ፍትሕ መዓዛ አጥቷል…!!!
ጲጥሮስ አሸናፊ
*…. የእድሜ ልክ እስረኛ ወንጀለኛን በእስክድር ነጋ ላይ መስክረህ ነፃ ሰው ትሆናነህ ብሎ የሚያዘጋጅ አቃቤ ህግ ላይ መድረሳችን እውነትም ፍትህ በአዲስ መአዛ ለመታጠኗ አይነተኛ ማሳያ ነው !
ሰው ከፖለቲካ ሹመት በፊት በነበረበት አይገኝም ይባላል። ምንም ሁሉንም ፖለቲካዊ ተሿሚ በጅምላ መውቀጡ አግባብ ባይሆንም ብዙ ተጠብቀው ከሚዛናቸው ቀለው የተገኙትን መውቀሱ ግን አይከፋም።
እንደ መዓዛ አሸናፊ አይነት የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ግለሰቦች ለሹመት ሲታጩ ስንቦርቅ የነበረው ቢያስ ሙያቸውን አክብረው ያስከብራሉ፣ ለሕሊናቸው ይገዛሉ፣ የሾሟቸውን ለማስደሰት ብለው ሙሉ ታሪካቸውን አያበላሹም፣ የፖለቲከኞች ዱላና ቆመጥ አይሆኑም፣ ሰብዐዊነት ያስቀድማሉ፣ ሕግን አክብረው ያስከብራሉ ወዘተ በሚል ቅን አስተሳሰብ ነበር። ከፖለቲካ ሹመኞች መካከል በተለየ ተስፋ ካደረኩባቸው መካከል አንዷ መዓዛ ነበረች። ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም “ፍትሕ መዓዛ ሊኖረው ነው” በሚል የመዓዛን ሹመት ሲቀኘው አስታውሳለሁ። አሁን ያ የታለመው የታሰበው የፍትሕ መዓዛ ጠፍቷል። ፍትሕና ፍርድ ቤቶች የዕቃ ዕቃ መጫዎቻዎች ሆነዋል። የዳኞች ውሳኔን የሚያስከብር የሕግ አግባብ ያለው ተቋምም እንደሌለ በገሃድ እየታየ ነው። የሴቶች መብት ተከራካሪ የነበረችው መዓዛን ጋዜጠኞች ለቃለምልልስ ሲጠይቋት ” የደንቢደሎ ታፋኝ ሴቶችን ጉዳይ የማታነሱብኝ ከሆነ” የሚል ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ከጀመረች ሰነባብታለች። ምርጫን ለማስረዘምና ሿሚዎቿን ለማስደሰት ቀደም ብላ የምታውቃቸውን የሕግ ባለሙያዎች “ምርጫው ይራዘም ዘንድ ተባበሩኝ” አይነት ሃገራዊ ሳይሆን ግላዊ ልመና ለሷና ለሹመቷ ሲሉ የድጋፍ ጽሑፎችን እንዲያቀርቡ ስትጎተጉትና ስትደልል የታዘቧት በርካቶች ነበሩ። መንግሥት ካለምንም ሕጋዊ ውይይት የፈለገውን መወሰንና ማስወሰን የሚችልበት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ፓርላማ እያለው ለሚዲያ ፍጆታ በሚል ባለሙያዎችን ካለፍላጎታቸው ማነካካት የሚጠበቅባት አልነበረም።
ለማንኛውም በኢትዮጵያ ፍትሕና ፍርድ ቤቶች ታሪክ ታስመዘግባለች ያልናት መዓዛ ባልተጠበቀ መልኩ የቀደሙ ቆሻሻና አሳፋሪ የፍትሕ መጓደልን፣ አድሏዊነትንና ፖለቲካዊ ውሳኔ አስፈፃሚነትን በነበረበት በማስቀጠል ተግባር ላይ ፊት አውራሪ ሆና ማየት በተለይ አስቀድሞ ለሚያውቃት ለማመን የሚከብድ ነው።
ፍትህ በግሩም መአዛ የታወደች መስሎን በሹመታቸው ዋዜማ ይህን ብለን ነበር!
ዜና ሹመት
ተወዳጇና የሴቶች መብት ተሟጋቿ መዓዛ አሸናፊ በነገው ዕለት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ይሾማሉ።
መዓዛ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ፤ ቀደም ብሎም በከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆናቸው የሚታወቁ ሲሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም የመጀመሪያው የሴቶች ባንክ የሆነው የእናት ባንክ ፕሬዚዳንት ነበሩ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ የተወለዱት መዓዛ በኢትዮጵያ የሴቶችን መብት ለማስከበር ከፍተኛ ትግል ካደረጉት ሁሉ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።
መዓዛ አሸናፊ በተባበሩት መንግሥታት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንም በሃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ሽልማቶች የተበረከተላቸውና ለታላቁ የኖቤል ሽልማትም ታጭተው የነበሩ ታላቅ ኢትዮጵያዊት ናቸው።
ወይዘሮ መዓዛ በነገው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የሚሾሙት እስካሁን በስልጣን ላይ የቆዩትን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ዳኜ መላኩን በመተካት ይሆናል። ከሰኔ 2008 ዓ/ም ጀምሮ በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት አቶ ዳኜ በጡረታ አንደሚሸኙም ታውቋል።
መልካም የስራ ዘመን ለክብርት ዳኛ መዓዛ አሸናፊ !
Meaza Ashenafi is to be sworn in as the president of the EFDR Supreme Court.
The ex president of Enat Bank and founder and executive director of Ethiopian Women Lawyers Association will receive the baton from Dagne Melaku in the House of People’s Representative tomorrow morning.
ዛሬ ዛሬማ ፍትሕ መዓዛዋን አጥታለች!