>
5:26 pm - Tuesday September 17, 2154

ሰላሙን የተነጠቀ ሕዝብ አምራች አይሆንም.. !!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ሰላሙን የተነጠቀ ሕዝብ አምራች አይሆንም.. !!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ይድረስ ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ፤ አዎ እርሶ እንዳሉት ኢትዮጵያ አምራች እንጂ ተዋጊ ሕዝብ አያስፈልጋትም ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው፤ ሕዝብ ጦርነት ውስጥ የገባው እርሶን ጨምሮ መግባባት ያቃታችሁ ፖለቲከኞች የጀመራችሁት ንቁሪያ እያደር ወደ ጡጫና እርግጫ በማምራቱ እንጂ። ይህን ሀቅ እንዲህ በቶሎ ይዘነጉታል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ዛሬ አገሪቱ ለገጠማት ችግር ከአፈጣጠሩ  ጀምሮ በሸር እና በክፋት የተወጠረው ወያኔ የአንበሳውን ድርሻ ቢወስድም እርሶ እና የሚመሩት ድርጅትም ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ በሙሉ ልብ ልነግርዎ እወዳለሁ።
ወያኔ ጦርነቱን ከመጫር አንስቶ ብዙ አስከፊ ወንጀሎችን በመፈጸም፣ አገር በማተራመስ እና በማሸበር ቢጠየቅም፤ የእርሶ እጅግ የተዳከመ የፖለቲካ ምሪት እና በአገሪቱ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር አቅም ወይም ፍላጎት ማጣት አገሪቱ ወደዚህ አቅጣጫ እንድታመራ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።
በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ በዚህ ደረጃ አገሪቱ ተዳክማ እና በብዞ አደጋዎች ተከባ አጣብቂኝ ውስጥ የገባችበት ጊዜ የለም። ዳር ድንበሯ ተናግቶ፣ ሚሊዮኖች በእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ተፈናቅለው፣ መቶሺዎች የርሃብ አደጋ አንጃቦባቸው፣ ግማሽ የሚሆነው የአገሪቱ ክፍል በሰላም እጦት እየታመሰ፣ ዜጎች ለዘመናት ያፈሩት ንብረት በታጠቁ ወሮበሎች እየተዘረፈ፣ የገበሬዎች ማሳ በእሳት እየወደመ፣ በመቶዎች በአንድ ሌሊት ታርደው የሚያድሩበት፣ ዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች የለት ተዕለት ዜና የሆነበት፣ ለብዙ ዜጎች በሰላም ውሎ ማደር ብርቅ የሆነበት እንዲህ ያለ ክፉ ጊዜ አጋጥሞን አያውቅም።
እርሶ በአይነቱ ለየት ያለ እና በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ የፈሰሰበተት በዓለ ሲመትዎን እንግዶች ሰብስበው ሲያከብሩ፤ የአገሪቱ የሰሜን ክፍል፤ ትግራይ፣ ከፊል ወሎ፣ ከፊል ጎንደር እና ከፊል አፋር በከፋ ጦርነት ውስጥ እየታመሱ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችም ለርሃብ ተጋልጠው የድረሱልን ጥሪ ያሰሙ ነበር። ከቀያቸው
የተፈናቀሉ መቶ ሺዎች መጠለያ እና ህክምና አጥተው የመንግስት ያለህ፣ የወገን ያለህ እያሉ ይጣሩ ነበር። የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ እና የእርሶን የመስቀል አደባባይ ትዕይንት ሳይ ወደ አይምሮዮ የመጣው የደርግ 10ኛ የአብዮት በዓል እና የ77ቱን የከፋ ድርቅ ግጥምጥሞሽ ነበር።
በእርሶ በዓለ ሲመት መስቀል አደባባይ የታየችው ኩሩዋና ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ፤ ለአለም ሊያሳዩት የጣሩት ገጽታዋ ከአዲስ አበባ ብዙም እርቀት ሳይጓዙ ደብዛው እንደማይገኝ ልቦናዎ ያውቀዋል። ኢትዮጵያ ክፉኛ ታማለች። ኢትዮጵያ ሰላም አይደለችም። ኢትዮጵያ ተርባለች። ኢትዮጵያ ዜጎቿ በየቀኑ የሚታረዱባት አገር ሆናለች። ኢትዮጵያ ሴቶች በገፍ የሚደፈሩባት፣ ሕጻናት የጥቃት ሰለባዎች የሆኑባት፣ ዜጎች በዘራቸው የሚሳደዱባት ምድር ሁናለች።  ግን አለም ሁሉ ፊቱን ያዞረብን ወቅት ላይ ስላለን በአልሞት ባይ ተጋዳይነት መንፈስ መግደርደሩ አይከፋም በሚል ገበናችንን ይዘን መልካም የሥራ ዘመን ተመኘንልዎ። የእርሶም አስተዳደር ከድክመቱ አገግሞ አገሪቱን እና ዜጎችን ከጥቃት ይታደጋል፣ አገርም ትረጋጋ ይሆናል ብለን።
ይሁንና እየሆነ ያለው የሰለለው ተስፋችንን የሚያለመልም ሳይሆን ስጋታችንን የሚያደነድን የሰቆቃ ውርጅብኝ እንጂ። አገር ወዳዱ የአፋር ሕዝብ በወያኔ ታጣቂዎች ስቃዮን እየበላ ነው። ለመከላከያ ደጀን የሆነው የወሎ ሕዝብ መከራ ውስጥ ነው። ወያኔ በምርኮ የያዘችው የትግራይ ሕዝብ ተገልጾ የማያልቅ መከራ እየወረደበት ነው።
ይባስ ብሎ በዚህ ሳምንት  በወለጋ ጊዳ ኪራሞ በጭካኔ እና ጥላቻ ናላቸው የዞረ የኦነግ-ሽኔ ታጣቂዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ሲጨፈጭፉ እንደ መንግስት ሀዘንዎን አለመግለጽኦ እና ተጎጂዎችን አለማጽናናትዎ፤ ለወትሮም አድርገውት ስለማያውቁ ባይገርመኝም፤ የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ በአስተዳደርዎ በኩል የሚታየው ዳተኝነት ዛሬም በዚህ ደረጃ መቀጠሉ ግን ነገን አጥብቄ ለአገሬ እንድፈራ አድርጎኛል። የአንድ ዜጋ ህይወት በእርሶ አስተዳደር ዘንድ ዋጋው ስንት ይሆን?
አምራች ሕዝብ ለመፍጠር የነጠቃችሁትን ሰላሙን መልሱለት።
Filed in: Amharic