>

ታሪክን በማጥፋት ታሪክ መስራት አይቻልም ‼ ይድረስ ለከንቲባ አዳነች አቤቤ  (ጴጥሮስ አሸናፊ)

ታሪክን በማጥፋት ታሪክ መስራት አይቻልም ‼

ይድረስ ለከንቲባ አዳነች አቤቤ 

ጴጥሮስ አሸናፊ

በ1952 ዓ/ም በአዲስ አበባ ጨርቆስ አካባቢ የተመሠረተው አጋዚያን ትምህርት ቤት በከንቲባ አዳነች አቤቤ በዛሬው ዕለት ስሙ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተቀይሯል። ይህ ትምህርት ቤት በግርማዊነታቸው ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ቢመሠረትም ከኋላ የመጣውና የበርካታ ተቋማትን ስም የቀየረው ደርግ ስሙን ሳይለውጠው በኋላም በሕወሓት አገዛዝ የቀደመ ስሙን ይዞ ቆይቷል። ከንቲባ አዳነች ስሙን ለመቀየር የተነሳሱበት ምክንያቱ ምን ይሆን?  ትምህርት ቤቱስ አስቀድሞ ለምን አጋዚያን ተባለ? አጋዚያንስ የተባሉት እነማን ናቸው።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ አጋዚያንን በተመለከተ ሲናገሩ:
አባታችን ኖኅ ሦሰት ልጆች ይወልዳል፤ ካም፣ ሴም ያፌት፡፡ ከጥፋት ውኃ መጉደል በኋላም የኖኅ መርከብ በደቡባዋዊ ጣና ሐይቅ በዘጌ ባሕረገብ አካባቢ የሚገኘውን የጣና ሐይቁን ወለል አድርጎ በሚያሳየውን አራራት ተራራ ላይ ያርፋል። ከዛም ካም ከአባቱ ከኖኅ ጋር ኢትዮጵያ ትቀርና፣ ሴም እስያን፣ እንዲሁም ያፌት አውሮፓን መግዛት ጀመሩ፡፡ ሴም ዘጠኝ ልጆችን ወለደ፡፡ ከነሱ መካከል ሣሕላን ከሚባለው ልጁ ዮቅጣን ይወለዳል፡፡ ዮቅጣንም 13 ልጆች ይወልዳል፡፡ ከነሱም አምስቱ ሣባ፣ ኦፊር፣ አቢማር፣ ሐዊላ እና አባል ነበሩ፡፡ የዮቅጣን ልጆች ነገደ ዮቅጣን የሚባል ነገድ ይፈጥራሉ፡፡
1ኛ ዜና መዋ 1፤17-21 ፣ ዘፍ 10
 ይህ ነገድ በመካከላኛው ምሥራቅና በየመን ሲኖሩ የህንድ ነገሥታት ሲያስቸገሯቸው በቀይ ባሕር በኩል ወደ ኢትዮጵያ ይሻገራሉ፡፡ ከዛም አምሰት ዓመት በወቅቱ ለነበረው ለካም ነገድ ነገሥታት ሲገብሩ ይቆያሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የህንድ ንጉስ ራማ/ብርሀማ ኢትዮጵያን መጥቶ ስለ ወረረ እነኝህ ነገደ ዮቅጣኖች ራማን በመውጋት የካሙን ነገድ ነጻ ያወጡታል፡፡ ከዛም ከሳባ ልጆች በምክክር አክናሁስ ተመርጦ ነገሰ፡፡ ነጻ ያወጡትን መንግሥት ስለያዙ አጋዚያ ተባሉ፡፡ ትርጉሞም ነጻ የሚያወጣ ማለት ነው፡፡ ይህም በ1980 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ላይ ነበር፡፡
በሌላ መልኩ አጋዚ ማለት በግእዝ ቋንቋ ተናጋሪ ከጋዛ የመጣ ማለት ሲሆን ይህም ከቀዳማዊ ምንሊክ፣ ከንግሰተ ሳባ፣ ከጠቢቡ ሰሎሞን ልጅ ጋር ከመጡት ከ12 የእስራኤል የተውጣጡ ከ12 ሺህ የእስራኤል የበኩር ልጆች ጋር ይያያዛል፡፡
እስራኤል አሥራ ሁለት (12)  ነገድ ሲኖራት የተሰየሙበትም በአሥራ ሁለቱ (12)  የያዕቆብ ልጆች ማለትም በሮቤል፣ ስምኦን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ዳን፣ ንፍታሌም፣ ጋድ፣ አሴር፣ ኢሳኮር፣ ዘሩባቤል፣ ዮሴፍ እና ብንያም ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም ከንግሥተ ሳባ/ንግሥተ አዜብ/ማክዳ የወለደውን ልጅ ቀዳማዊ ምንሊክ ከተወለደ ከ20 አመት በኋላ አባቱን ለማወቅ ከአክሱም ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለስ ከሶሰት አመት የህገ ኦሪትና የስርዓተ ንግሥና ትምህርት ከወሰደ በኋላ ሲመለስ አባቱ የዳዊት ልጅ ጠቢቡ ሰሎሞን ከታቦተ ጽዮን ጋር 12 ሺህ የእብራውያን የበኩር ልጆች ከየነገዱ አንድ ሺህ እያደረገ መላኩን ታሪክ ይናገራል፡፡ እነዚህም ግዕዝ ይናገሩ ስለነበር አጋዚያን ይባሉ ነበር፡፡
አክሱማዊያን ማን ናቸው ያሉ እንደሆነ በፊተኛው የካም ዘሮች ቀጥሎ የነገደ ዮቅጣን እና ከዛም ከእስራኤል የመጡ የ12ቱ ነገደ እስራኤል ቅልቅል የሆኑት ሳባውያን የአክሱም ስልጣኔ ባለቤት በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የእስልምና እምነት መስፋፋትን ተከትሎ የቀይ ባህርን ወደቦች አረቦች ሲቆጣጠሩት የአክሱም መዳከም ሲመጣ እንዲሁም በዮዲት ጉዲት/አስቴር ዘመን ከ 842-882 ዓ/ም ተሰደው ወደ ሸዋና ላስታ የሸሹት ነገዶች ናቸው፡፡
በሌላም በኩል የኢትዮጵያ ታሪክ ነገሥታት ዝርዝር ላይ በዘመነ ጲኦሪ 1ኛ ዘመን ላይ ከተከሰቱ ነገዶች ነገደ አጋዚአን ዋነኞቹ ናቸው። አጋዚአን ማለት በግዕዝ ነጻ አውጪ ማለት ነው።
በሰሙነ ትንሣኤ “ክርስቶስ ተንስአ እሙታን – በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን፤ አሠሮ ለሰይጣን – አግአዞ ለአዳም፤
ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ስልጣን ከሙታን ተነሣ፤ ሰይጣንን አሰረው አዳምንም ነጻ አወጣው እንላለን። አግአዞ ለአዳም (አዳምን ነጻ አወጣው) ከሚለው የምንረዳው  ክርስቶስ ነጻ አውጪ (አግዐዚ) ነው እንደ ማለት ነው። ቅድስት ሥላሴንም አጋዚተ ዓለም እንላለን።
በኢትዮጵያ ታሪክ እስከ ነገደ ጲኦሪ ድረስ የተዘረዘሩ ነገስታት ከነገደ “ካም” ናቸው ነገር ግን እዚህ ላይ ታሪክ ይቀየራል የሴም ልጅ የሆነው አርፋክደስ ልጆች ይወልዳል እርሱም ሳላህን፤ ሳላህ ኤቦርን፤ ፋሌቅንና፤ ዮቅጣንን ይወልዳል ዮቅጣን ደግሞ 13 ልጆችን ይወልዳል። ከእነዚህ 13 ልጆች አምስቱ ማለትም
ሳባ፣ ኦባል፣ ኦፊር፣ አቢማር እና ሐዊላ የሚባሉት ከወንድሞቻቸው ተለይተው ራቅ ወዳለ ስፍራ ይሄዳሉ። (በየመን አካባቢ ተጠግተው ይኖራሉ) በየመን ሳሉ የህንዱ ንጉስ እየወጋ ሲያስቸግራቸው የካሙ ነገድ በነገሰበት 1980 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከየመን ለቀው ወደ ኢትዮጵያ ይጠጋሉ በተለያዩ አቅጣጫ ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ።
ሳባ በትግሬ፣ ኦባል በአዳል፣ ኦፊር በኦጋዴን በኩል እነዚህ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ የመጀመሪያውን 5 አመት ለጲኦር እየገበሩ ነበር የኖሩት። በዚህ መካከል የህንዱ ንጉስ “ንጉስ ራማ” ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ጲኦሪን ወግቶ አሸንፎ ህዝቡን እንደ ባሪያ መግዛት ጀመረ በዚህ ጊዜ እነዚህ የዮቅጣን ልጆች ተሰባስበው ራማን ወግተው አሸንፈው የካሙን ነገድ ነጻ አወጡት ተመካክረውም የሳባን ነገድ “አክናሁስን” አነገሱት እናም ነጻ ያወጡትን ሃገር ያዙት መንገስቱንም ተረከቡ በዚህ ምክንያት “አጋዚአን” ተባሉ።
በዚህ ጊዜ የኢትዮጵያ ነገሥታት ዝርዝር ከነገደ ካም ወደ ነገደ ሴም ተሸጋግሯል። አገሪቱም “ብሔረ አጋዚያን” ተባለች ቋንቋቸውም “ግእዝ” ተባለ ይላሉ ተክለፃድቅ መኩሪያ።
በመጀመሪያ በኩሽ ቀጥሎ በናምሩድ ልጅ አቢስ አቢሲኒያ ከዚያም በሳባ ኖባ ስያሜ ኑብያ እየተባሉ ሲጠሩ ቆይተው የሴም ዘሮች ውስጥ ነገደ አጋዚአን ከመጡ በኋላ ደግሞ ከእነሱ አንዱ በሆነው በኢትዮጲስ 1ኛ ኢትዮጲስ ተብላ መሰየሟና በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ በገቡት ሃበሳን ምክንያት ሃበሻ ተብለዋል። ሃበሻ ማለት ድብልቅ ሲሆን የተለያዩ የነገዶች ድብልቅ መሆናችንን የሚያሳይ ነው
በሌላ በኩል ደግሞ ሀበሻ የተባለበት ምክንያት በዛሬው ምዕራብ የመን የሚገኘው የሀገሩ ስም ሀበሳት ሲሆን ሰዎቹ ሃበሳት የተባሉት “ሃበሳ” ከሚባል ነገድ አባት የተገኙ የነበሩና እነዚህ ነገዶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሰሜኑ ክፍል ስለተቀመጡ ሃበሳ የሚለው መጠሪያ ደግሞ በሳባውያን ፊደል “ሳ” የነበረው በአረበኛ “ሳ” ወደ “ሻ” ተለውጣ “ሐበሻ” የሚለው መጠሪያ አገኙ ይሉናል።
ኢትዮጵያ 🟩🟨🟥
በሱባ ቋንቋ ኢት ማለት ስጦታ ዮጵ ማለት ቢጫ ወርቅ ማለት ሲሆን የሱባ ቋንቋ ደግሞ የሴማዊያን ነገድ ቋንቋ ነው። እንደ መሪ ራስ አማን አገላለጽ “መፅሃፈ አብርሂት 1999 ዓ.ም”
ኢት —–ስጦታ
ዮጵ —–ቢጫ ወርቅ
ግዮን —–ፈሳሽ ወንዝ
አንድ ላይ “ኢትዮጵግዮን” በአማርኛው ትርጉም ደግሞ የግዮን ወርቅ ስጦታ ተብላ ኢትዮጵያ ትጠራ እንደነበር የሱባ ቋንቋን ዋቢ አድርገው ይገልፃሉ። ነገር ግን በቋንቋ ማደግ ውስጥ ኢትዮጵግዮን ወደ ኢትዮጵያ አንሶ አሁን ላይ ያለውን ስያሜ ይዟል።
ግን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አጋዚያንን ለምን ጠሉት?
Filed in: Amharic