>

አስካለ ደምሌ ማን ናት ?!

አስካለ ደምሌ ማን ናት ?!

ጌጥዬ ያለው

ወ/ሪት አስካለ ደሞሌ በ1984 ዓ.ም. በጎጃም መርጦለማርያም ተወለደች። ከልጅነቷ ጀምሮ  እድገቷ በሸዋ፤ አዲስ አበባ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በኮተቤ  ደጃዝማች ወንድ ይራድ ትምህርት ቤት፣ በአምሀ ደስታ፣ በአብርሀ ወአፅብሐ እና በቁስቋም ጣይቱ ብጡል  ትምህርት ቤቶች ተምራለች። በተጨማሪም የሁለተኛ  ደረጃ ትምህርቷን  በየካቲት 12 ትምህርት ቤት ተከታትላለች።
በቀድሞው ተፈሪ መኮንን ትምርት ቤት በአሁኑ እንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በዲፕሎማ አካውንቲንግ  አጥንታለች። ከዚህ በመቀጠል በጌጅ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በዲግሪ አካውንቲንግ ተምራለች።
አስካለ አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋምን ጨምሮ ለአለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተለያዩ መንግሥታዊ  ተቋማት በሙያዋ አገልግላለች። ባገለገለችባቸው የመንግሥት የአስተዳድር መሥሪያ ቤቶች የአዲስ አበባ የኗሪነት መታወቂያ ካርድ የከተማዋ ኗሪ ላልሆኑ ሰዎች በሕገ ወጥ ሂደት ሲሰጥ በማየቷ ተቃውማለች። በድንች ማህተም የተሰሩ መታወቂያዎችን በማጋጥም ትግሏን ገና  ከቢሮ ሳትወጣ  ጀምራዋለች። የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ሲመሰረት ጀምሮ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ከተቋቋመ በኋላም ሰፊ  የትግል እንቅስቃሴዎችን አድርጋለች። የፓርቲው ከፍተኛ አደራጅ በመሆን ብሎም የድርጅቱ የሴቶች አደረጃጀት ሓላፊ በመሆን ታግላለች። ከእነ  እስክንድር ነጋ ጋር   በሀሰት የሽብር ወንጀል ተከሳ ቃሊቲ ወህኒ ቤት ብትገኝም አሁንም በድርጅቱ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች ነው።
ወ/ሪት አስካለ ደምሌ ከተከሰሰችባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ‘የኦሮሞ ወጣቶች የምኒልክን ሀውልት እንዳያፈርሱ ተከላክለሻል’ የሚል ነው።
‹‹የመንግሥት ሠራተኛ ሆኜ ሥሠራ በጥቅማጥቅም ደልለው ኃሳቤን ለማስጣል ሞክረዋል፡፡ ከደረጃየ በላይ አመራር እንድሆን እና የጋራ መኖሪያ ቤት እንዲሰጠኝ ተጠይቄያለሁ፡፡ በኋላም ‹መንግሥት ደሞዝ እየከፈለሽ መንግሥትን መቃወም አትችዪም› ተብያለሁ፡፡ ሦስት ጊዜ ታግቻለሁ፡፡ ደህንነቶች (መንግሥታዊ ሰላዮች ማለቷ ነው)  አስፈራርተውኛል፡፡  በተመሳሳይ የመንግሥት የወረዳ አመራሮች አስፈራርተውኛል፡፡ ለችሎቱ መናገር የማልችላቸው ወንጀሎች ተፈፅመውብኛል፡፡ ‹የአማራ እና የደቡብ ተወላጆችን አንድ ላይ አደራጅተሻል› ተብየ ነው የተወነጀልኩት፡፡ የደህንነቶችን ስልክ ቁጥር መዝግቤ ይዣለሁ ማንነታቸው ይጣራልኝ፡፡›› ብላለች  አስካለ ደምሌ ታሕሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የእምነት ክህደት ቃሏን ስትሰጥ።
አስካለ ወጣትነቷን ለዴሞክራሲና ለነፃነት አሳልፋ የሰጠች የነፃነት ታጋይ ነች።  አንዳች ወንጀል የለባትም፤ በአስቸኳይ ክሷ ተቋርጦ ትፈታ!
Filed in: Amharic