>

በእስክንድር ውስጥ ሆኜ ኢትዮጲያን ሳያት-ሰው አጣሁባት!!! (ወንድወሰን ተክሉ)

በእስክንድር ውስጥ ሆኜ ኢትዮጲያን ሳያት-ሰው አጣሁባት!!!

ወንድወሰን ተክሉ

በሰው አልባ ሀገር ሰው ሆኖ የመገኘት እያስከፈለ ያለ ዋጋ
ሐሙስ ጥቅምት 21ቀን 2021 እስክንድር ነጋ በግፍ ታስሮ በሚሰቃይበት ቅሊንጦ እስር ቤት ውስጥ መደብደቡን የሰማሁበት መጥፎ ቀን ሆነ።  አንድ በህግ ጥላ ስር ውስጥ ያለ ሰው ለምን እና እንዴት ይደበደባል -እሺ ድብደባው ቢፈጸምም እስር ቤት ውስጥ ድብድብ ውሃ የመጠጣት ያህል በሆነበት ስፍራ ነውና ምንስ አዲስ ነገር አለውና ነው የሚያስደንቀው የሚሉ ሰው ያልሆኑ ሰዎች ሲያስተጋቡትና ብሎም ድብደባው በእስር ቤት ውስጥ ከምግባረ ብልሹ ታራሚ የሚፈጠር ተራ ክስተት ነውም እያስሉ ሲያናፍሱም እየሰማን ነው።
በተፈጸመበት ድብደባ ፍርድ ቤት መቅረብ ያልቻለው እስክንድር ዛሬ በተደረገለት ህክምና በእግሩ ላይ የአውራ ጣቱ ስብራት የደረሰበት በመሆኑ እግሩ በጄሶ ተጠቅልሎ ለቀጣይ ስድስት ሳምንታት የማይነቀሳቀስ ሰው ሆናል።
እስክንድር በሚሰቃይበት ቅሊንጦ እስር ቤት ውስጥ የተደበደበው በእለተ ረቡእ ጥቅምት 20ቀን 2021 ከቃልቲ እስር ቤት ወደ ቅሊንጦ  እስር ቤት እንዲዛወሩ በተደረገ ሁለት የህግ ታራሚዎች በኩል ሲሆን በእለቱ እስክንድር እስከ ቀኑ 12ሰዓት ፍርድ ቤት ሲከራከር የዋለበት እለት ነው የደብዳቢዎቹ ዝውውር የተፈጸመው። ደብዳቢዎቹ በቃልቲ እስር ቤት ቆይታው በእስክንድር ላይ አደጋ ለመጣል ተደጋጋሚ የመተናኮል ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩ መሆናቸውና በእለቱ እስክንድር በሌለበት እነዚህን ልዩ ተልእኮ የተሰጣቸውን ደብዳቢዎች ከቃልቲ አውጥቶ ቅሊንጦ እንዲዛወሩ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በቅሊንጦ ውስጥ ካሉት በአስሮች ከሚቆጠሩ እስር ቤቶች ውስጥ ለይተውና መርጠው እስክንድር ባለበት ክፍል ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉ መሆናቸውን ማየት በራሱ ድብደባ ተብሎ የተገለጸውን የግድያ ሙከራን ያዘዘውና ያስፈጸመው አቢይ አህመድ አሊ መሆኑን ነገሮችን በጥልቀት ማየት ለማይችለውና ለማይፈልገው ማንኛውም ተራ ተመልካች ቁልጭ አድርጎ  ማሳየት የሚችል መንግስታዊ ጥቃት ነው።
እንደ እኔ እምነትና አረዳድ እስክንድር ላይ የተፈጸመው የግድያ ጥቃት እንጂ ተራ ድብደባ አይደለም። ግድያውን ለመፈጸም እየተጋጋጡ ያሉት «ባለአደራ ብለህ ከመጣህ ግልጽ ጦርነት እንከፍታለን » ያለው ፋሺስቱ አቢይ አህመድ «ባለአደራ ገለመሌ እኔ አላውቅም አቢይ አህመድ ታከለ ኡማ ለማ መገርሳ የማምንባቸው አሻጋሪዎች መሆናቸውን ታከሉ ኡማም የአዲስ አበባ ከንቲባ መሆኑን ነው እኔ የማውቀው » ያለው ብርሃኑ ነጋና እና እሱ የሚመራው ኢዜማ የተባለ ፓርቲ እንደ ተቌም ደግሞ በመዓዛ አሸናፊ የሚመራው ጠቅላይ ፍርድ ቤት እራሷ መዓዛ አሸናፊ ፣ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ኢሳት ሚዲያ፣በተመስገን ጥሩነህ የሚመራው የመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት፣የፌዴራሉ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርና የአቢይ ባሪያ አሽከር የሆነው ብአዴን እና ዛሬ ብልጽግና የተባለው መንግስት ተብዬ ገዳይ ቡድን አገልጋይ የሆኑት ምኒስቴር ተብዬዎች በሙሉ ናቸው ብዬ ነው የምረዳው እንጂ እስክንድር ነጋ ላይ የተፈጸመ ተራ ድብደባ ነው ብዬ ፈጽሞ የማምን አይደለሁም።
እስክንድር የተሰበረውን እግሩን ከታከመ በኋላ ከቃሊቲ ሆኖ ባስተላለፈው መልእክት እስክንድር ከማረሚያ ቤት ሆኖ ባስተላለፈው መልዕክት፣ “በሰሜን ያለውን ጦርነት አስባለሁ። የታሰሩትን አባሎቻችንን አስባለሁ። አጥንታችንን መስበር ይቻላል። ትግላችንን ግን መስበር አይቻልም ” በማለት ለቆመለት አላማ የቱንም ያህል መስዋእትነትን የሚያስከፍል መሆኑን በጽኑ ቢያውቅም ለዚህ ከባድ መስዋእትነትን እያስከፈለ ላለው  ለዓላማ ያለውን እማይናወጥ ጽኑ አቌም ገልጿል።
የእስክንድር ህይወት በከፍተኛ  አደጋ ላይ ማለት ከጀመርን እጅግ ሰንብቷል። የእስክንድርን ህይወት አደጋ ላይ የጣለውና በእነዚህ ሰው ባልሆኑ ሰው ነኝ ባዮች ሁሉ ጥርስ ውስጥ ያስገባው የአዲስ አበባ ጉዳይ መሆኑ ቢታወቅም የእስክንድር ለእውነት፣ለፍትህ፣ለእኩልነትናለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመስረት ላይ ያለው ጽኑ አቌም እና ንጽህናው በሴራ ፖለቲካ ተክነው በንጹሃን ደም እጃቸውን ላጨማለቁ ድኩማን ሰው ነን ባዮች እጅግ እማይፈለግ አደገኛነት ሆኖ ነው የእስክንድር ህይወት አደጋ ላይ ያለ ሊሆን የቻለው።
እጃቸው በደም የተጨማለቀ አሸባሪ ፋሺስቶች  የሀገሪቱን መንበረ ስልጣን በመቆጣጠር ፈላጭ ቆራጭ በሆኑበት ሁኔታ ወደ እስር ቤት የሚያስወረውረው «ወንጀል » የእስክንድር ንጽህና እና በዚህ ንጽህናው ደግሞ ህዝባዊና ሀገራዊ ራእይ የሰነቀ አቌመ ጽኑ ሆኖ መገኘት እጅግ ከባድ ወንጀል ሆኖ ነው እስክንድርን ዋጋ እያስከፈለ ያለው።

 እስክንድር ህይወቱን የሰጠለትስ ሕዝብ የት አለ??

በትናትናው የእስክንድር የፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ ለመታደም በልደታ ፍርድ ቤት የታደመ አዲስ አበቤ የእስክንድርን ወደ ፍርድ ቤት አለመምጣትና ለመምጣትም ያልቻለበትን ምክንያት በተፈጸመበት ጥቃት መሆኑን እንደሰማ ቁጣውንና ተቌውሞውን በማሰማቱ ወንጀለኞቹ ተረኞች በርካታዎቹን  አፍሰው  አጉረዋቸዋል።
በእርግጥ አዲስ አበቤ እስክንድርና ባልደረቦቹ ወደ ፍርድ ቤት በሚመላለሱበት ወቅት በአካል እየሄደ ድጋፉን ቢገልጽም፣ወደ ቃልቲና ቅሊንጦ እስር ቤቶች በመመላለስ መሪዎቹን እየጎበኘ ቢሆንም እስክንድር እየከፈለ ካለው መስዋእትነትና ታግሎ ከሚያታግለው ዓለማው አንጻር አያነጻጸርን ብናየው ግን ወደ ፍርድ ቤትና እስር ቤቶቹ መሄድ ብቻ ይበቃል ተብሎ የማይገለጽ -ምንም አልተደረገም ለማለት በሚያስችል መልኩ ህዝቡ ጀግናውን እያየ ነው ማለት ይቻላል።
ፋሺስታዊው የኦሮሙማ ፖለቲካ ኤሊቶች ስብስብ የሆነው የኦህዴድ/ብልጽግና አዲስ አበባ የኦሮሚያ ብቻ የግል አንጡራ ሀብት ናት ብሎ ለመሰልቀጥ የተነሳ ኋይል ሆኖ ሳለና ይህንን ኋይል ፊት ለፊት ተጋፍጦ አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጲያዊ ናት ብሎ በመነሳት አንዳችም ተወካይና ጠበቃ በጠፋበት ጨለማ ወቅት መጀመሪያ በሲቪክነት የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ለጥቆም ባልደራስ ለእውነተኛ ዶሞክራሲ ፓርቲን በመመስረት ለዘራፊው ታከለ ኡማና ለአለቃው ፋሺስቱ አቢይ አህመድ የጉሮሮ ውስጥ አጥንት ያህል ሆኖ ለተናነቀውና ለታገለው እስክንድርና ባልደረቦቹ አዲስ አበቤውና የተቀረውም ኢትዮጱያዊ ማድረግ ያለበትን በማድረግ መሪውን ለመታደግ ሲጥር አልታየም ወይም እየታየም አይደለም።
አማራው በሰኔ 2019 ውድና ብርቅ የሆኑትን መሪዎቹን ጄ/ል አሳምነው፣ዶ/ር  አምባቸውንና ሁለቱን ባለደረቦቻቸውን በድንገትና በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለውበት ሲያጣ ለምንና እንዴት  መሪዎቼ ይገደሉብኛል ብሎ ብድግ በማለት በስርዓቱ ላይ እማያዳግም እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ጥቃቱን በዝምታ በመቀበሉ ምክንያት ዛሬ ፋሺስቱ አቢይ በአማራው ላይ አራተኛውን ምስለኔ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ የተባለ ታማኝ አገልጋይ በመሾም አጠቃላይ አማራን በሰሜን በትህነግና በደቡብ በራሱ በተስፋፊው የኦሮሚያ ወራሪ ሚሊሺያ አስወርሮ ሰሜን ጎንደርንና ወሎን እያስረከበ ያለንበትን ሁኔታ ለማየት እንደተገደድነው ሁሉ አዲስ አበቤም በሰኔ22ቀን 2020 ላይ በአቢይ አህመድ በተገደለው ሀጫሉ የተባለ ዘፋኝ አሳብቦ እስክንድርንና ባልደረቦቹን ሲያስር ግልብጥ ብሎ በመውጣት ስርዓቱን አስጨንቆ መሪዎቹን መታደግ ሲገባው ዝም በማለቱ አዲስ አበባን እንዲያጣ ከመደረጉም በላይ ምትክ የለሽ ጀግናውንም ለስቃይ ዳርጎት ይገኛል።
በእስክንድር ውስጥ ሆነን ኢትዮጲያን ስንመለከት ይህች ጥንታዊት፣ታሪካዊትና ታላቅ የሆነች ሀገር ዛሬ ላይ ባለው ትውልድ ውስጥ ሰው ሆኖ ያለ ሰው የሌላት ሀገር ሆና ነው የምትታየው። በምእራብ ሰሜን ኢትዮጲያ ግዛቷ በባድ ሱዳን ተወርሮ የተያዘባት፣የሀገሪቷ ቀንደኛና ደመኛ ጠላት ኢሳያስ አፈወርቂ አዛዥና ናዛዥ ሆኖ ኢትዮጲያዊያንን በግፍ የሚጨፈጭፍባት፣ዜጎች በእምነታቸውና በተፈጥሮአዊ ማንነተቻው እየተለዩ የሚጨፈጨፉባትና እነእስክንድርን ጨምሮ በርካታ ንጹኋን በፈጠራ ክስ በግፍ የሚሰቃዩባት ሀገር የሆነቺው ሰው ነኝ የሚል መብቱን ክብሩን ያወቀ ኢትዮጲያዊ ሰው ስለሌለባት ነው እንጂ መብቱንና ክብሩን የሚያውቅ ምሉእ የሆነ ዜጋ ቢኖራት ኖሮ እነዚህን ክስተቶች በጭብጨባና አሊያም በዝምታ አዚም ተለጉሞ የሚያይ አይኖርም ነበር።
እስክንድርንም ሆነ ጄኔራል አሳምነው ጽጌን ከሁሉም እጅግ የተለዩ ባለራእይ ጀግኖች የሚያደርጋቸው ሁለቱም ከማንም በፊት ቀድመው ዛሬ እየሆነ ያለውንና ብሎም ነገም የሚሆነውን ቀድመው አይተው ያስጠነቀቁን መሆናቸው። ጄ/ል አሳምነው ጽጌ ይህ ትውልድ ታሪካዊ ስህተት እንዳይፈጽም ብሎ ባስጠነቀቀበት ድንቅ ታሪካዊና ትንቢታዊ ንግግሩ « አማራው በታሪኩ አጋጥሞት በማያውቅ ሁኔታ በጠላት ተከቧል። እንደ ከአራትመቶ ዓመት በፊት አይነት ከበባና ወረራ አንዣብቦበታል። ስለዚህም ይህንን ለመመከት አማራው እራሱን ካላደራጀ ይህ ትውልድ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት የሚሰራ ይሆናልና እጅግ መጠንቀቅ ያስፈልጋል» ብሎን እንደነበረ ሁሉ እስክንድር ነጋም ዛሬ በአዲስ አበባ ላይ እየተፈጸመ ያለውን እና ብሎም በሀገር ደረጃ እይተካሄደ ያለውን ዘርና እምነት ተኮር ጭፍጨፋን «በኢትዮጲያ ውስጥ የሙፈጠር የጄኖሳይድ አደጋ ስጋት» በሚል እስከ ተመድ …ድረስ ተጉዞ ዛሬ እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ ከሁለት ዓመት በፊት በግልጽ የነገረን ባለራእይ መሪ ነው።
የአንድ መሪ ሰው መገለጫ መስፈርታዊ ችሌታ በርካታ ችሌታዎችን ያካተተ ቢሆንም ትልቁና ውናው የመሪነት መለኪያ ራእይ ወይም ባለራእይ መሆንን ይጠይቃል።  ጄ/ል አሳምነውና እስክንድር ታላቅ የመሪነት ጸጋ የሆነውን ባለራእየትን የተጎናጸፉ ድንቅ አርቆ አላሚ፣አስተንትኖ አሳቢና ቀድሞ ተዘጋጆች መሪዎች የሆኑ ሲሆን  አሳምነውን በግፍ ግድያ ላይመለስ ስናጣው እስክንድርን በፈጠራ ክስ በግፍ እስር እንዲነጠለን ስንደረግ ለምንና እንዴት ብለን መነሳት ካልቻልን ሀገሪቷ ሰው የሆነ ሰው ስለሌላት ብቻ ነው።
በእስክንድር ውስጥ ሆነን ኢትዮጲያዊያንን ስንመለከት የስራ ባልደረባ ብቻ ሳይሆን ታማኝ የግል ጔደኛ የነበሩትን እንደነ የኢሳቱ ሲሳይ አጌና፣ የእስክንድር አድናቂ የነበረቺውን ብርቱኴን ሚደቅሳን ጨምሮ ዛሬ በገዢው የብልጽግና መንግስት ጎራ ተሰልፈው ያሉ ፖለቲከኞች፣ጋዜጠኝና አክትቪስቶች፣ምሁራን፣የእምነት ተቌማት መሪዎች፣የሀገር ሽማግሌዎችና እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች በማህበረሰቡ ውስጥ ተሰሚነትን ፈጥረናል የሚሉ ተጽእኖ ፈጣሪዎችን በሙሉ እጅግ የገለማ፣ያፈጠጠና ያገጠጠ ክህደታዊም ይባል ግዴለሻዊ -አሊያም ሆድ አደራዊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ተዘፍቀው ሰው የሚያሰኘውን የተሟላ ስብእናን ያጡ ሆነው ስናይ ሀገራችን ሰው አልባ መሆናን ነው ቢመረንም ቁልጭ ብሎ የሚታየን።
እስክንድር ከጀግናው ጄ/ል አሳምነው ጽጌ እጅግ የተለየ የሚያደርገው ደግሞ ሁለት መሰረታዊ ነጥቦችን ስናይ አንደኛው የእስክንድር ትግልና አጠቃላይ ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ ለአንድ ብሄር ሕዝብ (ለአማራ) ሳይሆን የትንሺቷ ኢትዮጲያ ቤት ለሆነቺው አዲስ አበቤና ብሎም በሀገር ደረጃ ለመላው ኢትዮጲያ ያለመ መሆንና ሁለተኛው የሚለይበት ደግሞ እስክንድር የቱንም ያህል በፈጠራ ክስ በግፍ እየተሰቃየ ያለ ሰው ቢሆንም በህይወት ያለ ባለራእያሙ ጀግናችን መሆኑ የተለየ ያደርገዋል።
በዚህ ሰላሳ ዓመት በፈጀው ፋሺስታዊው ትህነግ መራሹ ኢህአዴግ ቁጥር 1 እና ኦህዴድ መራሹ ኢህአዴግ ቁጥር 2 አገዛዝ ሀገራችን በርካታ ድንቅ ልጆቻ በግፍ ተነጥቃለች። በዚህም ብዙዎቻችን በቁጭትና በንዴት ወያኔንና የዛሬውን ወራሿን ኦህዴድን እናወግዛለን እንከሳለን። በግፍ የተገደሉ ጀግኖቻችንን የቱንም ያህል ብንወዳቸውና የቱንም ያህል ብንፈልጋቸው ዛሬ በህይወት ፈጽሞ አናገኛቸውም። ግን ዛሬም በህይወት ያሉ ድንቅ ጀግኖች አሉን። እስክንድር ነጋ አንዱና ዋነኛው ነው። በግፍ የተገደሉብንን ህይወት ማስመለስ ካልቻልንና  የማንችልም ከሆነ በህይወት ያለውንና ያሉትን ጀግኖቻችንን ግን እንዳይነኩ በመከላከልና በመጠበቅ ጀግኖቻችንን ከጠላታችን ጥቃት መታደግ ይቻለናል። ስለእኛ ብለው የተነሱትን እና የሚነሱትን ካልጠበቅን ከጠላቶቻችን የጥቃት ፍላጻ ተከላክለን ካልጠበቅን መሪ አልባ ህዝብና መሪ አልባ ሀገር ሆነን ለሀገርና ለህዝብ ኋላፊነት እማይመጥኑና ብቁ በማይሆኑ በእንደነ ፋሺስቱ አቢይ አህመድ መሰል ጸረ ህዝብና ጸረ ሀገር ሰዎች እጅ የምንገዛ ባሪያዎች እንሆናለን። ጀግኖቹን ያላከበረና ያላስከበረን ህዝብ የሚያከብር ባላንጣም ሆነ ጠላት የለምና እንደ ህዝብም ሆነ እንደ ሀገር እኛ አዲስ አበቤያዊያን እና ኢትዮጲያዊያን ዛሬ በንይወት ያለውን ጀግናችንን እስክንድር ነጋንና መሰል መሪዎቻችንን ህልውና ለመታደግ ማድረግ የሚገባንን ትግል በጽናት እናጧጥፍ። ይህ ዛሬ ነገ የሚባል ጉዳይ ሳይሆን ዛሬውኑ መጀመርና መፈጸም ያለብን ወሳኝ ተግባር ነው።
እኔም ለጀግናዬ በጀግንነት እታገላለሁ!!!
Filed in: Amharic