>

ጥያቄው መቼና ምን ያህል የትግራይ ወጣት ካስጨረሱ በኋላ ነው ?  የሚለው ነው ....!!! (ግርማ ካሳ)

ጥያቄው መቼና ምን ያህል የትግራይ ወጣት ካስጨረሱ በኋላ ነው ?  የሚለው ነው ….!!!
ግርማ ካሳ

*…. በድርድር በዉይይት የማምን ሰው ነኝ፡፡ ችግርን በድርድር መፍታት ትልቅነት ነው፡፡ ሆኖም ለመደራደር ፍቃደኝነት መኖር አለበት፡፡ በአንድ  እጅ ማጨብጨብ አይቻልምና፡፡ 
ወያኔዎች ወረው ከያዙት ከአማራና አፋር ክልል ወጥተው ፣ ያሉ የፖለቲካ ልዩነቶችም ካሉ በድርድርና በንግግር እንዲፈቱ ከሁለት ወራት በላይ ግፊት ሳደርግ ነበር፡፡ ደጋግመን፣  ምን አልባት በመከላከያ ውስጥ ባሉ፣  የድብቅ ኦነጋዊ አሽከሮቻቸው ሳቦታጅና ባላቸው የመሳሪያ የበላይነት (እድሜ ለነ ዶር አብይ አህመድና አቶ ደመቀ መኮንን)  አልፎ አልፎ በለስ ሊቀናቸው ይችል ይሆናል እንጂ ፣ የማታ ማታ ሕዝብን ማሸነፍ እንደማይችሉ ነግረናቸዋል፡፡ ለማታሸንፉት የትግራይን ወጣት አታስጨርሱ ብለናቸዋል፡፡ እነርሱ ግን አልሰሙም፡፡
በ24 ሰዓት ለሚባረሩት፣ ትላንትና ጭፍራን ያዝን፣ ውጫሌን ያዝን ብለው ጨረቃ ላይ የወጡ ይመስል ሲፈነጥዙ ነበር፡፡ አዘንኩ፡፡ እኔ የምፈነጥዘው ሰላም ሲመጣ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ፣ የወሎ ሕዝብ፣ የጎንደር ሕዝብ ፣ የአፋር ሕዝብ፣ የወለጋ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ ሲገባ ነው፡፡ የትግራይ ወጣት እየታፈሰ ወደ ጦር ሜዳ ሳይሆን ወደ ትምህርት ቤቶች መሄድ ሲጀምር ነው፡፡ የተፈናቀሉ ወደ ቅያቸው ሲመለሱ ነው፡፡
ውጊያ ላይ ከተማ መያዝ፣ ከተማ ማስለቀቅ ያለ ነገር ነው፡፡ ደብረ ደቢጥን ያዙ፣ እንዲለቁ ተደረገ፣ እንደገና ያዙ እንደገና ለቀቁ፡ ጋሸናን ያዙ፣ እንዲለቁ ተደረገ፣ እንደገና መልሰው ጋሸናን ያዙ፣ አሁን ደግሞ እነርሱ ተከበዋል፡፡ ውጫሌን ያዙ፣ ጭፍራ ደጃፍ ደረሱ፣ ለ24 ሰዓታት “ሆሆሆ” አሉ፡፡ አሁን ደግሞ ከውጫሌም ከጭፍራም ተባረሩ፡፡
ወያኔዎች ከሁሉም የአማራ ክልል(ጠለምትንና ራያን ጨምሮ) ይወገዳሉ ባይ ነኝ፡፡ ጥያቄው መቼና ምን ያህል የትግራይ ወጣት ካስጨረሱ በኋላ ነው ?  የሚለው ነው፡፡ አራት ኪሎ ባለው፣  አቋሙ የማይታወቀው፣ አገር የመመራት ብቃት በሌለው፣ በሚዋሸውና በሚያጭበረብረው የብልጽግና  የፖለቲካ አመራር ተማምኜ አይደለም፡፡ ነገር ግን አንደኛ በአማራና በአፋር ማህበረሰብ አባላት፣ በአማራና አፋር  ሚሊሾያዎች፣ ፋኖዎችና ልዩ ኃይሎች፣  በሃቀኛ ለሕዝብ የቆሙ የመከላከያ አዛዦች በሚመሩት ክፍለ ጦሮች ውስጥ ባሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተማምኜ ነው፡፡
አንድ ነገር አንርሳ፣ ሕወሃቶች ያዝን ያሏቸው በርካታ ቦታዎችን የያዙት፣ በዋናነት ከሶስት ምክንያቶች በአንዱ ወይም በሁለቱ፣ ወይም በሶስቱ ነው፡፡ 1ኛ በሳቦታጅ(በሴራ) መከላከያ እንዲለቅና እንዲያፈገፍግ በማድረግ፣ 2ኛ በጣም ከፍተኛ የታጣቁ፣  ብዛት ያላቸው፣ የታጣቂ ማዕበል በማሰማራት፣ 3ኛ የዶር አብይ አመራር ጥሎላቸው ስለሄደ፣ ባገኙትና ባላቸው ከፍተኛ የከባድ መሳሪያ የበላይነት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ እስከተወሰደ ደረጃ ነው ሊያስኬዳቸው የሚችለው፡፡ የቻለው፡፡
ለትግራይ ማሀብረሰብ አባላት ይሄን እላለሁ፡፡ ልጆቻችሁ እየረገፉ ነው፡፡ ስጋቸው የአሞራና የጅብ እራት እየሆነ ነው፡፡ አዲስ አበባ እንገባለን  አሏችሁ፡፡  ገቡ ???? ባህር ዳር፣ ጎንደር እንገባለን አሏችሁ ገቡ ? የሱዳንን ኮሪዶር እስናከፍታለን አሏችሁ፡፡ አስከፈቱ ? ከ24 ጊዜ በላይ በወልቃይት ጦርነት ከፍተው እንደተሸነፉ ነግረዋቹሃል ? ይኸው አራት ወር ሊሆናቸው ነው፣ አማራና አፋር ክልል ወረው ከያዙ፡፡ ምን አመጡላችሁ ?  ለነዚህ ጥያቄዎች እዚህ ምላሽ እንድትስጠኝ አይደለም፡፡ ለብሽሽቅ ብዬም አይደለም፡፡ ለራሳችሁ ፣ እስቲ ቆም ብላችሁ ለጠየኳቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሞክሩ፡፡ከራሳችሁ ጋር ተነጋገሩ፡፡
Filed in: Amharic