በለጠ ጌትነት
“የመሪዎች ሴራ በኢትዮጵያ” !!!
በአስቴር ቀለብ ስዩም የህሊና እስረኛ/ቃሊቲ/
የነፃነት ታጋይ አስቴር ስዩም አዩኝ አላዩኝ እያለች በጠባቧ እስር ቤት ሁና ይህን የደከመ ስርዓት መሞገቷን ቀጥላለች። ህመሟ፣ የልጆችን ናፍቆትና የአሳሪዎቿን ጫና ተቋቁማ ያዘጋጀችው “የመሪዎች ሴራ በኢትዮጵያ” የሚል መፅሐፍ በገቢያ ላይ ስለዋለ እንድታነቡት እየጋበዝኩ ለግንዛቤ ያህል የመፅሐፉን መግቢያ እንሚከተለው ላካፍላችሁ እወዳለሁ፡፡ (በለጠ ጌትነት 0918777673 ወይም ዘላለም መፅሐፍ መደበር 0912400094 ታገኙታላችሁ)
“መግቢያ”
ይህ መጽሐፍ በሀገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት ዙሪያ ያጠነጥናል። ኢትየጵያ በታሪካዊ ጠላቶችዋ አዝማችነትና በእናት ጡት ነካሽ ባንዳዎች አማካኝነት ጦርነት ተከፍቶባታል። በተለይም ጀግናውና አይበገሬው፣ እንግዳ ተቀባዩና ሩህሩሁ፣ ፍትሀዊና ሚዛን የማያጓድለው የአማራ ህዝብ የአለም አቀፉ የጥቃት ኢላማ ማዕከል ሆኖ እነሆ በመኖርና ባለመኖር አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ቁምስቅሉን በማየት ላይ ይገኛል። በአራቱም ማዕዘን በህልውና ፍልሚያ ላይ ነን። ጥቃቱም መጠነ-ሰፊ ነው።
በርካታ ቅን ሰዎች የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግሥት ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የመምራት ታሪካዊ ሀላፊነት እንደወደቀበት አድርገው ያስባሉ። ይሁን እንጂ ሀገሪቱን እየገዛ ያለው ገዢ ፓርቲ (ብልጽግና) በአመለካከትም ሆነ በተግባር ከሕወሓት-ኢህአዴግ አብራክ የተገኘ መሆኑን ዘንግተውታል። በተፈጥሮ ህግ ደግሞ ከእባብ እንቁላል ርግብ አይፈለፈልም።
በፖለቲካውም ቢሆን ከእዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም። ኢህአዴግ ሌላ ካባ (የብልጽግና ካባ) ደርቦ በመንበረ-ሥልጣኑ ዙፋን ላይ ተቀምጦ እንመለከተዋለን።
የአማራ ክልሉ ገዥ (ብአዴን) ትናንት የህወሐት ተላላኪና ጥቅም አስጠባቂ ነበረ፣ ዛሬ ደግሞ “እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው” በሚል ብሒል የኦህዴድ ተላላኪ ከመሆኑም በአሻገር ለኦህዴድ የበላይነት ተግቶ ይሰራል። ኦህዴድ በመፃኢዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ስመ-ገናና እና ልዕለ-ሀያል ሆኖ የመቀጠል ቀቢፀ ፍላጎት አለው። ይህንን ፍላጎቱን ለማሳካተም የአማራን ህዝብ በሆነው ሁሉ ማዳከምን አይነተኛ መርህ አድርጎ ሲንቀሳቀስ እያስተዋልነው ነው። ይህ መጽሐፍ ይህን ርእሰ ጉዳይ በስፋት ይፈትሻል። በአንድ ጠጠር ሁለት ወፍ ለመግደል የሚካሄደውንም የተቀነባበረና የተጠና ፖለቲካዊ ሴራም ያጋልጣል።
ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የብልጽግና ካቢኔ ከወላጅ አባቱ ሕወሓት ኢህአዴግ በተማረው መሠረት የሚቃወሙትን ሁሉ እየሰበሰበ ማሰር፣ ማንገላታትና ማዋከብን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል። እኔም የእዚሁ ጥቃት ሰለባ መሆኔም ይታወቃል።
“ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ምን አገባኝ ማለት ሲጀምር ያቺ አገር አበቃላት” ይለናል ጆን ሩስ። እውነት ነው፣ ባለሥልጣናት የምዕራባውያኑን ሴራ እየተቀበሉ እንደወረደ እንተግብረው ሲሉ በዝምታ ለመመልከት አንችልም።
እኔ የብልፅግናን ድብቅ ተልዕኮ ፊት ለፊት በመቃወሜ ከህፃናት ልጆቼ፣ ከምወደው ባለቤቴና ከምወዳቸው ወዳጆቼ ተለይቼ እድሜዬን በመከራና እንግልት እንዳሳልፍ መደረጌ አልጎዳኝም ለማለት አልደፍርም። ይሁን እንጂ የጠላቶቼ ዱላ የፈለገውን ያህል እስከ አጥንቶቼ ዘልቆ ቢሰማኝም፣ ነፍሴ ከሚደርስባት ስቃይ የተነሳ በውስጤ ፈስሳ ልታልቅ ብትደረስም ያመንኩበትን ከማድረግ የሚያግደኝ አንዳችም ምድራዊ ሀይል እንደሌለ እረዳለሁ። ይህ ሁሉ የበደል ናዳ የሚወርድብኝ ለሀገሬና ለህዝቤ ደህንነት በመሆኑ ይበልጥ ያጀግነኛል እንጂ ተስፋ አያስቆርጠኝም።
በአጠቃላይ ይህን መጽሀፍ ስታነቡ በእዚህች ታሪካዊና እድሜ-ጠገብ ሀገር ውስጥ እነማን ምን እያደረጉ እንዳሉ ትረዳላችሁ ብዬ አስባለሁ። ውድ ወገኖቼ! በማንኛውም ጊዜም ሆነ ስፍራ ለክፉዎችና መሠሪዎች አታጎብድዱ፣ ክፉውን ተቃወሙ፣ ለድምፅ አልባዎች ድምፅ ሁኑ፣ በፍቅር ተመላለሱ፣ በእውነትና በፍትሀዊነት ኑሩ፣ እናንተ በፈጣሪ አምላክ ጥላ ስር የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ናችሁ፣ ምንም በእናንተ ላይ እንዲሰለጥን ራሳችሁን የሌላው ባርያ ለማድረግ አትፍቀዱ።
የዚህ መጽሐፍ አላማም ሆነ ተልዕኮ ይኸው ነው። መልካም ንባብ!!!
“በግፈኞች እየተገረፍን፤ በእግዚአብሔር ሐይል እናሸንፋለን!!”
ቀለብ ስዩም
የህሊና እስረኛ/ቃሊቲ/
ጥቅምት/2014 ዓ/ም