>

የእምዬ ፡ ምኒልክ  ዘመን አይሽሬ ምክር...!!! (አሳፍ ሀይሉ)

የእምዬ ፡ ምኒልክ  ዘመን አይሽሬ ምክር…!!!

አሳፍ ሀይሉ

(በ1901 ዓ ፡ ም ፡ ግንቦት ፡ 10 ቀን ፡ አዲስ ፡ አበባ ፡ ጃን ፡ ሜዳ ፡  ጉባዔ ላይ የታወጀ)

‹‹ያገሬ ፡ የኢትዮጵያ ፡ ሰዎች ፡ ልጆቸ ፡ ወዳጆቸ ፡ እግዚአብሔር ፡ የገለጸልኝን ፡ ምክር ፡ ልምከራችሁ ፡፡ ምክሬንም ፡ እግዚአብሔር ፡ በልባችሁ ፡ እንዲአሳድርባችሁ ፡ ተስፋ ፡ አደርጋለሁ ፡፡

አጼ ፡ ቴዎድሮስ ፡ የሞቱ ፡ ጊዜ ፡ ከሳቸው ፡ ጋራ ፡ የነበረው ፡ ሰው ፡ ሁሉ ፡ ያንዱን ፡ አገር ፡ አንዱ ፡ እደርባለኁ ፡ አንዱን ፡ ገድዬ ፡ እኔ ፡ ጌታ ፡ እሆናለሁ ፡ እያለ ፡ ሁሉም ፡ ላይረባ ፡ ተላልቆ ፡ ቀረ ፡፡

ከዚህም ፡ በኋላ ፡ ያጼ ፡ ዮሐንስ ፡ ሰው ፡ የኾነውን ፡ የምታውቁት ፡ ነው ፧ ባገር ፡ በሽታ ፡ ሳይገባበት ፡ ሌላ ፡ የባዕድ ፡ ጦር ፡ ሳይነሣበት ፡ በምቀኝነት ፡ እርስ ፡ በርሱ ፡ እንደተላለቀ ፡ አይታችኁታል ፡፡

አሁንም ፡ ልጆቼ ፡ ወዳጆቼ ፡ አንዱ ፡ ባንዱ ፡ ምቀኝነት ፡ ይቅር ፧ ያንዱን ፡ አገር ፡ አንዱ ፡ እኔ ፡ እደርባለሁ ፡ እንዳትባባሉ ፡፡ እኔ ፡ እስካሁን ፡ በፍቅር ፡ እንዳኖርኋችሁ ፡ እናንተም ፡ ተስማምታችሁ ፡ በፍቅር ፡ እንድትኖሩ ፡ እለምናችኋለሁ ፡፡

እናንተ ፡ አንድ ፡ ልብ ፡ ከሆናችሁ ፡ በምቀኝነት ፡ እርስ ፡ በርሳችሁ ፡ ተዋግታችሁ ፡ ካላለቃችሁ ፡ በቀር ፡ አገራችንን ፡ ኢትዮጵያን ፡ ለሌላ ፡ ለባዕድ ፡ አትሰጧትም ፡ ክፉም ፡ ነገር ፡ አገራችነን ፡ አያገኛትም ፧ ነፋስ እንዳይገባባችሁ ፡ አገራችሁን ፡ በያላችሁበት ፡ በርትታችሁ ፡ ጠብቁ ፡ ወንድሜ ፡ ወንድሜ ፡ እየተባባላችሁ ፡ ተደጋገፉ ፡ የኢትዮጵያን ፡ ጠላት ፡ ተጋግዛችሁ ፡ ተደንበር ፡ መልሱ ፡፡

የኢትዮጵያ ፡ ጠላት ፡ ባንዱ ፡ ወገን ፡ ትቶ ፡ ባንድ ፡ ወገን ፡ ቢሄድና ፡ ደምበር ፡ ቢጋፋ ፡ በኔ ፡ ወገን ፡ ታልመጣ ፡ ምን ፡ ቸገረኝ ፡ ብላችሁ ፡ ዝም ፡ አትበሉ ፧ ያ ፡ ጠላት ፡ በመጣበት ፡ በኩል ፡ ኁላችሁም ፡ ሂዳችሁ ፡ አንድነት ፡ ተጋግዛችሁ ፡ ጠላታችሁን ፡ መልሱ ፡ እስከ ፡ እየቤታችሁ ፡ እስቲመጣ ፡ ዝም ፡ ብላችሁ ፡ አትቆዩ ፡፡

ይህነን ፡ ምክር ፡ ለናንተ ፡ መስጠቴ ፡ እኔማ ፡ በእግዚአብሔር ፡ ቸርነት ፡ ይህነን ፡ ያህል ፡ ዘመን ፡ ገዝቸ ፡ የለምን፡፡ ነገር ፡ ግን ፡ ሰው ፡ ነኝና ፡ እንግዴህ ፡ እስንት ፡ ያህል ፡ ዘመን ፡ እቆያለሁ ፡ ስል ፡ ነው ፡፡ አሁንም ፡ እኔ ፡ እንደተመኘሁት ፡ እግዚአብሔር ፡ የተጨመረበትና ፡ ፈቃዱ ፡ ሁኖ ፡ ልጄን ፡ ቢአቆምላችሁ ፡ ከልጀ ፡ ጋራ ፡ ሁናችኁ ፡ አገራችሁን ፡ ጠብቁ ፡ አደራ ፡ ብያችኋለሁ ፡፡ አደራ ፡ የሚአኖሩበት ፡ ሰው ፡ የታመነ ፡ ስለሆነ ፡ ነው ፧ ልጀን ፡ አደራ ፡ መስጠቴ ፡ ከልጀ ፡ ጋር ፡ ኢትዮጵያን ፡ አደራ ፡ ጠብቁ ፡ ማለቴ ፡ ነው ፡፡

እኔም ፡ እሄው ፡ በገዢዎቹ ፡ አለማወቅ ፡ በሕዝቡ ፡ አለመሰማማት ፡ የተነሳ ፡ ተብዙ ፡ ዘመን ፡ ጀምራ ፡ ተከፋፍላ ፡ የነበረችውን ፡ አገራችነን ፡ ኢትዮጵያን ፡ ማስኘ ፡ ተጣጥሬ ፡ ይሄው ፡ አስፍቻታለሁ ፡፡ እናንተም ፡ ከልጀ ፡ ጋራ ፡ ሁናችሁ ፡ ተሰማምታችሁ ፡ የኢትዮጵያ ፡ ደንበር ፡ እንዲሰፋ ፡ እንጂ ፡ አንድም ፡ ጋት ፡ መሬት ፡ እንዳይጠብ ፡ አድርጉ ፡ ጠብቁ ፡ አልሙ ፡፡ የደጊቱ ፡ አገራችን ፡ የኢትዮጵያ ፡ አምላክ ፡ ይገዛችሁ ፡ ይጠብቃችሁ ፡፡

ከዚህ ፡ ቃል ፡ የወጣ ፡ በሰማይም ፡ ነፍሱ ፡ በምድርም ፡ ሥጋው ፡ ልጅ ፡ እስከ ፡ ልጅ ፡ ልጁ ፡ የተረገመ ፡ ይሁን ፡ የኢትዮጵያ ፡ ወቃቢ ፡ ያጥፋው ፧ እኔም ፡ ሳለሁ ፡ ከፈቃዴ ፡ የወጣውን ፡ እረግሚአለኁ ፡፡››

 /ምንጭ ድርሳን፡- አፈወርቅ ፡ ገብረ ፡ ኢየሱስ ፡ ዘብሔረ ፡ ዘጌ ፡፡ ዳግማዊ ፡ ምኒልክ ፡ ንጉሠ ፡ ነገሥት ፡ ዘኢትዮጵያ ፡፡ ገጽ 113-115፡፡ በሽህ ፡ ተ፱፻፩ ፡ ዓመተ ፡ ምሕረት ፡ ሮማ ፡ ከተማ ፡ ታተመ ፡፡/

ዛሬ ላይ ያለን፣ እስቲ ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ ምኒልክ ቀድመው ከተናገሩት ያልሆነና ያልሆንነው ምን አለ? ሁሉም የተናገሩት ቃል ተፈጽሟል፡፡ የቀረን ቢኖር የእርግማን ቃላቸው ነው፡፡ እሱንም እየኖርነው ነው፡፡ ምኒልክ ነብይ ነው፡፡

‹‹ባቡሩም ሰገረ፣ ስልኩም ተናገረ

ምኒልክ ነቢይ ነው ልቤ ጠረጠረ፡፡

ነቢይ ለመሆንህ የተገባህ ነህ

አላፊውን ትተህ መጩን ታውቃለህ፡፡»

ክብር ለኢትዮጵያዊው ነብይ ለእምዬ ምኒልክ!

ልቦናውን ይስጠን፡

Filed in: Amharic