>

የበደል እምባ (ዘምሳሌ)

የበደል እምባ

ዘምሳሌ


ባለጊዜ ሆነው ድምፃቸው ሲሰማ
የጥላቻውን ጡብ ሲሰሩ ከተማ
ንፁሃን ሲጠፉ ገጠር ከከተማ
ሕዝብን እያሞኙ ሰምተው እንዳልተሰማ

የማይፀና  ዝና  ዘርን ተንተርሰው
ስልጣን ሲታበዩ ቃላቸውን ኣጥፈው
ታሪክ አጠልሽተው በርዘው ደልዘው
ሀገር  ጠል ሰዎች  ፖርላማ አስገብተው

ጥጋበኛ አራጆች  እጃቸው ደም  መልቶ
ጉርሱን ያጣ ህዝብም  ምሬት  ተበራክቶ
የገደለው ሲኖር የሞተላት ጠፍቶ
ኢትዮጵያን ያለ ልብ በቁም ተንገላቶ

ከፈፀሙት በደል  ስህተት ሳይማሩ
እነርሱ  ግን ብሰው ህዝቡን ሲያስመርሩ
ሀገር አጥፊዎችን ዝምብለው እያኖሩ
አባቶች የሰሩት   ድንበር  ሲያሰብሩ

አዕላፍ መሣሪያ ታጥቀው እያጠቁ
በወንጀላቸው ብሰው በህዝብ ቢሳለቁ
ባለስልጣናቱ  መፍትሄ አያፈልቁ
በሀገር ሲያፌዙ ወይ ስልጣን አይለቁ

መድረሱ አይቀርም  ሊያገኙ የእጃቸው
ሀገር ባንድ ቆሞ  በቃችሁ  ሊላቸው
የጊዜ ጉዳይ ነው ቀን ሊመጣባቸው
በደል እምባ ሊቀር  ሕዝብ ሊፈረድባቸው

 

Filed in: Amharic