>
3:19 am - Tuesday December 7, 2021

መረጃና ማስረጃ [ኤርሚያስ ለገሰ]

Ermias Legesseከእለታት በአንዱ ቀን ዳኝነት የሚባል የአዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረባ ብዙ ማይሎች አቆራርጦ እቤቴ መጣ። በጣም ጥሩ ጊዜም አሳለፍን። ባለቤቴ አፍልታ የሰጠችን ቡና ከእስታር ባክስ ደብል እስፔሬሶ እንደሚያስንቅ ከቤቴ ሳይወጣ ምስክርነቱን ሰጠ። የተቀጣጠርነው በመጵሀፌ ዙሪያ ልናወራ በመሆኑ ብዙ ሰአት ፈጅተን አወጋን። ዳኝነት የሚገርም እይታ ነበረው። ነገሮችን እንደ ዶሮ እየበለተ ይመለከታል ።ያቺ ያልታደለች ሀገር ስንትና ስንት ብርቅዬ ልጆቿን አጥታለች? …ይሁን እስቲ!
ከዳኝነት ጋር በነበረን ቆይታ የተናገረው አንድ ቁምነገር ትልቅ ቦታ ሰጥቼዋለሁ። እንዲህ ነበር ያለው፣
” የምናውቀውን ነገር ስጋ አልብሰህ አሳየኸን። ማስረጃም መረጃም አድርገን የወሰድነው ጉዳዩን በደንብ ስለምናውቀው ነው ። በእርግጥ ከአንተ መጽሃፍ በኃላ የወጣው የገብሩ አስራት መፅሐፍ የአንተን የሚያዳብር ነው ” የሚል ነበር።
( በነገራችን ላይ Emi Solomon የምትባል ትንታግ ኢትዬጲያዊት ተመሳሳይ ይዘት ያለው አስተያየት አስፍራ ተመልክቻለሁ…ምስጋናዬን በጐን በኩል ልኬያለሁ።)
እናም ከዛ በኃላ መረጃን ከማስረጃ ማዋደድ አንዱ ስራዬ ሆነ። ደግነቱ የድሮ ጓደኞቼ የመሰረቱትና ራሱን ” ኢህአዴግ” ብሎ የሚጠራው “ጉርና ሆድ ማሰሮ” ከስሩ ተሾንቁሯልና የፅሑፍ ብቻ ሳይሆን የአንደበት ማስረጃም እያፈሰሰ ነው። ምስጋና ይህን ከባድ መስእዋትነት እየከፈላችሁ ላላችሁ የኢትዮጵያ ልጆች። ምስጋና ” ለእኔ የሆነው ኢሳት”… ኢትዮጵያ ዉለታ አትረሳምና…
በመሆኑም ዛሬ ከወደ አምስተርዳም የተላለፈው የድምፅ ማስረጃ ልተላለፍ። ዜናው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር የሁሉንም ክልሎች የፀጥታ ጥምር ኮሚቴ ሰብስቦ በሚስጥር የሚዶልቱትን ሴራ የሚያጋልጥ ነው። እንደዚህ አይነት ስብሰባዎችን ለአራት ያህል ጊዜያቶች ተሳትፌያለሁና አሰራሩ እንዴት እንደሆነ መጠነኛ መንደርደሪያ ሰጥቼ ወደ ነጥቤ ልግባ።
ስራው ይጀምር የነበረው ከኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ሰብስቦ ባጠናቀረውና ራሱን የፀጥታው ምክርቤት ብሎ ለሰየመው አካል ሪፖርት በማቅረብ ነበር ። ይህ የፀጥታ ምክርቤት በህግ ያልተደራጀ ለአንዳንድ ሚኒስትሮች ሳይቀር ድብቅ የነበረ ስውር ቡድን ነበር።
( በአንድ ወቅት ለግርማ ብሩ ምክርቤቱ የወሰነውን ንገረው ተብዬ ቢሮው ስሄድ ” የምን ምክርቤት ነው?” በማለት አመናጭቆኝ ነበር። ትእግስት አድርጌ ” የምክር ቤቱ ሲያሰኘው ፀጥታ፣ ሳያሰኘው ደግሞ ኮሙዩኒኬሽን ይባላል። ሰብሳቢው አቶ መለስ ሲሆን አባላቶቹ ጓድ በረኸት ፣ ጓድ አባይ ፣ጓድ ስዩም( ውጭ ጉዳይ) ፣ጓድ ኢሳያስ ( ደህንነት)፣ ዶክተር ሽፈራው፣ ኦቦ ሙክታር ( ኢህአዴግ ቢሮ) ናቸው” በማለት ለማስረዳት ጥረት አድርጌያለሁ ።
( እርግጠኛ ባልሆንም ከአቶ መለስ ግብአተ መሬት በኋላ የፀጥታው ምክርቤት ስራ ላይ ያለ አይመስለኝም ። ቧልት ካልሆነ በስተቀር ጋሽ ሀይሌም፣ ጋሽ ሐይሌ ናቸው። ጓድ ሬድዋንም ፣ጓድ ሬድዋን ናቸው!!)
ያም ሆነ ይህ ምክርቤቱ (“ድርጅቱ”) ትእዛዝ የሚሰጥባቸውን ተከትሎ የፌደራል ጉዳዬች የሁሉንም ክልል (አዲስአበባ እና ድሬደዋ ጨምሮ) የፀጥታ ጥምር በየሩብ አመቱ ሜክሲኮ በሚገኘው ፌዴራል ፓሊስ ይጠራል። ጥምር ኮሚቴ የሚባለው የየክልሎቹ ፀጥታ ዘርፍ ሃላፊዎች ፣ የፓሊስ አዛዦች ፣የመከላከል አዛዦች ፣የደህንነት ሃላፊዎች ናቸው። በነገራችን ላይ የሁሉንም ክልል የመከላከል ሃላፊዎችና የደህንነት ሃላፊዎች የሚመደቡት በአባይ ፀሐዬ ነው። የሩብ አመቱን የሚገመግመው ዶክተር ሽፈራው ሲሆን ፣ የአመቱን እና ግማሽ አመቱን አባይ ፀሐዬ ነው። የግምገማው ክብሪቶች ( አውጫጪዎች) የፌደራል ፓሊስ ፈላጭ ቆራጭ የሆኑት ታጋይ ግርማይ ማንጁስ ፣ ታጋይ መውጫ እና ታጋይ ኢሳያስ ወ/ ጊዬርጊስ ናቸው።

ጥምር ኮሚቴው በየጊዜው የሚገመግማቸው ነጥቦች የተወሰኑ ናቸው። የመጀመሪያውና ሰፊ ሰአት የሚወስደው የሐይማኖት ጉዳይ ነው። የሐይማኖት መሪዎቹን መመልመል፣ ሰርጐ መግባት፣ ፀረ ኢሕአዴግ የሆኑትን መለየት፣ ሀይማኖቶቹን በደረጃ መፈረጅ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ከሐይማኖት ተቋማቸው ጋር ያላቸው ግንኙነትና ተሳትፎ ፣ተከታዬቻቸውን መሰለል፣ በስጋታቸው መጠን ደረጃ ማውጣት፣… ወዘተ ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ናቸው። እነዚህ ነጥቦች በዝርዝር ቢቀመጡ ራሱን የቻለ መጽሃፍ ይወጣቸዋል። በመሆኑም ለዛሬ ( እንዳላሰለቻችሁ!) በአንዱ ላይ ብቻ ላተኩር።

የሐይማኖት ተከታዬችን እንዴት እንደሚፈረጁና ደረጃ እንደሚወጣላቸው።

የሁሉም ሐይማኖት ተከታዬችና አመራሮች አራት ደረጃ ይወጣላቸዋል። የመጀመሪያውና “ኤ” ፍረጃ የሚሰጣቸው የኢህአዴግ አባላት ሆነው በየደረጃው የሚገኙት ምክርቤቶች አባላት የሆኑ፣ ስለሀይማኖታቸው ደንታ የሌላቸው፣ ሃይማኖታቸውን የሚያስቀድሙትን እየሰለሉ መረጃ የሚሰጡ፣ በምክር ቤት ካባ በየስብሰባው እየተገኙ ክፍያ በመቀበል የማስፈራራት ስራ የሚሰሩ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በየወረዳው እስከ አምስት መቶ የሚደርሱ ሲሆኑ እጅግ ኃላቀሮችና ሆዳሞች ናቸው። የአስመሳይነት ባህሪ ስላላቸው ጥቅማቸው የተቋረጠ እለት ከኢህአዴግ በተቃራኒው “( ሰለሞን ተካልኝ in my mind)
ሁለተኛው ደረጃ ” ቢ” የሚሰጣቸው ሆኖ የልባቸውን በልባቸው ይዘው እንደ እስስት የሚቀያየሩ ናቸው። የኢህአዴግ ደጋፊ ነው ብለው የሚያስቡት ሰው ከተመለከቱ እንደነሱ ኢህአዴግ የለም። ” በጣም ጥሩ እየሰራችሁ ነው፣ ከጐናችሁ ነን፣ እከሌ አክራሪ ይመስለኛል በደንብ ተከታተሉት…” በሚሉ ቃላት ሀብታሞች ናቸው። ከገዥው መደብ ተቃራኒ ሰው ሲያገኙ በአንድ ጊዜ ተከርብተው ወደ ማማት ይሸጋገራሉ ። እነዚህ ሐይሎች አንጻራዊ በሆነ መልኩ ፊደል የቀመሱና የመንግሥት ስራ ተቀጥረው የሚሰሩ ናቸው።
ሶስተኛው ፍረጃ ” ሲ” የሚባል ሲሆን ለኢህአዴግ ከፍተኛ ጥላቻ ያላቸው፣ ሀይማኖታቸው መደፈሩን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ በዚህ ምክንያት እርር ትክን የሚሉና አንገታቸውን ለሰይፍ ለመስጠት የተዘጋጁ ናቸው። እነዚህ ሐይሎች በአብዛኛው የተማሩ፣ ማስተባበር የሚችሉ ናቸው። አብዛኛው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች እዚህ ፍረጃ ውስጥ ይገባሉ።
አራተኛው ” ዲ “ የሚል ፍረጃ ሲሆን ከ” ሲ ” ጋር ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸው ሲሆኑ ከሀይማኖታዊ ቀናኢነታቸው በተጨማሪ የተቃዋሚ ፓለቲካ ድርጅት አባል/ ደጋፊ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ” በወንጀል የሚጠየቁ” ሊስት ውስጥ ያሉ ሲሆን ፣በሀገሪቷ ግርግር ይነሳል ተብሎ ከተገመተ በየቤቱ እየተለቀሙ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ የሚታሰሩ ናቸው።
( በምርጫ አደረጃጀት ስለሚኖረው ፍረጃ ለማንበብ የመለስ ትሩፋቶች መጽሃፍን ከገጽ 166 -169 ይመልከቱ ። መጽሃፉ በእጃቸው ለሌላ ሰዎች ወዳጆቼ በመፃፍ ተባበሩኝ። Nati, Anani Le Ethiopia, …)

ይህን አጠቃላይ ስእል ከሰጠሁ ዘንዳ ወደዛሬው አጀንዳ ልመለስ። ጋዜጠኛ አፈወርቅ አግደው ስላሰማን ዜና። የአዲሳባ ፓሊስ ባልደረባው ኮማንደር ያቀረበው ሪፓርት ።( የኮማንደሩ ስም ባይጠቀስም እጅግ በጣም እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው ስሙ መኮንን ነው። ለመረጃ ያህል ይህ ኮማንደር በምርጫ 97 ግርግር ወቅት አዛዥ ሆኖ በሚሰራበት ላፍቶ ክፍለከተማ ከክፍለከተማው ከንቲባ ከነበረው ሐይሌ ፍስሐ ጋር ወጣቶችን እየለቀመና ጨርቅ እየጠቀጠቀ ሲገርፍ የነበረ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በመሬት ወረራው በግንባር ቀደምትነት በመሳተፍ ከአምስት መሬት በላይ እንደወሰደ የዛ አካባቢ የበታች ካድሬዎች ይመሰክራሉ ። )
እናም ኮማንደር መኮንን ” ብገልፀውም እርስ በራስ ስለሆንን ችግር የለውም” በማለት ከተገለፀው ውስጥ ከፊሉ እንዲህ ይላል፣
133,743 የህብረተሰብ ክፍል በፀረ አክራሪነት ትግሉ ላይ የተሳተፈና የተፈረጀ ነው። በዚህም ከ A እስከ D የመፈረጅ ስራ ተሰርቷል። በዚህም መሰረት በ”ኤ “ደረጃ 48,855፣ በ” ቢ ” ደረጃ 75,930፣ በ” ሲ ” ደረጃ 8,093፣ እንዲሁም በ” ዲ ” ደረጃ 865 ናቸው። ይሄ ፍረጃ ከተደረገ በኋላ ህብረተሰቡ አሁንም ” የፀረ አክራሪነት ንቅናቄ ኮሚቴው ” በቀጠና እና መንደር ስለሆነ ይህን በግል እርስ በራስ በማገማገም የማስተካከል ስራ ሰርቷል ።በተለይም C እና D የተፈረጁትን። በዚህ መሰረት ከ D ወደ C 52፣
ከ C ወደ B 4,440 ፣ ከ B ወደ A 7,980፣ ተሸጋሽገዋል። በአጠቃላይ ሽግሽግ የተካሄደው 12,490 ሰው ነው። ራሳቸውን የማረም ስራ በህብረተሰቡ ሙሉ ተሳትፎ ተሰርቷል ።”
እንግዲህ ከዚህ የኮማንደር ሪፓርት ብዙ ነገሮች መዞ ማውጣት ይቻላል ። ህብረተሰቡን እርስ በራስ እንዴት እያበላሉት እንደሆነ፣ ዜጐች እንዴት ተሸማቀው እየኖሩ እንደሆነ፣ ዜጐች ያለፍርድ ቤት ውሳኔ ፍርድ እየተሰጣቸው መሆኑ፣ ከ50 ሺህ ያላነሰ የምክር ቤት አባል እንዴት ለአፈና ስርአቱ እያገለገለ እንደሆነ… ወዘተ።
ታዲያ ማን ማድረግ ይቻላል?
ቢያንስ በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች ቢያንስ አራት ነገር ማድረግ የሚችሉ ይመስለኛል ። የመጀመሪያው መንግስት በሐይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እየገባ መሆኑንና የራሱን ሕገመንግሥት እየጣሰ መሆኑን ሙሉ ሪከርዱን በመያዝ ፍርድ ቤት መሄድ። ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ፍርድቤት ምንም ወሰነ ምንም!!… ሁለተኛ ለአለም አቀፍ ተቋማት፣ ኤምባሲዎች ፣ለሀይማኖት ነጳነት ተሟጋቾች እየተረጐሙ እንዲደርስ ማድረግ ። …ሶስተኛ ለሀይማኖት ተቋማቱ አመራሮች ( ሲኖዶስ ፣መጅሊስ፣ ቦርድ…) የመንግስት ድርጊት በእነሱ እውቅና እየተፈፀመ መሆኑን መጠየቅ፣ ካልሆነ መንግሥትን እንዲከሱና እንዲያወግዙ መጠየቅ።…አራተኛ አማኞች መንግስት እየሰራ ያለውን በተጨባጭ መረጃ እንዲገነዘቡ ማድረግ። ይህ ተቃዋሚዎች ከተቋቋሙበት አንዱ አላማ ነውና ተጨባጭ የተግባር እንቅስቃሴ ይጠበቅባቸዋል ።
ከምንወዳት ሀገራችን በርቀት የምንገኝ ዜጐች የሀይማኖቶቻችን መደፈር እንቅልፍ እንዳላስተኛን ይታወቃል። መቆጨት ብቻውን በቂ አይደለምና ወደ ፈጣን ተግባር መግባት ይኖርብናል ። በየሃገሩ ባሉና በሲኖዶሱ ለሚተዳደሩ አብያተክርስቲያናት ምላሻቸውን እንዲሰጡ እና ድርጊቱን እንዲያወግዙ ጫና ማሳደር ይቻላል። ወደ ፍርድቤት ለመሔድ ዝግጁነት ያሳዩ የፓለቲካ ድርጅቶችን በፉይናንስና ሞራል መደገፍ ያስፈልጋል ። በስደት ለምንኖርበት ሐገራት መረጃውን መስጠት ያስፈልጋል ።
መንግሥት ንጹሃንን አስሮ ራሱ ወንጀል እየሰራ መሆኑን ማጋለጥ ጊዜ የማይሰጠው ወቅታዊና አንገብጋቢ አጀንዳ ሆኖ ከፊታችን ተደቅኗል።
እነ አቡበከር ይፈቱ!!
እነ አንዷለም ይፈቱ!!
እነ ፍቄ ይፈቱ!!
እነ በቀለ ይፈቱ!!
እነ እስክንድር ይፈቱ!!
ሁላችንም እንፈታ!!

Filed in: Amharic