>
5:26 pm - Monday September 15, 2617

ፌስቡክ ያገደው የጋሻው መርሻ መልእክት

ፌስቡክ ያገደው የጋሻው መርሻ መልእክት
…. የወገን ጦር ከባድ መሳሪያዎች አቅጣጫ ቀይረው ስለነበር የጦሳ ገደላ ገደል ድምፁን ሲያስተጋባው ህዝቡ ጦርነቱ ለደሴ የቀረበ መስሎት ተደናግጦ ነበር። የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ ወያኔ እና ከዳሚወቿ ደሴ ገባን እያሉ ራሳቸውን ሲያረኩ ውለዋል አሉ። መቸም እንደ ወያኔ አይነት ዝናብ ሳይኖር መብረቁን አየሁት ብሎ የሚዘላብድ ፍጡር አይቸ አላውቅም።
በሴራ ጦሩ እየሸሸ የሚባለውን ነገር በአይኔ ተመልክቸ እንዳረጋገጥኩት ከሆነ ውሸት ነው። ከስንዴ እንክርዳድ፣ ከወተት የማጠኛው ከሰል እንደሚገኘው ከጦሩ ውስጥም የሚያበላሹ ሊገኙ ይችላሉ። ይህ ግን በዓለም ሁሉ የሚያጋጥም እንጅ በእኛ ብቻ የደረሰ የተለዬ ክስተት አይደለም። የእናት ሆድ ዥጉርጉር እንዲሉት ነው ነገሩ። የአንድ እናት ልጆች አንዱ ካህን አንዱ ማጅራት መች የመሆን እድል ያላቸው መሆኑን በየሰፈራችን ምስክርነት ማምጣት እንችላለን። ስለሆነም ተዋጊው ጦር ላይ እንደሁልጊዜው በጀግንነት ሲዋደቅ እንጅ የተለዬ ችግር መኖሩን አላየሁም።
አንዳንዱ ሰው ተዋጊው ጦር የተለዬ ዩንፎርም ስለለበሰ እና መሳሪያ ስለተሸከመ ብቻ ከእኛ ዝቅ ያለች ነፍስ ያለው አድርጎ ይመለከተዋል። እርሱ ሰፈሩን ጥሎ እየፈረጠጠ ፍርሃቱን በሰራዊቱ ሊያላክክ ይሞክራል። ወዳጀ ወታደሩ ከእኔ ከአንቺ እኩል ነፍስ ያለው ስጋ ለበስ እንጅ ብረት ቅብ አይደለም። ለወታደራዊ ታክቲክ ማፈግፈግ እንዳለ ሆኖ ወታደር አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ ነፍሱ ወደኋላ ተመለስ ብላ ልትመክረው ትችላለች። ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ ብዙ መከራ የተቀበለ ሰራዊት መሆኑን አንካድ። ይህ ሰራዊት ያለምንም እረፍት ለአንድ ዓመት የተዋጋ ከመሆኑም በላይ ከውስጥም ከውጭም ከፍተኛ ክህደት የተፈፀመበት ሰራዊት መሆኑን አንዘንጋ።  በዚህም የተነሳ በቡድንም ሆነ ለብቻው ወደኋላ የሚያፈገፍግ የሰራዊት አባል ሊያጋጥም ይችላል። እንደዚህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥም ወታደሩን አበረታቶ፣ እግሩን አጥቦ፣ ልብሱን ቀይሮ፣ ምግብ እና መጠጥ ሰጥቶ ወገን እንዳለው፣ ደጀን ህዝብ ከኋላው እንዳለ ሲያስረዱት ሳያቅማማ ለመዋጋት ተመልሶ ይገባል። ይኸ ክስተት የተለመደ ነው። የደባርቁ ጉልህ ምሳሌ እንደሆነ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
ከተማ ተዘርፍጦ ጦሩ ሆነ ብሎ እንደተፈታ የሚያወራውን አትስሙት። ትክክለኛ መረጃ ከጦር ግንባር የለውም። ዝም ብሎ የመጣለትን ነው የሚያወራው። አንዳንዱ የወሬ ሱስ ስላለበት ብቻ ያወራል። በነገራችን ላይ በጦር ግንባር ላይ ትንሽዬ የመረጃ ክፍተት እና ስህተት እጅግ ብዙ ዋጋ ነው የምታስከፍለው። ስለዚህ እንዳመጣልን የምናወራ ሰዎች እባካችሁ በህዝብ አምላክ ይዘናቹሃል ዝም በሉ።
በተዋጊው በኩል ህዝቡ በሚገባ ደጀን አልሆነንም፣ መረጃ አልሰጠም የሚል ቅሬታ ነበር። ይህ አሁን ተቀርፏል። ወታደሩም አይዋጋም በሴራ ለቆ ይወጣል የሚለው ውሸት መሆኑን አይተናል። የአዬር ኃይሉ ሆነ ብሎ ሌላ ቦታ ነው የሚመታው የሚሉ አሉቧልታዎች ነበሩ። እነዚህን አሉቧልታዎች ቀረብ ብለን ስንማለከታቸው እውነት ሆነው አላገኘናቸውም። ከተዋጊው ኃይል አካባቢ ባገኘሁት መረጃ ከዚህ በፊት ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ወደጠላት የሚያስተኩስ የሰው እጥረት ነበር። ከሰሞኑ ባለው ሁኔታ ግን ህዝቡን የማነቃቃት ስራ ስለተሰራ አንዲትም የመረጃ እጥረት አልነበረም። በመረጃው መሰረትም መከላከያ ሰራዊቱ ስኬታማ የአየር እና የምድር ኃይል ድብደባዎችን በማድረግ ወራሪውን ቡድን ከባድ የሰባዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ እንዲጎነጭ አድርጎታል። ለምሳሌ ከኩታበር ጀምሮ እስከ ቢስቲማ አቅጣጫ ያለው መረጃ ልቅም እና ጥንቅቅ ያለ ስለነበር የሚደንቅ ስራ ተሰርቷል። አዬር ኃይሉ ግሩም ነበር። አዬር ኃይሉ ገራሚ ስራ የሰራው የተዋጊ ጀቶቹ እና አብራሪዎቹ ስለተለወጡ አልነበረም። ይልቁንስ የመረጃው አይነት እና እውነትነት ስለተለወጠ እንጅ። መረጃውን በማድረስ ረገድ ብዙ የአካባቢው ልጆች ግሩም ስራ ሰርተዋል። ይህንን ከሽኖ በማስተላለፍ በኩል አቶ የሱፍ ኢብራሂም እና ጓደኞቻቸው በብዙው ተወተዋል።
በአጠቃላይ ህዝቡ በተለዬ ወጣቱ የሚያስተባብረው አመራር ካገኘ ታምር መፍጠር እንደሚችል በትንሽ ስራ አይተነዋል። ጓዳ ለጓዳ ተዘርፍጦ ወጣቱ ወኔ የለውም የሚለውን በትንሽ ጉልበት እና መናበብ ወጣቱ ማዕበል ሆኖ ሲጎርፍ አሳይተናል። ወጣቱን በማስተባበር በኩል ብዙ የደሴ እና የሌላ አካባቢ ወጣቶች አመርቂ ስራ ሰርተዋል። የቀድሞው ጦር አመራሮች እና አባላት እንዲሁም ወያኔ በየሰበቡ ከጦሩ የቀነሰቻቸው  ወገኖች ደሴ ከተማ ለወያኔ እሾህ እንድትሆን የሚደንቅ ስራ ሰርተዋል።  ሁሉንም ማመስገን ይገባል።
ሌላው እና የመጨረሻው ነገር የወያኔን ፕሮፖጋንዳ እንደሰሞኑ ዱቄት አድርገነው አናውቅም። ወያኔ በራሷ አመራሮች እና በደንገጡሮቿ በኩል የምትለቀውን ፕሮፖጋንዳ እንደ እስራኤል ሚሳኤል አምካኝ አየር ላይ እየቀለብን እሳት ለኩሰን ጭኗ ስር ነው የወተፍንላት። በራሷ ጅራፍ ገርፈናታል ማለት ይቻላል። አሁን ብዙ ሙት እና ቁስለኛ አስተናግደዋል። በዚህ አቅማቸው እንኳን ማሸነፍ በወጉ መሸነፍ እንኳን አይችሉም። በተደጋጋሚ እንዳልኩት እንኳን ደሴ እና ኮምቦልቻ ሊገቡ መቀሌ እንኳን መግባት ይከብዳቸዋል።
ይኸው ነው…!
የአብን ከፍተኛ አመራር – ጋሻው መርሻ ይማም
Filed in: Amharic