲሰቃዩ አደረጉ፡፡ ባልደራሶች ከፍርድ ቤት ወደ ፍርድ ቤት ሳይታክታቸው ተመላለሱ፡፡ ፍትህን ግን ማግነት አልቻሉም፡፡
    ሰኔ 2013 ዓ/ም ቀጠሮ ነበራቸው፡፡ እንደገና ለሶስት ወር ፣ ለጥቅምት 4 2014 ዓ/ም ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ሰጠ፡፡ እነ ኮሚዲያን ልመንህ ታደሰ አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ሄደው ከተመለሱ በኋላ የሰሩት አስቂኝ ድራማ ነበር፡፡ ስለአሜሪካ ሲናገሩ፣ “በሕንጣ ላይ ሕንጣ” ነበር ያሉት፡፡ አሁን የባልደራስ እስረኞች ጉዳይ በቀጠሮ ላይ ቀጠሮ እየሆነባቸው ነው፡፡ ፍርድ ቤቶችም  ፍርድ ቤት ሳይህ ፍርድ ጨፍላቂ ሆነዋል፡፡
    “ዳኞች ለምንድን ነው ፍትህን ማስፈን ያልቻሉት ?” ብለን ብንጠይቅ፣ ልክ በሕወሃት ጊዜ እንደነበረው ዳኞች ነጻ ስላልሆኑ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ከነ ዶር አብይ አህመድ ፍቃድ ውጭ ብትሆን፣ የከፍተኛው ሆነ የሰበር ችሎት ዳኞች ከኦህዴድ ብልጽግና ፍቃድ ውጭ ቢሆኑ፣ በሃላፊነታቸው መቀጠል አይችሉም፡፡ ቦታቸውን ያጣሉ፡፡ ስለዚህ አራት ኪሎን ላለማስቀየም ዜጎችን ያጉላሉ፡፡
    ስለዚህ የባልደራስ እስረኞች ጉዳይ ፍርድ ቤቶች ጋር ሳይሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ጽ/ቤት እና ለጠቅላይ ሚኒስተሩ የሚታዘዘው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ዶር ጌዴዎን ማቴዎስ ጋር ነው፡፡
     ዶር አብይ አህመድም ሆነ ዶር ጌዴዮን ያውቃሉ እነ እስክንድር ቅንጣት ያህል ወንጀል እንደሌለባቸው፡፡ ያውቃሉ የአቃቤ ሕግ ምስክሮች የዉሽትና የፈጠራ እንደሆኑ፡፡ ያውቃሉ የመጋረጃ ጀርባ ምስክርነት በየትም አገር ያልተለመደ አሳፋሪ አሰራር መሆኑን፡፡ ያውቃሉ ክርክር ሳይደረግ ከአንድ አመት በላይ ዜጎች ማሰር አረመኔነት መሆኑን፡፡
  እንግዲህ አዲስ ምእራፍ መጥቷል አይደለም ያሉን፡፡ በአዲስ ምእራፍ ከአሮጌው፣ አስቀያሜው፣ ሰይጣናዊ፣ ወያኒያዊው አሰራራቸው ወጥተው፣ መሰረታዊ የሆነው ፍትህን የማስፈን ውሳኔ ይወስኑ፡፡ በፍርድ ቤቶች ጣልቃ መግባታቸውን ያቁሙ፡፡ በዳኞች እግር ላይ ያሰሩት ሰንሰለት ይበጥሱ፡፡ “በዚህም በዚያም እነ እስክንድር እንዲፈቱ እንዳታደረጉ” ብለው ያስተላለፉትን ሰርኩላር ይሰረዙ፡፡
   ከባልደራስ እስረኞች ውጭ ሌላ የታሰሩ እስረኞችም አሉ፡፡ እነ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባና ሌሎች፡፡ እነርሱም ቢሆን ፍትህ ሊነፈጉ አይገባም፡፡ ማንም ሰው በፍትህ እጦት መንገላታት የለበትም፡፡ የተፋጠነ ፍትህ ማግኘት አለባቸው፡፡ ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ በግልጽ ችሎት ራሳቸውን የመከላከል እድል ተሰጥቷቸው፣ የሚቀጡ ከሆነ ይቀጡ፣ የሚለቀቁ ከሆነም ይለቀቁ፡፡ ክርክር ሳይሰማ በተልክላሻ ምክንያቶች በቀጠሮ ላይ ቀጠሮ እየተሰጠ መንገላታት የለባቸውም፡፡
  መታወቅ ያለበት ግን የነ ጃዋር ጉዳይ ሌላ ነው፣ የነ እስክንድር ጉዳይ ሌላ ነው፡፡ ለነ ጃዋር ተብሎ፣ እነ እስክንደር ነጋ የሚታሰሩበት ምንም ምክን ያት የለም፡፡ እነ እክንደርንም ለመፍታት ወንጀለኛ ከሆኑ እነ ጃዋር የሚፈቱበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ወንጀል መስራታቸው ካልተረጋገጠ ሁሉም ይፈቱ፡፡
    (በነገራችን ላይ እነ እስክንደር ይፈቱ እያልኩ አይደለም፡፡ አቃቤ በዝግ ከሶ የለም፣ በግልጽ  ችሎት ምስክሮቹን ያሰማ፡፡ ከዚያ እነርሱ ራሳቸውን በበቂ ሁኔታ በግልጽ ችሎት ይመክታሉ)
Filed in: Amharic