>

ኢትዮጵያ ትነሳለች ! (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

አይዞሽ ተነሽ ኢትዮጵያ፣ኢትዮጵያ ትነሳለች 

ደረጀ መላኩ (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)


ኢትዮጵያ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1896 አድዋ ላይ የፋሺስት ጣሊያንን ጦር ድል በመምታቷ ምክንያት ቅኝ ገዢዎችን ያስደነገጠ፣ያስቆጣ፣ አንገት ያስደፋና ቂም አርግዘው በኢትዮጵያ ላይ አሁን ድረስ ሴራና ተንኮል እንዲጎነጉኑ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ ኢትዮጵያ የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ተምሳሌትና ምልክት ለመሆን የበቃች ታሪካዊት ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ከፊትለፊት መስመር ላይ በመቆም የጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግልንም የመራች ናት፡፡ ኢትዮጵያ ከአልጄሪያ የነጻነት ጦርነት ጀምሮ እስከ የደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ የአፓርታይድ ትግል ድረስ አስተዋጽኦዋ የትዬየሌሌ ነው፡፡ ለብዙ አመታት ኢትዮጵያ የጸረ ቅኝ አገዛዝ ተጻራሪ ናት፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ኢትዮጵያ የፓንአፍሪካኒዝም የማእዘን ድንጋይም ከመሆኗ ባሻግር ለአፍሪካ ህዝቦችና ለሌሎች ለጥቁሩ አለም  የነጻነት እንቅስቃሴ ተምሳሌት ናት፡፡

በነገራችን ላይ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1930ዎቹ አጋማሽ ላይ የጣሊያን ፋሺስት ጦር ለተወሰኑ አመታት ኢትዮጵያን በመግዛቱ ምክንያት እግረመንገዱን ስለቴክኖሎጂ ጠቀሜታ ያስተዋወቀ ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ይመስላል አጼ ሀይለስላሴ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት፣ ኢትዮጵያን እንደ ቀሪው አለም በተለይም አውሮፓውያኑ ለማዘመን ሲሉ የዘመናዊነት እንቅስቃሴ  እንዲጸነስ ያደረጉት፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የምእራቡን አለም ዘመናዊነት እንዳለ በመቀበል ገቢራዊ ለማድረግ በመሞከራቸው በአሰቡት ደረጃ የተሳካላቸው አለመስልህ አለኝ፡፡ በተለይም  የምራባውያን ከፍተኛ ትምህርት ብቻውን ለኢትዮጵያ ብልጽግና እና ዘመናዊነት ያመጣል መባሉ ስህተት እንደነበር በርካታ ምሁራን የሄሱት ጉዳይ ነው፡፡ አጼሀይለስላሴ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ማስገንባታቸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ በምእራቡ አለም እውቀት እንዲካኑ በማድረጋቸው ታሪክ ስፍራውን አይነሳቸውም፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው ወይም እንደምናስታውሰው በአሁኑ ዘመን በህይወት የሚገኙት አንጋፋዎቹ ፕሮፌሰሮችና የፖለቲካ መሪዎች፣ በምእራቡ አለም የታወቁ ዩንቨርስቲዎችና የምርምር ማእከላት የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን የአጼ ሀይለስላሴ የትምህርት ፍሬዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ይህ የምእራቡ አለም የትምህርት ሞዴል እና የትምህርት ስርዓት ኢትዮጵያን እና ህዝቧን ወደ የላቀ የህይወት ደረጃ እንዳላደረሳት ዛሬ በህይወት ያለነው ምስክሮች ነን፡፡ ለምን ? እሰቲ በየአካባቢችሁ ተወያዩበት፡፡ በእኔ በኩል ምክንያቶቹ በርካታዎች ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ፣መሰረታ ምክንያቱ ግን የኢትዮጵያን ባህላዊ የትምህርት እውቀት አፈር ድሜ በማስጋጥ የምእራቡን አለም እውቀት እንዳለ ሳናላምጥ በመቀበላችን ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት በቀጥታ የተቀዳው ከምእራቡ አለም ነበር፡፡ በደርግ ዘመን ደግሞ የሶሻሊስቱን ርእዮት አለም የትምህርት ፖሊሲ ገቢራዊ አደረግን ዛሬ ደግሞ ቅጥ አምባሩ የጠፋበት የትምህርት ፖሊሲ ከጎሳ ፖለቲካ ጋር ተለንቆጡ ቁልቁል አውርዶናል፡፡ አንድ መዘንጋት የሌለብን ቁምነገር በአጼ ሀይለስላሰዴ ዘመን ትምህርት ተስፋፍቷል፡፡ በርካታ የኢትዮጵያ ልጆች የትምህርት መኣድ ተቋድሰዋል፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም ችግሩ የመጣው ወደ ውጭ ሀገር በተለይም ወደ የምእራቡ አለም ለትምህርት ተልከው የተመለሱት ኢትዮጵያውያን የባህል ግጭት ውስጥ ወደቁ፡፡ በአስተሳሰብ ከኢትዮጵያ ባላዊ መሪዎች መስማማት አልቻሉም፡፡ በአጭሩ ግጭት ውስጥ ወደቁ፡፡ በዚህ ምክንያት አብዮት መቀጣጠል፡፡ በነገራችን ላይ አብዮቱ አሁን ድረስ ፍጻሜውን አላገኘም፡፡ በነገራችን ላይ ያንዬ የነበረው አብዮት ከጎሳ ፖለቲካ ተጻራሪ የሆነ ኢትዮጵያን እንደ የበለጸጉት ሀገራት ወደፊት እንድትራመድ በማሰብ እና በማለም እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ የብሔር አክራሪዎች እንቅስቃሴ ከዘመናዊነት እሳቤ ውጭ እንደነበር ምሁራን በሰፊው የሄዱበት ጉዳይ ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ የቀዝቃዛውን ጦርነት ተከትሎም የመጣ ነው፡፡ የአጼ ሀይለስላሴ ንጉሳዊ አገዛዝ ከመውደቃቸው በፊት ጠንካራ ተቋማት ስላልነበሩ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1974 አጼ ሀይለስላሴ ከወደቁ በኋላ በተለያዩ ሃሳቦች የተማረኩ ወጣቶች የጎሳ ፖለቲካ እና የሶሻሊስት ርእዮት ኢትዮጵያ ከወደቀችበት ሊያነሳት ይቻለዋል፣ በሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ፡፡ ለአብነት ያህል እንደ አውሮፓውኑ አቆጣጠር 1975 የተመሰረተው የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት ይጠቀሳል፡፡ የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት አመሰራረት ከእኩልነት መብት ጥያቄ ያፈነገጠ ነበር፡፡ ከሌላው ኢትዮጵያዊ በተለየ መልኩ የትግራይ ህዝብ ተጨቋኝ አልነበረም፡፡ የፊውዳል ስርዓቱ የነበረው በኢትዮጵያ የግዛት ክልል ነበር፡፡ ስለሆነም ጭቆናው ከነበረ በሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች ላይ ነበር እንጂ የትግራይ ወንድሞቻችን በተለየ መልኩ ተበድለዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ይህ የታሪክ ቅጥፈት ነው፡፡ የአልባኒያ ሶሻሊዝምን ሞዴልን ይከተሉ የነበሩት የያኔዎቹ ‹‹ተሃህት › ወይም በአልባኒያ ዝግ የሶሻሊስት ርእዮት ነሁልለው የነበሩት የያኔዎች ተጋዳላዮች  Inspired by Hoxha’s Communist Albania model, › የትግራይ ህዝብ ይሞግታቸው ስለነበር ‹‹ የራስን እድል በራስ ለመወሰን›› የሚለውን መብት ለትግራይ ህዝብ ገቢራዊ ለማድረግ ነው የምንታገለው በማለት የትግራይን ህዝብ ሰብከውታል፡፡ ይህ ሃሳብ ( የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚለውን የሶሻሊስቱ የጆሴፍ ስታሊን ጽንሰ ሃሳብ ማለቴ ነው) በ1980ዎቹ መጨረሻ ( እ.ኤ.አ.) የወያኔ ቡድን መላው ኢትዮጵያን በመዳፉ አስገብቶ የማእከላዊ መንግስቱን ከተቆጣረ በኋላ በህግመንግስቱ ውስጥ በማካተት ለሁሉም የኢትዮጵያ ነገዶች ወይም ብሔሮች መብት እንዲሆን አደረገው፡፡ የወያኔ ቡድን ይህን ገቢራዊ ለማድግ የተገደደው ትግራይ በግዜው በኢኮኖሚ ጠንክራ እንደ ሀገር መቆም ስለማትችል ኢትዮጵያን አንድ አድርጌ መግዛት ከቻልኩ በሚል እሳቤ እንደነበር  ብዙዎች የፖለቲካ አዋቂዎች የሄዱበት አቢይ ጉዳይ ነበር፡፡ ከጂኦፖለቲከል አኳያ ኢትዮጵያ የግዛት አንደነቷ እንዲጠበቅ ተፈልጎ ነበር፡፡ ውጤቱ ግን አላማረም፡፡ በስመ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ርእዮት የወያኔ ኢህአዲግ ስርዓት ነግሶ ነበር፡፡ ሁላችንም እንደምናስታውሰው የወያኔ ኢህአዲግ ስርዓት በበላይነት ይመራ የነበረው ደግሞ በወያኔ ቡድን ስለመሆኑ ክርክር የሚያስነሳ አይመስለኝም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1995 በወጣው የኢትዮጵያው ህገመንግስት ‹‹ የራስን እድል በራስ መወሰን እሰከመገንጠል የሚለው መብት›› እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ይህ አንቀጽ ደግሞ ማህበራዊ መከፋፈል ላይ የሚያተኩር፣የሀገሪቱን ማህበራዊ እና ብሔራዊ ፋብሪክ (ስሪት) ችላ ያለ እንደሆነ በርካታ ስመጥር የህገመንግስት ምሁራን የተቹት አቢይ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ይሄንኑ የወያኔን መንገድ በግዜው ሲተቹ ከነበሩት አንዱ የተሃህት መስራች አባላት አንዱ የሆኑት አቶ አረጋ በርሄ ይገኙበታል፡፡ እንደ አቶ አረጋዊ በርሄና ሌሎች የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት አንጋፋ አባላት የነበሩ በኢትዮጵያ አንድነት ስር አምባገነንነትን መታገል አግባብ እንደሆነ የሚያምኑ እንደነበሩ ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሌሎች የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ግን የጎሳ ፖለቲካ በማስፈን፣ የበላይነት እንቀዳጀለን በማለት አምነው ስለነበር አምባገነን ፈላጭ ቆራጭ ስርአት ዘርግተው ኢትዮጵያን በጎሳ ክልሎች ከፋፍለው እነርሱ የማእከላዊ መንግስቱን በመቆጣጠር ለ27 አመታት ገዝተዋል፡፡ አንደ ጎርጎሮሲኑ አቆጣጠር 1974 ጀምሮ ወያኔ በትረ መንግስቱን እስከተቆጣጠረበት ግዜ ድረስ በኢትዮጵያ ምድር ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ መድረክ መፍጠር አልተቻለም፡፡ ወያኔ መድበለ ፓርቲ ስርዓት መስርቻለሁ በማለት ቢቀላምድም እስከ ውድቀቱ ድረስ በኢትዮጵያ አምባገነን ስርዓት ከማንበር ውጭ የፈየደው ቁምነገር አልነበረም፡፡ ወያኔ የሀገሪቱን ባንክና ታንክ በመቆጣጠር የፈለገውን ሲያደርግ የነበረ እኩይ ስርዓት ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የግፉ ጽዋ ሞልቶ ስለፈሰሰ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2014 ጀምሮ በተለይም በኦሮሚያ ክልል የተቀጣጠለው አመጽ፣የአማራውን ክልል በመጨመሩ አሰልሶም ይሄው ህዝባዊ አመጽ በመላው ሀገሪቱ ስለተደራሰ የወያኔ-ኢህአዲግ አገዛዝ በየካቲት 2018 ( እ.ኤ.አ.) የግዜው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሀይለማርም ደሳለኝ ስልጣናቸውን በግዛ ፈቃዳቸው እንዲለቁ መገደዳቸው ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎ ያለምንም ደም መፋሰስ በመጋቢት 2018 ( እ.ኤ.አ.) በተካሄደው ምርጫ ዶክተር አብይ መሐመድ የኢህአዲግ ስራ አስፈጻሚ ሊቀመንበር ኋላም በጎሳ ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት  ጠቅላይ ሚንሰትር ተብለው መሰየማቸው ይታወሳል፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ህገመንግስት ያለተሻሻለ ሲሆን፣ በህገመንግስቱ የተደነቆለው ‹‹የራስን እድል በራስ መወሰን ›› የሚለው አንቀጽ 39 ለአፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያን ለሚወዱ አፍሪካውያን ሁሉ ከባድ ስጋት ጥሏል፡፡ ይህ ጎሳ ህገ መንግስት በቅድመ የአፍሪካ ቅኝ አገዛዝ ዘመን  የነበረ ቅኝ ገዢዎች ገቢራዊ አድርገውት የነበረ፣ብሔራዊና ማህበራዊ ትስስርን ችላ ያለ፣የሲቪክ ማንነትን የሚክድ ነው፡፡ እንደ ፒተር ኤክ Peter Ekehየመሰሉ አፍሪካዊ የፖለቲካ ጠበብት በጥናታቸው እንደረሱበት ከሆነ፣ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች ዋነኛ አለማ የአከባቢያቸውን የተፈጥሮ ሀብት በብቸኝነት ለመቀራመት እንጂ ቆመንለታል የሚሉትን ማህበረሰብ ከውርደት ፣ከድህነት፣ከችጋር ለማውጣት አይደለም፡፡ በአፍሪካ የጎሳ ፖለቲካ የቅኝ ገዢዎች ውርዴ የነበረ ሲሆን፣ በዛሬው ዘመን በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የጎሳ ፖለቲካ በህግ የታገደ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ በኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ ለመጀመር የሞከረችው ጣሊያን ስትሆን የሽንፈትን ጽዋ ስለተጎነጨች እቅዷ ከሽፎባት ቆይቷል፡፡ አሰዛኙ ዜና ግን በኢትዮጵያ ሀገር በቀል የሆነው የወያኔ ቡድን በ1983 ዓ.ም. የጎሳ ፖለቲካ መርዝ በኢትዮጵያ ምድር በመዝራት ኢትዮጵያን ለስቃይ ዳርጓት ይገኛል፡፡በምእራብ ኢትዮጵያ በተለይም በወለጋና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚፈጸሙ ዘር ተኮር ጥቃቶች መሰረታዊ ምክንያቱ የዚሁ የጎሳ ፖለቲካ መርዝ ነው፡፡ ጠበቃ ተማም አባቡልጉ አንዳለው ከመርዘኛ ዛፍ ፍሬ የሚጠበቀው መርዝ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ህዳር 2020 በተገንጣይ ሀይሎችን በማእከላዊ መንግስት መሃከል የተከፈተው ጦርነት መጨረሻው ምን እንደሆነ ለማወቅ ወይም ለመተንበይ እጅግ አዳጋች እየሆነ ስለመምጣቱ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች የሄሱት ጉዳይ እየሆነ መጥቷል፡፡ በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መሃል ያለው  የርእዮት አለም ልዩነት ምን እንደሆነ ለማወቅም አስቸጋሪ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱ የፖለቲካ ተንታኞች ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ከዚህ ባሻግር የኢትዮጵያ መንግስት የጠላትን ፍልስፍና ሃሳብ ( ለአብነት ያህል የጨቋኝ ጨቋኝ ፍልስፍና፣ ይጠቀሳል ) ለምን መግደል አልፈለገም በማለት የሚጠይቁ ኢትዮጵያውያንም እጅግ እየበዙ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የወያኔ የፕሮፓጋንዳ አታሼ የነበሩት ሟቹ አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው የሰሜኑ ጦርነት በተጀመረ አጭር ግዜ ውስጥ የሰጡት መግለጫ አስደንጋጭና አነጋጋሪ ይመስል ነበር፡፡ ምክንያቱም የወያኔ ቡድን ድንገተኛ ጥቃት በሰሜን እዝ ላይ በመሰንዘር ጉዳት ስላደረሰ ብቻ የኢትዮጵያን የጦር ሀይል በአጭር ግዜ ውስጥ ማሸነፍ እንደሚችሉ በአደባባይ ደስኩረው ነበር ሆኖም ግን ጦርነቱ ከተጀመረ አመት ሊሞላው አንድ ወር ቀርቶታል፡፡ (ይህ ጽሁፍ በሚዘጋጅበት ጥቅምት 12 ቀን 2014  ጀምሮ ህዳር ወር 2014 መጀመሪያ ወር ይቀረዋል)

በእውነቱ ለመናገር የሁለቱ ሀይሎች ጦርነት ከገጠሙ በኋላ ( የፌዴራል መንግስቱ ጦርና የአሸባሪው ወያኔ ቡድን ታጣቂዎች ማለቴ ነው) ለጦርነቱ የተሰጠው ግምት አንዳንድ ስህተት ነበረው፡፡ የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች በአንድ በኩል ጦርነቱን በአሸናፊነት እንደሚወጡ በብዙ የደሰኮሩ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦር አታሼዎችም ቢሆኑ ጦርነቱን በፍጥነት ለመቋጨት ዝግጁ እንደሆኑ ለመገናኛ ብዙሃን ከሰጡት ቃለምልልስ ላይ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ መንግስት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔ ካደረገ በኋላ የአሸባሪው ወያኔ ቡድን በአማራ ክልል ሰሜን ወሎና ሰሜን ጎንደር፣እንዲሁም በአፋር ክልል ወረራ በመፈጸሙ ምክንያት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ የወያኔ አሸባሪ ቡድን የርስበርሱን ጦርነት አድማስ በማስፋት አትዮጵያን ለማዳከምና አንድነቷን ለማላላት በሚጎነጉነው ሴራ ሰፍር ቁጥር የሌላቸው ዜጎች እየተገደሉ ስለመሆኑ፣ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵዊ ዜጎች እትብታቸው ከተቀበረበት መንደር ስለመፈናቀላቸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ለርሃብ መሰል አደጋ እንደተጋለጠ፣ በተለይም ሴቶችና አዛውንቶች ለጥቃት እንደተጋለጡ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አንዳንድ የአለም አቀፉ መገናኛ ብዙሃን በተለይም በምእራቡ አለም የሚገኙ አንዳንድ የታወቁ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ በተመለከተ የሚያወጡት ዘገባ ሚዛኑን የጠበቀ አይደለም፡፡ የወያኔ አሸባሪ ቡድን የሚፈጽውን ገደብ የሌለውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ሰፊ የዜና ሽፋን ሲሰጡ አይታዩም፡፡ አረ ሲፈልጉም ከነጭራሹ አይዘግቡትም፡፡ እነርሱ ( የምእራቡ አለም የዜና አውታሮችን ማለቴ ነው) የማእከላዊ መንግስት ፈጸማጨቸው የሚሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ብቻ ነው የዜና ሽፋን የሚሰጡት፡፡ በምእራብ ወለጋ ኦነግ ሸኔ ተብሎ በሚጠራው ( በመንግስት የዜና አውታሮች አጠራር ማለቴ ነው) በአማራ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ግፍ በተመለከተ ዜናውን ለአለም ህዝብ ለማሰራጨት መንፈሳዊ ወኔ የከዳቸው ናቸው፡፡ በትግራይ ኢትዮጵያዊ ሲቪል ዜጎቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰርክአዲስ እንደሚዘግቡት ሁሉ፣ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ፣ሰሜን ጎንደርና ደቡብ ጎንደር፣እንዲሁም አፋር ክልል በሚኖሩ የአማራና አፋር ተወላጆች ሲቪል ኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ አሸባሪው የወያኔ ቡድን የፈጸመውን ግፍ በተመለከተ ለመዘገብ አልፈለጉም፡፡ ለምን እስቲ ህሊና ያላችሁ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ምክንያታዊና የገለልተኛ አቋም ይዛችሁ ኦብጄክትቭሊ ጠይቁ፡፡ 

ምእራባውያን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ትችት፣በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ጉዳይ ላይ ገደቡን የጣሰ ጣልቃ ገብነት ለመተግበር መሞከራቸው፣ ግፍና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈጸመው በኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ነው እያሉ ዘውትር በታወቁ መገናኛ ብዙሀኖቻቸው እየዘገቡ፣ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ያለውን አሸባሪውን የወያኔ ቡድን በሎጂስቲክና በፖለቲካ መደገፋቸውን ከቀጠሉ ውጤቱ ለአካባቢው ሰላም የሚፈይድ አይመስለኝም፡፡ በአካበቢው(በተለይም በኢትዮጵያ ምድር ማለቴ ነው)  የባያፍራን (Biafran )ግዛት ከመፍጠር ውጭ የሚያመጣው ፋይዳ ያለ አይመስለኝም፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠጠር በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ በባያፍራን ግዛት ተቀስቅሶ የነበረው ጦርነት ለተራዘመ ግዜ የቆየ ነበር፡፡ ደምአፋሳሽ ጦርነት ቀጥሎ ነበር፡፡ ጦርነት በምንም አይነት መፍትሔ ሊሆን አይቻለውም፡፡ በዚሁ መሰረት በሰሜን ኢትዮጵያ በአሸባሪው ጥጋብና ትእቢት አመሃኝነት የተቆሰቆሰው ጦርነት ግዜ በገዛ ቁጥር ኢትዮጵያ ሀገራችንን ከባድ ዋጋ ያስከፍላታል፡፡ ፍጻሜው አያምርም፡፡ በአካባቢው የጂኦ ፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማሳካት እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ሀገራት የትዬሌሌ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል ቻይና በአፍሪካና ኢትዮጵያ ላይ ያላትን ተጽእኖ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ከዚህ ባሻግር ይህቺው የአለማችን ሁለተኛው የኢኮኖሚ ክንድ በናይል ወንዝ ፖለቲካ ላይ ያላት ተጽእኖዋም ሰፊ ነው፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ በምእራባውያን በተለይም በተባበረችው አሜሪካ የነበራትን ተቀባይነት መዘንጋት የለብንም በግዜው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት ሟቹ አቶ መለሰ ዜናዊ የአፍሪካ ወጣትና ተራማጅ መሪ እየተባሉ በምእራባውያን ሲሞካሹም ነበር፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ይህቺን ሀገር በራሳቸው መንገድ፣ለራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም ሲሉ ለመቀራመት የማይተኙ በርካታ ሀገራት እንደሆኑ ኢትዮጵያውያን ማስታወስ ይገባናል፡፡ የምእራቡ አለምም ሆነ አረቦች፣ እንዲሁም ቻይናና ሩሲያ በመጀመሪያ የራሳቸውን ሀገር ህዝቦች ለማሟላት የቆሙ ስለመሆናቸው ክርክር የሚያስነሳ አይመስለኝም፡፡ የሚያዋጣን የህብረት ፍልስፍና ተከትለን ራሳችንን መቻል ነው፡፡

ከሰላሳ አመታት በፊት የወያኔ አሸባሪ ቡድንን ሲደግፉ የነበሩት ምእራባውያን ዛሬም ያንን አሸባሪ ቡድን ለመደገፍ መነሳታቸው ስህተት ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ሰላም መከበር የሚደማ ልብ እንደሌላቸው ማሳያ ነው፡፡ ምናልባት ወያኔ ኢትዮጵያን የጎሳ ፖለቲካ ቤተሙከራ እንዲያደርግ እገዛ ማድረጋቸውና ፣ ወያኔ ከጠፋ የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ሊያከትምለት ይችላል በሚል ስጋት ላይ ከወደቁ ይህ የራሳቸው ጉዳይ ይሆናል፡፡ እንደ ሴናተር ክሪስ ስሚዝን የመሰሉ የተባበሩት አሜሪካ የህዝብ ኮንግሬስ አባል የህሊና ሚዛናቸውን ተጠቅመው አጥፊዎችን ሁሉ መውቀስ ተገቢ ነው በማለት ምክረሃሳብ በሰጡት መሰረት የኦነግ ሸኔ እና የወያኔ አሸባሪ ቡድኖች የሚፈጸሙትን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በግልጽ ማውገዝ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡የአሜሪካ መንፈስ ሰብዓዊ መብት መሆኑን ማስታወሱ ታላቅነት ነው ፡፡ ሁሉም ተፋላሚ ሀይሎች አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ መርዳት ያባት ነው፡፡ለማናቸውም የምእራቡ አለም የሰብዓዊ መብቶች፣ዴሞክራሲያዊ መብቶችና የህግ የበላይነት እንዲከበር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እንማጸናለን፡፡

በኢትዮጵያ የርስበርስ ጦርነትን ለማቆም ምን ይበጀናል ?

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል በተለይም በአማራ ክልል ወሎ፣ሰሜን እና ደቡብ ጎንደር፣ እንዲሁም አፋር ክልል የወያኔ አሸባሪ ቡድን በፈጸመው ወረራ ምክንያት የተቀሰቀሰው የርስበርስ ጦርነት በፍጥነት መቋጫ ሊበጅለት ይገባል ብዬ አሰባለሁ፡፡ መፍትሔውን በተመለከተ የተለያዩ አካላቶች ወይም ግለሰቦች የተለያዩ ምክረ ሃሳቦቻቸውን ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ በእኔ በኩል ይህንኑ ደም አፋሳሽ ጦርነት ለመቋጨት የአፍሪካው ህብረት እና በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካው ቀንድ ከፍተኛ ተወካዮች ሃላፊነቱን መውስድ አለባቸው የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ለማናቸውም በአፍሪካ ህብረትና በአፍሪካ ህብረት የአፍሪካው ቀንድ ተመልካችነት የሚከተሉት ነጥቦች ቢካተቱ መልካም ነው፡፡

1.የኢትዮጵያው ፓርላማ የወያኔ ቡድንን አሸባሪ ብሎ መሰየሙ የታወቀ ስለመሆኑ የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም አለም አቀፉ ህብረተሰብ በተለይም የምእራቡ አለም ይህንኑ የኢትዮጵያን ፓርላማ ውሳኔ መቀበል ያለበት ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ባሻግር የወያኔ ቡድን በግፍ ወረራ ከፈጸመባቸው የአማራ እና አፋር ክልሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መውጣት አለበት፡፡

  1. በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው በሁሉም የኢትዮጵያ ግዛቶች ተፈናቅለው ለሚገኙ ሲቪል ኢትዮጵያውያን ያለምንም እንቅፋት ሰብዓዊ እርዳታ ሊደርሳቸው ይገባል፡፡ የሰብዓዊ እርዳታው አቅርቦት በየብስና በኢትዮጵያ መንግስት የአየር ኮሪደር ቁጥጥር ስር ሆኖ በጢያራ የእርዳታ እህል ቢከፋፈል የሰብዓዊ ቀውሱን ለመቀነስ ይረዳል፡፡
  2. በአጭር ግዜ ውስጥ በትግራይ ክልል ሁሉንም የፖለቲካ ሀይሎች ያሳተፈ የምርጫ ውድድር የሚካሄድበት ስትራቴጂና ስልት ለአካባቢው ሰላም ይበጃል፡፡

4.ያለምንም መዘግየት በኢትዮጵያ ምድር የሚገኙ የፖለቲካ ሀይሎችን ሁሉ ያሳተፈ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ቢዘጋጅ፣ ለኢትዮጵያ ሰላም መንገድ እዳው ገብስ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ይህን በእውነትና ፍትህ መሰረት ላይ ሆኖ ሊዘጋጅ የሚገባውን ብሔራዊ የውይይት መድረክ ሃላፊነቱን ወስዶ መፈጸም ያለበት ማን ነው የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው ሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች መንግስትን ጨምሮ በብርቱ ፣ በቀና መንፈስ ከወዲሁ ሊነጋገሩበት ይገባል፡፡ በሪፐብሊኩ ፕሬዜዴንት፣በሃይማኖት አባቶች፣በሃገር ሽግሌዎች፣ምሁራን፣ ወይንስ የውጭ ሀገር መንግስታት( ለኢትዮጵያ አንድነት የሚደማ ልብ ያላቸውን ሀገራት ማለቴ ነው፡፡ካሉ፡፡) አመሃኝነት ይሁን ለሚለው በቅድሚያ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሀይሎች ይሁንታ ሊሰጠው ይገባል የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ እስቲ በዚህ ጉዳይ ላይ በየአካባቢያችሁ ተወያዩበት፡፡

  1. በጦርነቱ ግዜ ለተፈጸሙ ግፎች እና የሰብዓዊ መብት ጥቶች ሁሉ ( ከሁለቱም ወገኖች አኳያ የተፈጸሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ማለቴ ነው፡፡) ይቅር ለእግዜአብሔር ለመባባል እንዲያስችለን የእውነታና እርቅ ኮሚሽን በፍጥነት መቆም ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህ የእውነታና እርቅ ኮሚሽን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎች ስለፈጸሙት ግፍ በአደባባይ እንዲናዘዙ፣ ግፍ የተፈጸመባቸውም ይቅርታ የሚሰጡበትን የሚያመቻች ከማናቸውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ የሆኑ ሰዎችን በአባልነት ቢያቅፍ ፖለቲካዊ ፈውስ ለማግኘት አንድ እርምጃ ያራምደናል፡፡
  2. የሲቪል ማንነትን እና ብሔራዊ ስሜትን ለማስረጽ ይረዳ ዘንድ በመደበኛ ኢመደበኛ የትምህርት ስርአቱ ውስጥ እንዲካተት ኢትዮጵያውያን ሁሉ መተባበር አለብን፡፡ በተለይም የትምህርት ባለሙያዎች እውቀት ላይ መሰረት ያደረገ ፐሮግራም መንደፍ የህሊና እና የሞራል ሃላፊነት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ የቋንቋ ብዝሃነትን በአግባቡ ለመጠቀም ይረዳን ዘንድ እውቀትና ጥበብ ግድ ይለናል፡፡ ለአብነት ያህል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከአንድ በላይ ቋንቋ ቢማር ክፋት ያለው አይመስለኝም፡፡ ቋንቋ መግባቢያ መሳሪያ እንደመሆኑ መጠን አንድ ሰው ከአንድ በላይ ቋንቋ መማሩ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በቀላሉ መግባባት ይቻለዋል፡፡ አንድ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ አማርኛን ቋንቋ ማወቁ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም፡፡ሌላውም ኢትዮጵያዊ የኦሮምኛ ወይም ትግርኛ ቋንቋ ማወቁ ተገቢ ነው፡፡

7.የህግ አስፈጻሚዎችና የጸጥታ ሀይሎች የጦር መሳሪያ ብቻ ሳይሆን፣ በእውቀትም መታጠቅ አለባቸው፡፡ በተለይም የሰብዓዊ መብት እና የዲሞክራሲያዊ መብት አጠባበቅ፣ስለ የህግ የበላይነት አጠባበቅ መሰረታዊ እውቀት ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ገቢራዊ የሚያደርጉበት ስልት መነደፍ ወይም የፖለቲካ ነጻነት መስፈን አለበት፡፡ በየ አካባቢው ያሉ ሚሊሻዎችና የክልል ልዩ ሀይል አባላት ወደ መደበኛ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባልነት ተካታው በበለጠ ሳይንሳዊ በሆነ የወታደራዊ ሙያ ታንጸው የብሔራዊ ስሜታቸው ከፍ ስለሚልበት ሁኔታ የሀገሪቱ የጦር ባለሙያዎች እና የፖለቲካ ሰዎች እንዲመክሩበት እንማጸናለን፡፡

ከላይ የሰፈሩት ምክረ ሃሳቦች አሁን ለገጠመን የርስበርስ ጦርነት በከፊልም ቢሆን የመፍትሔ ሃሳቦች ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ ባሻግር አለም አቀፉ ህብረተሰብና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት በታሪክ ፊት ቆመዋል፡፡ በተለይም የተባበሩት መንግስታት የቆመለትን አላማ ገሸሽ በማድረግ ለሀብታም ሀገራት በተለይም በምእራቡ አለም እና የተባበረችው አሜሪካ ተጽእኖ ስር መውደቅ የለበትም ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለያዩ ግዜያት ኢትዮጵያ በፈተና በወደቀችበት ግዜ የአለሙ መንግስታት ማህበር ከሀይለኞችና ሀብታሞች ምእራባውን ፍላጎት አንጻር መቆሙ ትዝብት ላይ ጥሎታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ የህሊና ሚዛናቸው ያልተሰበረ የብይነ መንግስታቱ ሰራተኞች የተባበሩት መንግስታትን አሰራር በመተቸታቸው ከስራ ገበታቸው ለግዜው ገሸሽ እንዲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ትእዛዝ መሰጠቱ ከአንዳንድ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ስለመዘገቡ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አንዳንድ ሀብታም ሀገራት በተለይም ምእራባውያን ወይም የተባበረችው አሜሪካ በብይነ መንግስታቱ ወይም በብይነ መንግስታቱ ወኪል መስሪያ ቤቶች የየእለት ስራዎች ላይ ተጽእኖአቸው ሰፊ ነው፡፡ የራሳቸውን የውጭ ፖሊሲ በተባበሩት መንግስታት አመሃኝነት ለማስፈጸም የተለያዩ ዘዴዎችን ስለመጠቀማቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ስለሆነም የተባበሩት መንግስታት ዛሬ ኢትዮጵያ የገጠማትን የታሪክ ፈተና በህሊና ሚዛን ላይ ሆኖ ስለሚፈታበት መንገድ መምከር ያለበት ይመስለኛል፡፡

ሁላችንም የኢትዮጵያን ጥንታዊ የታሪክ ባለቤትነት መገንዘብ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የጂኦፖለቲካ መገኛዋ እና ለሌሎች የጥቁር አለም ሀገራት ሁሉ የነጻነት ምልክት ከመሆኗ ባሻግር ኢትዮጵያ የከሸፈች ሀገር ልትሆን ትችላለች ብሎ ለማሰብ ቢቻልም፡፡ ኢትዮጵያ አንድነቷ ሊናጋ አይቻለውም፡፡ ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ማህበርና የተባበሩት መንግስታት መስራች አባል ሀገር እንደመሆኗ መጠን፣ ለተገለሉ እና በቅኝ ለተገዙ ሀገራት በጽኑ የታገለች ሀገር ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣሊያን በግፍ በተወረረችበት ዘመን ሳይቀር የመንግስታቱን ማህበር አክብራ የነበረች ሀገር ናት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አጼ ሀይለስላሴ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1936 በመንግስታቱ ማህበር ፊት ቆመው ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣሊያን በግፍ ስለመወረሯ አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም የመንግስታቱ ማህበር የማያይ አይን፣ የማይሰማ ጆሮ ነበር የሰጣቸው፡፡ በነገራችን ላይ በተመሳሳይ መልኩ አሁን በህይወት ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  በህሊና ሚዛን ላይ መቀመጥ አቅቶት፡፡ በኢትዮጵያ ፍርደ ገምድል ውሳኔ የሚያሳልፍ ከሆነ የሚከተሉት ብርቱ ችግሮች ይከሰታሉ ብዬ እሰጋለሁ፡፡

  • በአፍሪካው ቀንድ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የፖለቲካ አለመረጋጋት በከፍተኛ ደረጃ ይከሰታል
  • አካባቢው ለአሸባሪዎች መፈልፈል ለም መሬት ይሆናል
  • የአለም አቀፍና የአሁጉሩ (የአፍሪካ) የፖለቲካ ክብድት ክሽፈት እውን ይሆናል(the loss of a continental and global political heavyweigh)
  • የሚከፈለው ዋጋ ለግምት የሚያዳግት ይሆናል

ለዚህም ነው  እንደ ወያኔ አይነቱን አሸባሪ እና ተገንጣይ ቡድን፣ለከት በሌለው ዝርፊያ የሚታወቅን ነውረኛ ቡድን  ደግፎ መቆም እጅግ አሳዛኝ እና አናዳጅ የሚሆነው፡፡ ባለፉት ሰላሳ አመታት እጅግ መጠነ ሰፊ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ችግር ውስጥ ለተዶለችው ኢትዮጵያ ከብይነ መንግስታቱ ድርጅት ፍትሃዊ ፍርድ ያስፈልጋታል፡፡

ኢትዮጵያ ምንግዜም ቢሆን ሃይለኛ ሃሳብ ያላት ሀገር ናት፡፡ Ethiopia has always been a powerful idea የኢትዮጵያ ሃሳብ ጠባቦችንና አፍንጫቸው ስር የሚያስቡ ሰዎችን አይምሮ መግራት ይቻለዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ታሪክ እንደሚያስተምረን ኢትዮጵያ የቱንም ያህል በከባድ ችግር ውስጥ ብትዶልም መነሳቷ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ትነሳለች፡፡ እኛም ኢትዮጵያ እንድትነሳ በታሪክ ፊት ቆመናል፡፡

የዛሬውን ጽሁፌን የምቋጨው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ግንቦት 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በኢትዮጵያ መዲና አዲሰ አበባ ከተማ ላይ አጼ ሀይለስላሴ፣ክዋሚ ንክሩሃማ፣ ጀማል አብዱል ናስር በመሰሉ ወዘተ ታላላቅ የአፍሪካ መሪዎች  በተገኙበት በአዲስ አበባ ሲመሰረት በታላቁ እና ባለርእዩ የአፍሪካ ልጅ ዶክተር ክዋሚ ንክሩህማ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያቀረበትን ግጥም በመጋበዝ ይሆናል፡፡ አይዞሽ ተነሽ ኢትዮጵያ

Ethiopia shall rise

Ethiopia, Africa’s bright gem

Set high among the verdant hills

That gave birth to the unfailing

Waters of the Nile

Ethiopia shall rise

Ethiopia, land of the wise;

Ethiopia, bold cradle of Africa’s ancient rule

And fertile school

Of our African culture;

Ethiopia, the wise

Shall rise

And remould with us the full figure Of Africa’s hopes

And destiny.

Kwame Nkrumah, 1963

 

Filed in: Amharic