አበበ ገላው
*…. የቀድሞው የባህር ሀይል የአድሚራል እስክንድር ደስታ ልዩ አማካሪ ነበሩ።
*…. በመቀጠልም በማስታወቅያ ሚኒስቴር በሬድዮ መምሪያ ሀላፊነት በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በዋና አዘጋጅነት ሰርተዋል።
*…. የአሩሲ ገጠር ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ። በመተሀራ ስኩዋር ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው አገራቸውን ህዝባቸውን አገልግለዋል።
ዛሬ ማምሻውን የቀድሞው የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ከፋለ ማሞ በስደት ይኖሩበት በነበረው አምስተርዳም፣ ሆላንድ ማረፍ ከቤተሰቦቻቸው የሰማሁት በጥልቅ ሃዘን ነው። ጋዜጠኛ ክፍሌ ሙላትን ተክተው የኢነጋማ ፕሬዚዳንት የነብሩት አቶ ከፋለ በዘመነ ህወሃት በእስርና ሰቆቃ ፍዳና መከራ ያስመረራቸውን ጋዜጠኞች በአለም ቀፍ ደረጃ በመወከልና ልሳን በመሆን የሚደርሰውን ግፍና ሰቆቃ በማሳወቅ ቁልፍ ሚና የተጫወቱ ብርቱ ሰው ነበሩ።
እኤአ በ1997/8 ከአቶ ከፋለ ጋር በቅርበት የመስራት እድል ገጥሞኝ ነበር። እርሳቸው የኢነጋማ ፕሬዚዳንት፣ ሙሉጌታ ሉሌ ምክትል ፕሬዚዳንት እኔ የማህበሩ ጸሃፊ ነበርን። አቶ ከፋለ እንደ ልጃቸው ነበር የሚያበረታቱኝ። ደጋግመው ጋዜጠኝነት ጥሪዬ (calling) እንደሆነና ምንም ፈታኝ ቢሆንም እንድገፋበት ያበረታቱኝ ነበር። ምክራቸውንም በቸልታ ሳላልፍ ለመተግበር ሞክሪያለሁ። ለዚሁም የጋሽ ከፋለ ምክርና ማበረታታት ጉልህ ሚና ነበረው ማለት እችላለሁ።
በነበረው አስቸጋሪ ሁኔታና ተደጋጋሚ እስርና ዛቻ ምክንያት ሙሉጌታ ሉሌም እርሳቸውም ስደትን የግድ ተቀብለው ሲሰደዱ እርግጠኛ የነበሩት ነገር ለውጥ አይቀሬ መሆኑን ነበር። ህወሃት ከማዕከላዊ መንግስት ተወግዶ ለውጡን ከእነ ፈተናው አይተው ማለፋቸው ትልቅ ነገር ነው።
ጋሽ ከፋለ ከኢነጋማ በፊት በተለያዩ ከፍተኛ ሃላፊነት አገራቸውን በቅንነት ያገለገሉ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነበሩ። ቸሩ ፈጣሪ ነፍሳቸውን በቀኙ ያኑርልን። ለመላ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ከልብ መጽናናትን እመኛለሁ።
_
የአቶ ከፋለ ማሞ አጭር የህይወት ታሪክ [ከቤተሰቦቻቸው]
አቶ ከፋለ ማሞ አለሜ በሀምሌ 16,1930 አም በሸዋ ክፍለ ሀገር በሰላሌ አውራጃ ከአባታቸው ማሞ አለሜ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ደስታ በጋሻው ተወለዱ። ለትምህርት እድሜያቸው ሲደርስ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ በአምሀደ ደስታ ትምህርት ቤት ከዛም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በታዋቂው በጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተማሩ። ከዛም ሁለት ዲግሪዎችን በአለም ላይ ታዋቂ በሆኑት በዩኒቨርስቲ ኦፍ ለንደን እንግሊዝ አገር እና ዩኒቨርስቲ ኦፍ ዊስኮንሲን ማዲሰን አሜሪካ በጥሩ ውጤት የማስተርስ ዲግሪዎችን ይዘዋል።
ተመርቀውም ወደ አገራቸው ተመልሰው የተለያዩ መስሪያ ቤቶችን አገልግለዋል። በዋነኛነት የቀድሞው የባህር ሀይል የአድሚራል እስክንድር ደስታ ልዩ አማካሪ ነበሩ። በመቀጠልም በማስታወቅያ ሚኒስቴር በሬድዮ መምሪያ ሀላፊነት በተለያዩ ጋዜጦች ላይ በዋና አዘጋጅነት የሰሩ ሲሆን የመጀመርያውን የጋዜጠኞች ማህበር መስራችም መሪም ሆነው ከእነ አሳምነው ገብረወልድ እና ማእረጉ በዛብህ ጋር አገልግለዋል። ከዛም በመቀጠል የአሩሲ ገጠር ልማት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ። በመተሀራ ስኩዋር ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ።
የተለያዩ ፋብሪካዎች ስራስኪያጅ በመሆንና እንዲሁም በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ሆነው ሰርተዋል። በዘመነ ኢሀደግ ደሞ ነጻ ጋዜጣ ላይ የሩህ መጽሄት ዋና አዘጋጅ ሆነው ሰርተዋል። ከሁሉም በላይ መንግስት ጋዜጠኞችን እያዋከበ ሲያስቸግር በድጋሚ የነጻ ጋዜጠኞች መሀበር መስርተው ከነ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ ጋር መርተዋል። በዛም ከመንግስት ብዙ ችግር ሲገጥማቸው ጋዜጠኛ ክፍሌ ሙላትን ተክተው ወደ አውሮፓ ተሰደው በሆላንድ ቀሪ ዘመናቸውን አገራቸውን እያገለገሉ ኖረዋል። አቶ ከፋለ ዛሬ ቢያልፉም በስጋ የአንዲት ሴት ልጅ አባትና የሁለት ልጅ ልጆች አያት ሲሆኑ። ነገር ግን ያለምንም ማጋነን ብዙ የመንፈስ ልጆችን ወልደዋል። ብዙ ወጣት ጋዜጠኞችን እና ፖለቲከኞችን ጠጋ ብለው በማማከር በመምከር ጥሩ ትውልድ አፍርተዋል። ከማንም እና ከምንም በላይ አገራቸውን ይወዱ ነበር ይህንንም በታማኝነት በማገልገል አሳይተዋል። መልካም እረፍት እና ለቤተሰብ መጽናናትን እንመኛለን። የሚወዱዋት አገራቸውን ኢትዬጽያን እግዚአብሔር ይባርክ!