>

የዘረኞች ምክር በቃን (ዘምሳሌ)

የዘረኞች ምክር በቃን


ኧረ ጎበዝ ይብቃ  ዘረኝነት ይቅር
ሞትን ሙቶ መኖር በኢትዮጵያ ምድር
ሀገር ማፈራረስ  ህዝብን  በማሸበር
ንፁሃን ዜጎችን ከእስር ቤት መቀርቀር

ታሪክ በማፍረስ ሕዝብ  ነጠላችሁ
መሬት ስትቆርሱ  ስፍራ  እየለያችሁ
ያልነበረን ታሪክ እየፈጠራችሁ
ነዋሪን ከምድሩ  ያፈናቀላችሁ

ብሶት ስትፈጥሩ ብሶት ሰትዘሩ
ግፍ እየኖራችሁ ግፍን ስትጨምሩ
ጥላቻን ስትዘሩ  ብሔር ስታከሩ
የሌላውን ሰው ዘር ጉድጓድ ስትቆፍሩ

በተረኝነት ገድል ስንቱ ቆስሎ ደማ
ህይወቱም ተቀጥፎ በመንገድ ገለማ
በጦረኝነት ጀብድ  በከንቱ አላማ
ለስልጣን  ሹክቻው አንዱ አንዱን ሲቀማ

በጎሳ ክፍፍል የሰውልጅ ሲገደል
ካገሩ  ሲገለል በእምነቱ ሲቆስል
ወጣቱ ተመርጦ ከደጁ ሲቃጠል
ሲታረድ ሲቆረጥ ሲጨምር ከገደል

አመታት ነጎዱ ግማሽ ምእት ሆነ
የዘረኝነት ምክር ባገር ከሰፈነ
በአጥፊዎች ደጃፍ ይኼው ከገነነ
የዜጎችን ህይዎት በከንቱ እያጎነ

ተረኝነት ይብቃ ዘረኝነት ይቅር
ሞትን ሙቶ መኖር በኢትዮጵያ ምድር
ሀገር ማፈራረስ  በጥጋብም መኖር
ንፁሃን ዜጎችን ከእስር ቤት መቀርቀር
በሀር አፍራሽ ህግም  ሀገር ማስተዳደር
ኢትዮጵያን አስጥሉ  ካለችበት መኸር
በቃን በሉ  ጎበዝ  የዘረኞች ምክር!!

ዘምሳሌ

Filed in: Amharic