አምባገነንነት የራስህን ነገር ለማስፈን ስትል፣ የሌሎችን ነፃነት መቀማት ነው.. !!!
አሳፍ ሀይሉ
ስለ ዲሞክራሲ የተፃፉ አንዳንድ መዛግብትን ስማትር፣ ፈረንጆቹ ብዙ ደሃ (የቁስ ማለቴ ነው) ደሃ አገሮች ለምን አምባገነንነት እንደሚመቻቸው ሲናገሩ፣ አምባገነንነት የሚያስገኘው ፈጣን ውጤትና እርካታ እጅግ መሣጭ ሆኖ ስለሚያገኙት ነው በማለት ያስረዱናል። ለራሳችን። ይገርመኝ ነበር እስከ ቅርብ ጊዜ።
በብዙ የሙያ ህይወቴ ራስን መግታት መቻል (Self-restraint) ታላቅ ፈተና እንደሆነ ተመልክቼያለሁ። ብዙ ሰዎች የሚወዱት ምንም መሸፋፈን የሌለበት አምባገነንነትን እንደሆነም ተመልክቼያለሁ።
በልምምጥ ከምታገኘው ይልቅ፣ ማንቁርቱን አንቀህ፣ በአንዲት ቀጭን ትዕዛዝ፣ አደባይሀለሁ ብለህ፣ ወይም አሳይተህ የምታገኘው እሺታ እጅግ ፈጣንና ቀላል እንደሆነም ተመልክቼያለሁ።
እና ሥልጣንህን፣ ጉልበትህን፣ የክፋት ሀይልህን እንድትጠቀም ያለው ግፊት ከውስጥህ ብቻ ሳይሆን፣ ከውጪም በኩል የሚመጣ ነው።
ብዙ ሰዎች ቀላል ሆኖ ላገኙት አምባገነንነት በቀላሉ እጅ ይሰጣሉ። በፍቅር ይወድቃሉ። They cannot resist the temptation of exercising power and the easy privileges of powerfulness.
በበኩሌ ጥሎብኝ የአምባገነንነት መንፈስ የተፀናወተው ሰውም ሆነ አውሬ አልወድም። አልቀርብም። ከልቤ እነቅለዋለሁ። ደረጃውን ከዜሮ በታች አቀለዋለሁ።
ለአምባገነን አልንበረከክም። አምባገነን ሆኜም አላውቅም። ነፃነቴን እስከ ጥግ እወዳለሁ። በሌሎች ነፃነትም አልገባም። በሰው ነገር አልገባም ብለህ ሸሽተኸው መኖር የማትችልበት አጋጣሚ ግን ይመጣብሀል። ሰው ከሆንክ እሺ ብለህ የማትቀበላቸው ብዙ አምባገነናዊ ነገሮች ያጋጥሙሀል።
የቆየ ምሳሌ ልንገርህ። አንዴ በተማሪነት ዘመኔ ያጋጠመኝ ነው። ከአራት ኪሎ ዘውዲቱ ሆቴል እስኪበቃን ቀምቅመንና ደንሰን እኩለ ሌሊት ላይ ወደ ማደሪያችን ሶስት ሆነን እየተመለስን ነበር።
በመሐል ቅድስተ ማርያም ቤተክርስትያን ጋር ስንደርስ፣ ሁለት ዛፓዎች (ያኔ ፖሊሶቹን ዛፓ ነበር የምንላቸው) ከቆሙበት የሸዋ ዳቦ በረንዳ አስፋልት ተሻግረው እየተሯሯጡ መጥተው አስቆሙን።
ሰዓት እላፊ የለም። መታወቂያ ግን ጠየቁን። አሳየን። በጣም ተናደዱ። ተማሪነታችንን ሲያውቁ። እኛ እዚህ ብርድ እየመታን እናንተ ጠጥታችሁ በሌሊት ትዞራላችሁ! ብለው ደነፉ። አምባገነንነት ከComplex ጋር ሲዋሃድ ከባድ ነው። ቃል አልወጣንም።
ቀጠሉና ተንበርከኩ አሉን። በህይወቴ ለማንም ተንበርክኬ አላውቅም። “ለምንድነው የምንበረከከው፣ እንዲሁ አናግሩኝ፣ አልንበረከክም!” አልኩኝ። ያጠፋሁት ነገር የለም። ማንበርከክ አትችሉም ነው።
ወጣትነት አለ። ሞቅታው አለ። እና ወኔውም አለ። ይሄ ሁሉ ተደማም ዛጭንቅላቴ ላይ ያንን ለአህያ እንጂ ለሰው የማይገባ የጎማ በትራቸውን ከግራ ከቀኝ አወረዱብኝ።
ይሄን ሲያይ ሌላኛው ጓደኛዬ በፍጥነት ተንበረከከ። የአራዳ ልጅ አይገግምም። አኳኋኑን አይቶ እጥነው። ከዱላው በላይ አናዶኝ እንደነበር ትዝ ይለኛል።
ሌላኛው ሶስተኛው ጓደኛችን ግን ጎንበስ እንደማለት አስመስሎ እንደ አጭር ርቀት አትሌት ወደ አፄ ናዖድ ት/ቤት አቅጣጫ ተፈተለከ። ዛፓዎቹ እሱን እያሳደዱ ሮጡ።
ከነከስክስ ጫማቸው አይደርሱበትም። ጫማቸውን አውልቀውም አይደርሱበትም። ሠላቢ ነበር። ኋላ ሲነግረን ልቤን ነካው። እኔን ለማስጣል ብሎ ነው የሮጠው። ገሰመኝ። በሩጫ የማስጣል፣ ጠላትህን distract የማድረግ ዘዴ በዚያ ሞቅታ እንዴት መጣለት?
(ወይ አንተ? እንዲህ ዓይነቱን አስቂኝ የአባርሮሽ ሀሳብ ራሱ የሚያመነጨው ሞቅታው ራሱ አይደል እንዴ?!)
እኔም ጭንቅላቴን እያሸሁ፣ ጓደኛዬም ጉልበቱን እያሸ በተራችን ከሥፍራው ተፈተለክን። እስከዛሬ ግን በጭለማ በቅድስት ማርያም ፊት በተጋፈጥኩት ዱላ እኮራለሁ። “አልንበረከክም” ብዬ በተቀበልኩት የአጉራዘለሎች ዱላ ነው። ብንበረከክ ነበር የሚቆጨኝ እስካሁን።
እንዲህ ነኝ። ሰው ላይ አልደርስም። ትህትናዬን አልለቅም። ነፃነቴን አላስረክብም። አምባገነን መሆን ሲያምርህ በሃጃህ አልገባብህም። መብትህ ነው። እንደፈለግክ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት። ነገር ግን እኔ ጋር መጥተህ የአምባገነንነት ዘዴህ እንደማይሠራ ተምረህ ወይም በከንቱ ተፈራግጠህ ትመለሳለህ። እንጂ ያሰብካትን ከበሬታ ገድለኸኝ-ካልሆነ በፀጋ ከእኔ አታገኛትም።
ኋላ ዕድሜ ሰጥቶኝ ግን፣ ከብዙ ፖሊሶችና ሌሎች የህግ አስከባሪ አካላት ጋር በሚያያይዝ የሥራ ህይወት ተሠማራሁ። ከዚያ ልምድ የቀሰምኩት ነገር ቢኖር፣ ፖሊሶቹም ሆኑ ሌሎች እንደልቡዎች አምባገነንነትን የሚመርጡት፣ አምባገነን መሆን ውስጣዊ ደስታን የሚያጎናፅፍና ቀላል እሺታ የሚያስገኝ ስለሆነ ብቻ እንዳልሆነ ነበር።
ለምሳሌ ከሆነ ሰው ጋር የተጣላች የሰፈር ወይዘሮ አንዱን ፖሊስ ሮጣ ከመንገድ ትጠራና፣ ፖሊሱ ዱላውን መዝዞ አናት አናቱን እንዲቀጠቅጥላት አጥብቃ ትሻለች። ፖሊሱ ያንን ምሷን ካላሳያት “ምን የዛሬ ፖሊስ፣ ከረፈፍ ሁላ! ምን ሊረቡ?” ነው ወሬዋ ሁሉ።
በሌላውም ያው ነው። ባለሥልጣን ሆኖ ጉልበቱን ካላሣየ፣ ልፍስፍስና ቀጥቃጣ ወይም ነፈዝ መሆን አለበት።
ሲሾም ያልበላን፣ ያላበላን፣ ተቀናቃኝን በክርኑ ያልደቆሰን፣ ያቄሰን ባለሥልጣን ጠላትም ወዳጅም አይፈልገውም። የተማረ ሆኖ ያልተኮፈሰን፣ በባሌም በቦሌም ብሎ የሚታይ ቁስ ያላካበተን፣ ማንም አያከብረውም። ለአርዓያነት አይበቃም። አያስመካምና።
ስለዚህ ብዙው ሰው ከውስጡ ግፊት በተጨማሪ፣ ከውጪ የሚጠበቅበትን ለመወጣት ሲል የሚጠበቅበትን፣ የተሳለለትን፣ የተሰፈረለትን ዓይነት አምባገነን ሆኖ ይገኛል።
አይኔ እያየ ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ትርፍ ሰው አጠገቤ አይቀመጥም ብሎ ሲቀውጥ የማውቀው ተሳፋሪ፣ በሌላ ምሽት ሹፌሩ ረዳት የለኝም ሂሳብ ትቀበልልኛለህ ወይ? የሚል favour ስለጠየቀው ብቻ፣ በታክሲው ትርፍ ሰው ከመጫን አልፎ፣ አንዷን ወይ ውረጂ ወይ ተጠጊ ብሎ ከወያላ ብሶ ሲያስፈራራ አይቼ ተሸማቅቄያለሁ።
ከምኔው?! በቃ ሳያስበው በውስጡ የሣለውን አምባገነን ገፀባህርይ በአፍታ እየተወጣው ነዋ! እና አምባገነንነትን የምንቀዳበት ምንጩ ብዙ ነው። በየመንገዱ ሞልቶልናል። ብዙዎቻችን ዕድሉን ስናገኝ የምንሆነው፣ ያንኑ ያወገዝነውን ነው። ለአምባገነንነት ብዙ አመቺ ሁኔታዎች አሉ። ቀላል ነው። ለጊዜውም ቢሆን ውጤታማም ነው።
ታዲያ ከስንት ጊዜ በኋላ አሁን ከሰሞኑ በፌስቡክ ገፄ ላይ እያየሁትኮ ነው አምባገነንነትን። ይሄን ሁሉ ያስለፈለፈኝ። የራሴኑ የአምባገነንነት ሽግግር በፅሞና እያየሁት።
ፌስቡክ። ብዙ ዓይነት አመልና ፍላጎት፣ ብዙ ዓይነት ዒላማና ዓላማ ያለው ሰው የሚርመሰመስበት ትልቅ የመርካቶ ዕድር ነው።
ሎሬት ፀጋዬ “አይ መርካቶ” በሚለው ግጥሙ መርካቶን የተቃርኖዎች ውሁድ አድርጎ እንዳቀረባት፣ ፌስቡክም የተቃርኖዎች ውሁድ ነው።
ተቃራኒዎች ሲገናኙ ደሞ ሁሌ በሠላም አይተላለፉም። ንትርክ አለው። ጭቅጭቅ አለው። መለካከፍና ከፍ ሲልም መዘላለፍ አለው።
ግን ይሄ የልፊያ ነገሩ የሚያደክምህ ሰዓት ይመጣል። ሰዉ ከሰው ጋር ምን ያለፋልፈዋል? እኔስ ምን አለፋለፈኝ? ምን አጨቃጨቀኝ? በቀላሉ block እና unfriend አድርጎ መገላገል እያለ? የምን አተካሮ ነው?
ትዳር አይደል የመሠረትነው!? እኔ ሀሳቤን አቀርባለሁ። አንተም ሀሳብህን ታቀርባለህ። “ላይክ” እና “ላሽ” ተባብሎ ማለፍ እየተቻለ፣ የምን ስድድብ? የምን ድብድብ ያስፈልጋል?
ሀሳቤ በተደጋጋሚ ካልተመቸህ block አድርገህ ትገላግለኛለህ። አምባገነንነት ነው። ይገባኛል። ግን አምባገነናዊነትን ተላብሰህ በቀላሉ መገላገል ስትችል ለምን ትቋሰላለህ ከኔ ጋር?
የአምባገነንነቱ ዓላማ ሠላምን ለመጎናፀፍ ነው። ያንተ መለፋደድ ልኩን ካለፈ በፍጥነት unfriend አድርጌ አሰናብትሀለሁ። ትዕግሥትና አክብሮት ካልገራህ በፈጣን block ወጊድልኝ ካጠገቤ እልሀለሁ። በሠላም መለያየት ስንችል፣ ለምን በየቀኑ ሙዳችንን እንሠራረቃለን?
ይሄ እኮ ሰው የሚፈልገውን የሚያገኝበት መድረክ ነው። አይደለም? ካልፈለግክ ጥለህ መሄድ የምትችልበት። እየመጣህ ለቅሶና አፍ-እላፊ ብቻ ከሆነ “ቻው” ብዬ ከቤቴ ጠርጌ አሰናብትሀለሁ። እንጂ ባንተ ዘለፋ የምቀይረው ሀባ ነገር የለኝም። አምባገነንነት ማለት ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው ይሄው መሠለኝ?!!
በቃ ፈጣንና ውጤታማ ሠላም ማግኛ መንገድ እኮ ነው አምባገነንነት። ትዕግሥትህን ለሰው ለማስረዳት ከምትደክም፣ እንደ አህያ ተራግጠህ ድርሽ እንዳይልብህ ብታሰናብተው ለአንተም ግልግል፣ ለእሱም እረፍት ነው። እና በጣም እየገረመኝ ነው። አምባገነንነት። ደስ ይላል።
ደሞ አንዴ የራስ ልጓምህን ከለቀቅከው የሚይዝህ ይሉኝታ የሚባል ነገር አይኖርህም። እና ለጊዜው አምባገነንነትን በፌስቡክ እየተለማመድኩት ነው። ቢያንስ የዜግነቴን ታህል እንኳ ይድረሰኝ እንጂ?!!!
ግን ይሄ በትንንሹ የህይወታችን ነገሮች የምንለማመደው የአምባገነንነት ልምድና ልማድ ተጠረቃቅሞ፣ ነገ የትም ቦታ ብትሄድ እንደ አመል የሚከተለን እንዳይሆንም እሰጋለሁ።
እንግዲህ የማህበረሰብ አጥኚዎቻችን ለወደፊቱ የማህበራዊ ሚዲያዎች አምባገነናዊ ባህርይን በግለሰብና በማህበረሰብ ሰብዕና ላይ በመፍጠር ወይም በማፍረስ የሚጫወቱትን ሚና አረጋግጠው ይፋ እስኪያደርጉልን ድረስ፣ በበኩሌ ይሄን የፌስቡክ የአምባገነንነት ጉዞ፣ ደስ የሚል አደገኛ ጉዞ ነው። ግን ክፉ አመል ነው። ብዬ በይፋ አምኛለሁ። እመሠክራለሁ።
በተለይ ለአንዳንድ ሀሳብ ለተንጠፈጠፈባቸው፣ በወግ መነጋገርን ለማታስለምዳቸው፣ ከምክንያት ይልቅ ዘለው በስድብ ላይ ለሚንጠላጠሉ ከንቱዎች በትክክል ይበጃልና የሚፈልግ አይቦዝን። በአምባገነንነት መብቱ ይጠቀምበት። እርግፍ አድርጎ ስለመተው ወደፊት ይታሰብበታል። ላሁኑ ጥርግ ነው።
በመጨረሻ የፌስቡክ ጓደኞቼን የምመክረው ከደረጃችሁ ልክ ከወረደባችሁ አሊያም ካሻቀበባችሁ የፌስቡክ እድርተኛ ጋር አትለፋለፉ! ብዬ ነው። Sometimes it’s just a waste of energy. ከእናንተ አስተሳሰብ ጋር አብሮ የማይሄድላችሁን፣ ያቅለሸለሻችሁን ሀሳብ ተሸካሚ simply “unfriend” ወይም “block” ግጩት። በጣም ደስ ይላል። ይገላግላል። ትደሰቱበታላችሁ። ሁለታችሁም።
እኔንም በተመሣሣይ መንገድ አሰናብቱኝ ብዬ እጠይቃለሁ። ከምክንያት ውጭ ሆናችሁ በገፄ ላይ ከምትደነፉ፣ በቃ unfriend ግጩኝና አሰናብቱኝ። የሆንኩትን ነኝ። ያልሆንኩትን አልሆንም። አብሮ እየተለፋለፉ ከማይመስል ሰው ጋር ማዝገም ምንድነው?
ጥርግ ማድረግ ነው እንጂ!
በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን፣ አደራ፣ እንዳይለምድባችሁ።
ጣፋጩ አምባገነንነት።
ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን ይባርክ።