>
7:28 am - Tuesday August 9, 2022

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝና ኮሚቴዎቹ

በታሪኩ ደሳለኝ /ሚኪ

Temesgen Desalegn 04.12.2014ዛሬ ህዳር 25/07 ዓ.ም በህዝበ ሙስሊሙ ለተመረጡት መፍትሄ አፈላለጊ ኮሚቴዎች ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የመከላከያ ምስክርነቱን ሲሰጥ ውሏል፡፡ ሰሚት አካባቢ የሚገኘው ፍርድ ቤት ስንደረስ ከጠዋቱ 1፡30 ቢሆንም ሙስሊሙ ህብረተሰብ አካባቢውን ሞልቶት ነበር፡፡ ሴቶች በአንድ በኩል ወንዶች ደግሞ በሌላ በኩል ቆመዋል፡፡ የስነ-ስርዓት አስተባባሪ የሆኑት ወጣቶች በተራ ቁጥር የመግቢያ ትኬት እያደሉ ነው፡፡ የደረስንበትን ቁጥር ወስደን የመግቢያ ሰዓት እስኪደርስ ቆመን መጠባበቅ ጀመርን፡፡ አንዲት ነጭ ሚኒባስ የፍርድ ቤቱ ህንፃ ፊት ለፊት ስትቆም ሁላችንም ትኩረታችን ወደ መኪናዋ ሆነ፡፡ መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች ከመኪናው ወርደው መንገድ ካስለቀቁ በኋላ ተመስገን ደሳለኝ ከአንድ ዕስረኛ ጋር በካቴና ታስሮ ወረደ፡፡ በወቅቱም የደስታ ጉርምርምታ አካባቢውን ሞላው፡፡ ሁሉም ሰው ተሜን በፈገግታ ይመለከቱት ነበር፡፡ የህዝብን አስተሳሰብ እንደናወፀ ተደርሶበታል የተባለው ይህ ወጣት እንዴት እንዲህ ባለ መንፈስ አቀባበል ተደረገለት? 3፡00 ሲሆን የበሩን ፍተሻ በማለፍ ወደ አዳራሹ ለመግባት ስንሰለፍ እነዚያ ትሁት አስተናባሪዎች እናንተማ አትሰለፉም በማለት ከፊት አንድንገባ አደረጉን፡፡
ችሎት ተሰይሞ ምስክርነት መሰማት ጀመረ፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መጅሊሱ ላይ ተቃውሞ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ኮሜቴዎቹ እነዴት እንደተመረጡ የሚያውቀውን ለመብራራት ከሦስቱ ዳኞች ፊት ተሰየመ፡፡ መጅሊሱ ዕኛን አይወክለንም፣ አህባሽ በግድ እየተጫነብን ነው፣ የአወሊያ ት/ቤት በቦርድ ይተዳደር የሚሉትን ሦስቱን ጥያቄዎች ሠላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ እንደጠየቁ አግባብነት ባለው ቋንቋ አስረዳ፡፡ ይሄንንም ጉዳይ ከፍትህ ጋዜጣ ጀምሮ በአዲስ ታይምስ፣ መፅሄት፣ በልዕልና ጋዜጣና በፋክት መፅሄት በሰፈው ትንታኔና ዘገባ እንደሰራ ተናገረ፡፡ ችግሩ ይቀል ዘንድም የመፍትሄ ሀሳቦችን እንዳቀረበ መሰከረ፡፡ በተመስገን ቃሎች መካከል የመስማማት ሹክሹክታ ከታዳሚው ይሰማ ነበር፡፡
ተመስገን ምስክርነት ሲሰጥ ካነሳቸው ሀሳቦች መካከል በጥቂቱ፦
– ጥያቄዎቹ ከሦስት ወደ አራት ያደገው በመንግስት የግፍ እርምጃ ሲሆን እርሱም ‹ኮሜቴዎቹ ይፈቱ› የሚለው ነው፡፡
– በአወሊያ ትምህርት ቤት የተደረገው ተቃውሞ በአንድ ቀን የፈነዳ ሳይሆን 23 ዓመት ሙሉ ሲንከባለል የቆየ ነው፡፡
– ኢህአዴግ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖትን ለስርዐቱ መገልገያነት አውሏቸዋል፡፡
– ይሄ ስርዐት በዕስልምና ሀይማኖት ላይ ጭፍለቃ አድርጎል፡፡
– አህባሽን ለመስተማር ከሊባኖስ የመጡ የሀይማኖት ሰው እንደነበሩና የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትሩም በመንግስት እስፖንሰርነት አስተማሪው መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
– መጅሊሱ ተናገረ ማለት ኢህአዴግ ተናገረ ማለት እንደሆነ
– ሙስሊሙ ህብረተሰብ የኢድአልአደሀን በአል ሲያከብር ፖሊስ ሲደበድባቸው አንዳችም መልስ ሳይሰጡ በሰላም ሲሄዱ እንዳየ በመናገር ተያያዝ ምሳሌን ተናግሯል፡፡ የመፍትሄ አፈላለጊው ኮሜቴ የጥምቀት ባአል ዕለት ሪፖርቱን አቅርቦ ሲጨርስ ከኮሜቴዎቹ አንዱ የሆነው ነው ካሚል ሸምሹ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ታቦት አስገብተው የሚመለሱበት ሰዓት በመሆኑ እዚሁ ቆይተን፤ እነሱን አስገብተን እንወጣለን ማለቱ ምን ያህል ሰላማዊ እንደሆኑ ያሳያል ብሏል፡፡
– እስላማዊ መንግስት ሊመሰርቱ ነው የሚለውን ነገር ሬድዋን ሁሴን ለሰንደቅ ጋዜጣ ከሰጠው ኢንተርቪ ላይ ማንበቡንና መሰል ጉዳዮችን በሰፊው ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
ተመስገን ምስክርነቱን በሚያሰማበት ወቅት አቃቤ ህግ መስቀለኛ ጥያቄዎችን እያቀረበ ነበር፡፡ እንደምሳሌም ‹እያንዳንዱን ጉዳዮች ዘግበናል፤ ትንታኔም ሰርተናል ብለሀል፡፡ ሁከት ሲያነሱስ ዘግበሀል?› ተመስገንም ‹በመጀመሪያ ሁከት ሲያነሱ አላየሁም፡፡ ሁከት የተባለውን ነገር መንግስት ባለው ሚዲያ ሁሉ ሲዘግበው ነው የሰማሁት›በማለት ተናግሯል፡፡
ዳኛው በበኩላቸው ‹ሬደዋን ሁሴን እስላማዊ መንግስት ሊመሰርቱ ነው ማለታቸው ለምን ይመስልሀል?› ሲሉ ጠየቀዋል፡፡ ተመስገንም ‹ሬደዋን ራሱ ከጨፍላቄዎቹ አንዱ በመሆኑ ነው› በማለት መልሷል፡፡ (ኮሜቴዎቹና በአዳራሹ የተገኙ ሰዎች በዚህ መልስ የረኩ ይመስላሉ፡፡ ይህን ለመናገር ከመልሱ በኋላ የተሰማው ድምፅ ምስክር ይሆነኛል)
ዳኛው ተመስገንን ከየት እነደመጣ ጠይቀውት ከዝዋይ እስር ቤት መሆኑንና የታሰረውም በጋዜጠኝነት ሞያው በፃፋቸው ፅሁፎች እንደሆነ ገልፃል፡፡ በዚህም የተመስገን የምስክርነት ቃል ማሳረጊያውን አግኝቷል፡፡
በአሳሪዎቹ እጅ ላይ እንኳን ሆኖ የሚቀውን፣ የእምነቱንና የእውነቱን ለመናገር ወደኋላ የማይለው ተመስገን በእውነት ስለእውነት መስክሮ ሲወጣ ወደ ህዝቡ ዞሮ እጁን ለሠላምታ አነሳ፡፡ እነሱም አፀፋውን በዕጥፍ መልሰው በክብር ወደ እስር ቤት ሸኙት፡፡ አጠገቤ ተቀምጠው ከነበሩት መካካል በእድሜ ትልቅ የሆኑ አንድ አባት ተመስገን ሲወጣ ከጀርባው በኩራት እያዩት ‹በእስር ቤትም ሆነህ እውነትን ያላረከስክ፤ አንተ ለኛ እንደቆምከው አላህ ለአንተም ይቁምልህ› በማለት የስንበት ቃል አሰምተዋል፡፡ ባይሰሙኝም እኔም አሜን አልኩኝ፡፡

Filed in: Amharic