አዲስ አበባ፡- አዲሱ መንግሥት እንደጀመረው አካታችና አማራጭ የፖለቲካ አካሄድ ቢኖር ኖሮ ወደ ትጥቅ ትግል አልገባም ነበር ሲሉ የቀድሞ ኦነግ አመራር አባልና በአሁኑ ወቅት በሳውዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ሌንጮ ባቲ ተናገሩ።
አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፣ በኢትዮጵያ በተዛነፈና በአግላይ የፖለቲካ አስተሳሰብ ምክንያት አገሪቱ በቅራኔ ውስጥ ዘመናትን እንድታሳልፍ ተገዳለች።
የሕዝቡ የዘመናት ጥማት የነበረው የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚያመጣ፣በሕዝቦች መካከል እኩልነትና ወንድማማችነት እንዲሰፍን የሚተጋ፣ተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ አንዱ የአገሪቱ ባለድርሻ አካል አይቶ የሚያበረታታ ባለራዕይ መሪ ማግኘት እንደ ነበር ያነሱት አምባሳደር ሌንጮ፣ በእሳቸው እምነት ያ የነበረው ምኞት አሁን እውን መሆኑን ገልጸዋል
በተለይ ከ60ዎቹ ጀምሮ እስከ ኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት በአገሪቱ እንደ ቡድንም ሆነ እንደ ግለሰብ የፖለቲካ ተሳትፎና የመብት ጥያቄ ያነገቡ ወጣቶችና ምሁራን ሕይወታቸውን ጭምር በመገበር ዋጋ መክፈላቸውን ያስታወሱት አምባሳደሩ፣ በሕዝቡ መራራ ትግል ወደ ሥልጣን የመጣው መንግሥት ለሕዝብ ጥያቄዎች ተገቢውን ክብር በመስጠትና የተለያዩ አስተሳሰቦች እንዲንሸራሸሩ በማሰብ ከሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለመስራት የሚያደርገው ጥረት የሚያስመሰግነው ተግባር ነው ሲሉ አድንቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይቅርታና በመደመር እሳቤ አገሪቱን ወደ ተሻለ ሰላምና ልማት ለመውሰድ ከሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመስራት ያሳዩት ቁርጠኝነት ያደነቁት አምባሳደር ሌንጮ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ ከምርጫው በፊት ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በምርጫ ብሎም በአገሪቱ ፖለቲካ እንዲሳተፉ በሽምግልና ጭምር ተደጋጋሚ ጥረት ማድረጋቸውን በቅርበት እንደሚያውቁና ሀሳቡን ተቀበለው ወደ ፉክክር የገቡ ፓርቲዎች እንዳሉ ሁሉ እስከ መጨረሻ ዕድሉን ያልተጠቀሙ እንዳሉ አስረድተዋል።
በዘንድሮ ዓመት በአገሪቱ የተካሄደው ምርጫ ታሪካዊና አዲስ ምዕራፍ መሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም ያሉት አምባሳደሩ፣ የተጀመረው የዲሞክራሲ ሂደት መሰረት እንዲይዝና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ከመታገል ውጪ በትጥቅ ትግል ወይም በሌላ አማራጭ ኢትዮጵያን ሌላ ቅርጽ ለማስያዝ የሚደረገው ማንኛውም ትግል ትርፉ ድካምና ከንቱ ልፋት መሆኑን ያመላከተ መሆኑን ተናግረዋል።
የአገሪቱ የፖለቲካ ቅኝት ባህልና የአመለካከት ዘይቤ በመቀየር ከጊዜ ጋር አብሮ በመዘመን ከትጥቅ ትግል እሳቤ ውጪ ያሉትን አማራጮች ማሰብ ካልተቻለ መዘዙ ወደኋላ የሚወስድና ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑ አገሪቱ ያለፈችበት ጎዳና ማየት በቂ ነው ያሉት አምባሳደር ሌንጮ፣ የትጥቅ ትግል ጊዜ ያለፈበት ፋሽን መሆኑን ተገንዝቦ እራስን ለዴሞክራሲያዊ ውድድር ማዘጋጀት ዘመኑ የሚጠይቀው የፖለቲካ ስልት መሆኑን ጠቁመዋል።
በአገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲረጋገጥ የተቋማት ግንባታ ማፋጠን፣ በዚያው ልክ ብቁና ቁርጠኛ አመራሮችን መመደብ፣ ሌብነት መጠየፍ እንደሚገባና በተለይ በትምህርት ዘርፍ ጠንካራ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በዘርፉ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑን በቅርበት ሰለሚያውቋቸው ዘርፉን ውጤታማ እንደሚያደርጉ ጽኑ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ዋቅሹም ፍቃዱ