>

እስክንድር እና ምስክሩ........በችሎቱ ፊት...?!? (ሰለሞን አላምኔ)

እስክንድር እና ምስክሩ……..በችሎቱ ፊት…?!?

ሰለሞን አላምኔ

… የመጀመሪያው የዐቃቤ ሕግ ምስክር የሆነው ባለ ስመ ብዙው (አቶ ፈንታሁን፣ ይባስ፣ ዘሪሁን) የዳኞችን የማጣሪያ እና የዐቃቤ ሕግን የድጋሜ ጥያቄዎች ተጠይቆ ተጠናቋል። ይባስ ምስክርነቱን ሰጥቶ ሲጨርስ ለፍርድ ቤቱ እንዲህ ሲል አቤቱታ አቀረበ “በሀሰት መሰከረ እየተባልኩ ነው። በሀሰት መስክሬ ከሆነ እስክንድር በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ይማልና ያረጋግጥልኝ። ከዚያ በኋላ ምስክርነቴን አነሳለሁ” አለ። እስክንድርም ወዲያውኑ በፍጥነት የተሰበረ እግሩን አንጠልጥሎ በመጽሐፍ ቅዱሱ ለመማል ምስክሩ ይባስ ወደ ተቀመጠበት ወንበር ለመጠጋት ሞከረ። ሆኖም ዳኞች ከሥነ ሥርዓት ውጭ መሆኑን መበጥቀስ ከለከሉ።
እስክንድርም አለ “አውቃለሁ። ይሄን ከእናንተ ፍርድ ውስጥ አታስገቡት። ከዚህ ለታደመው ሕዝብ፣ ለታሪክና ለፈጣሪ ግን መማል እፈልጋለሁ።” ሲል ችሎቱን ጠየቀ። ችሎቱ ይህንንም ከለከለ።
በመጨረሻም እስክንድር የአንገቱን ማዕተብ አውልቆ ይባስን “እንካ ተቀበለኝ” አለው። ይባስም ምንም ሳይል አንገቱን ደፍቶ ከአደራሽ ወጣ።
እኛም ከዝምታችን ወጣን ዳኛውም ችሎቱ ከሰዓት ይቀጥላል ብሎ ተነሳ። እስክንድርም በሰዓቱ ፊቱን ወደእኛ እያዞረ የተለመደውን ቃል በትልቅ ትህትና ” ትጉሉ ይቀጥላል ” አለን። እኛም አይን አይኑን በናፍቆት እያየን ችሎቱን ለቀን ወጣን
ለታሪክ ይቀመጥ
Filed in: Amharic