>

አሳሳቢነቱ የቀጠለው የአገራችን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ !  ኢሰመጉ

አሳሳቢነቱ የቀጠለው የአገራችን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ! 


ጥቅምት 3 ቀን 2014 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ- ኢሰመጉ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት፤ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ በትኩረት እየተከታተለ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንዲገቱ እና የጥቃት ሰለባዎች አፋጣኝ
መፍትሔ እንዲያገኙ የሚያሳስቡ መግለጫዎችን በማዘጋጀት ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ሲወተውት ቆይቷል፤ አሁንም  ይህን ተግባሩን አጠናክሮ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነት፣ የነፃነት እንዲሁም የንብረት መብት ሁኔታዎችን በተመለከተ
 በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ፤ ሀሮ፣ ባጊን እና ኪረሙ ቀበሌዎች ከመስከረም ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት በሸኔ ታጣቂዎች በነዋሪዎች ላይ ጥቃት ይፈፀም እንደነበር፣ መስከረም 26/2014 ዓ.ም  በአካባቢው የነበረው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በግዳጅ ምክንያት ከአካባቢው በመሄዱ፤ ከመስከረም 30/2014 ዓ.ም ጀምሮ
ባሉት ተከታታይ ቀናት የሸኔ ታጣቂዎች በሀሮ ቀበሌ ተኩስ በመክፈት የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ሰዎችን  እንደገደሉ፣ የአካል ጉዳት እንዳደረሱ እና ንብረት እንዳወደሙ መረጃዎች ለኢሰመጉ ደርሰውታል፡፡
 ይህ መግለጫ  አስከሚወጣበት ቀን ድረስ ታጣቂዎቹ በአካባቢው በመኖራቸው የሟቾችን አስክሬን ለማንሳት እና የአካል ጉዳት  የደረሰባቸውን ሰዎች ወደ ህክምና ለመውሰድ አለመቻሉን፣ ሴቶች እና ሕፃናት አሁንም በጫካ ውስጥ እንዳሉ እና
ለጥቃት እንደተጋለጡ እንዲሁም ነዋሪዎች በምግብ እጦት ላይ መሆናቸውን ኢሰመጉ ካሰባሰባቸው መረጃዎች  ለመረዳት ተችሏል፡፡
 በተጨማሪም ለግዳጅ ሄዶ የነበረው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በ2/2/2014 ዓ.ም ወደ ሀሮ ቀበሌ ተመልሶ የነበረ ቢሆንም፤ አመሻሹን ተመልሶ መውጣቱን፣ በዚህም የሸኔ ታጣቂዎች በአካባቢው በብዛት እንዳሉ እና ነዋሪዎች በከፍተኛ የደህንነት
ስጋት ውስጥ መሆናቸውን እንዲሁም ይህ መግለጫ እስከሚወጣበት ቀን ድረስ በአካባቢው የተኩስ ድምፅ እንደነበረ  ለኢሰመጉ የሚደርሱት መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
Filed in: Amharic