የብርሃኑ ነጋ መርህ አልባ ንግዳዊ የፖለቲካ ጠበብትነት ያስደንቃል…!?! የአንዳርጋቸዉ የፖለቲካ ጠለፋም ያስገርማል…!?!
ሸንቁጥ አየለ
በቅንጅት 50% የሀገሪቱን ወንበር በህዝብ ይሁንታ አሸንፈዉ ሳለ የህዝብ ይሁንታ ይዘን ወደ ፓርላማ አንገባም ካሉት የቅንጅት አመራሮች አንዱ እና ዋናዉ ብርሃኑ ነጋ ነበር::
ያዉ ሰዉዬ ዛሬ ኢዜማ የሚለዉን የፖለቲካ የንግድ ድርጅቱን ከፊቱ አስቀድሞ ምርጫ ቢወዳደር አንዳች ሽርፍራፊ ወንበር ሳያገኝ ቢቀር የአቢይ ተላላኪ ለመሆን ሚኒስቴርነትን ተቀብሏል::
መርህ አልባ ንግዳዊ የፖለቲካ ጥበብ ይልሃል ይሄ ነዉ አይደል?
ህዝብ ሲመርጥህ እንቢ ትልና ገዥ ሲመርጥህ እሽ ትላለህ::ብርሃኑ ከትቂት አመታት በፊት ርባናቢስ የዲያስፖራ ምሁራንን ሰብስቦ ስለ ፖለቲካዊ ንግድነት ሲደሰኩርላቸዉ እግራቸዉን እያነሱ ብዙዎች እንዳጨበጨቡለት ዛሬም በሀገር ቤት ይሄንኑ የብርሃኑን መርህ አልባ የፖለቲካ ጥበብ የቀሰሙ ብዙ ወጣት ፖለቲከኞች ሞልተዋል::
በመሆኑም ተስፋ የተጣለባቸዉን ወጣት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ሳይቀር ብርሃኑና አንዳርጋቸዉ መክረዉና አማክረዉ በመርህ አልባ የፖለቲካ ጥበባቸዉ የአቢይ ሎሌ ማድረግ ብቻ ሳይሆን እንወክለዋለን ስለሚሉት ህዝብ እንዳይናገሩ ሁሉ አፋቸዉን አሲዘዋቸዋል::
ብርሃኑ ነጋም ሆነ አንዳርጋቸዉ ጽጌ ከወያኔ እስከ ኦህዴድ/ኦነግ አንድ የሚስማሙበት ነገር ቢኖር ሌሎች ነገዶች ሲጠቁ ለእርድ እንደቀረበ በሬ እያጓሩ ይጮሃሉ:: ሆኖም የአማራ ህዝብ “አማራ” ተብሎ ሲገደል ግን አማራ ተገደለ አትበሉ ምክንያቱም አማራ ካላችሁ ሀገር ይፈርሳል ብለዉ እንደ አሳማ እያናፉ ይጮሃሉ::
የአብኑ ትልቅ ሰዉ የምነዉ በለጠ ሞላ ሰሞኑን አንዳርጋቸዉ የትግል አርያዬ እና ሞዴሌ ነዉ ብሎ የነገረን ነገር አለ::ከአንዳርጋቸዉ: የሚገኝ የትግል አራያነት አማራ ሲጨፈጨፍ አማራ ታረደ ካላችሁ ሀገር ይፈርሳል እና ዝም በሉ የሚል ብቻ እንደሆነ በለጠ ሞላ ጠፍቶት አይደለም::ብርሃኑ እና አንዳርጋቸዉ መርህ አልባ ምክራቸዉን ሀገር ቤት ላሉ ወጣት ፖለቲከኞች አካፍለዉ እንጂ::
ብርሃኑ ነጋ የፖለቲካ ጥበቡን ተጠቅሞ ፖለቲካ ማለት ይሄ ነዉ የሚል ጠቢባዊ ምክር ለወጣቶቹ በማካፈሉ ጭምር መሆን አለበት የኦህዴዳዉያን/ኦነጋዉያን ተላላኪዎች እነ አንዳርጋቸዉ ጽጌ የእነ በለጠ ሞላ ሞዴል እና አርያ ፖለቲከኞች ሆነዉ የቀረቡት::
አንዳርጋቸዉ እና ብርሃኑ ነጋ የዲያስፖራን የዉጭዉን ሀገር የፖለቲካ ትግል ጠልፈዉ አስራ ሶስት አመታት እኪሳቸዉ ከተዉ እርባና ቢሱን የአማራ ምሁር በፕሮፖጋንዳ ልምጭ እየዥለጡ ሽቅብ ሽቅብ አዘልለዉታል::
በዲያስፖራ የሚገኘዉ ብዙሃኑ የአማራ ምሁር የአናሳነት ስነልቦና ስለተጠናወተዉ እራሱ ቆሞ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ይዞ ከመምጣት እና ሌሎች ነገዶችን አግባብቶ ወይም አስገድዶ ከመሰብሰብ ይልቅ እንደ ብርሃኑ አይነት መርህ አልባ የፖለቲካ ነጋዴዎች እንዲመሩት ሲባዝን የሚዉል ብኩን ነዉ::በዚህ ለአማራ ህዝብ ጥፋት እንዲሁም ለኢትዮጵያዊነት ጥፋት ግንባር ቀደሙ ተጠያቂ ጭምር ነዉ:: እነብርሃኑም ይሄን የዲያስፖራ ምሁር ጥባጢቤ ተጫዉተዉበታል::
ብርሃኑ እና አንዳርጋቸዉ አሁን ደግሞ ሀገር ቤት ገብተዋል::
የሀገር ቤቱንም የፖለቲካ ቀመር እንደለመዱት በመርህ አልባ ዙሪያ ጥምትም እና ዉጤት አልባ የፖለቲካ ግብ እያሳሰሩት ነዉ:: እነዚህ ሰዎች ያዉ አንዲት ስላቃዊ መፈክር አለቻቸዉ::አማራ ሲጨፈጨፍ አማራ ተጨፈጨፈ ካላችሁ ሀገር ይፈርሳል የሚሏት ግብዝ የአማራ ፖለቲከኞችን ማስፈራሪያ አለቻቸዉ::
በልባቸዉ ግን ያዉቃሉ::የጊዜ ጉዳይ እንጂ ! የሚሆነዉን ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ::ቢፈሩትም ቢጠሉትም የሚሆነዉ ሁሉ ይሆናል::ለጊዜዉ ግን ፖለቲካዉን ያለ መርህ እና በፖለቲካ ንግድ እየዘወሩት ነዉ::
የብርሃኑ ነጋ መርህ አልባ ንግዳዊ የፖለቲካ ጠበብትነት ያስደንቃል ! የአንዳርጋቸዉ የፖለቲካ ጠለፋም ያስገርማል::