>

ኦባሳንጆ ለአፍሪካ ህብረት የጸጥታው ምክር ቤት በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ገለፃ አደረጉ (ደመቀ ከበደ)

ኦባሳንጆ ለአፍሪካ ህብረት የጸጥታው ምክር ቤት በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ገለፃ አደረጉ
(ደመቀ ከበደ)


ህብረቱ ዛሬ ጥቅምት 29 ቀን 2014 ዓ/ም አስቸኳይ #ዝግስብሰባ አካሂዷል፡፡ ስብሰባው በበይነ መረብ የተካሄደ ነው፡፡
በስብሰባው የህብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ፣ የህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴገን ኦባሳንጆ፣ በአፍሪካ ህብረት የግብጽ ቋሚ ተወካይ መሃመድ ጋድ እና በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ተሳትፈዋል፡፡
ስብሰባው የተካሄደው በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምክርና የአፍሪካ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴገን ኦባሳንጆን ገለጻ ለማድመጥ ነበር፡፡
ይህንንም የምክር ቤቱ የአል ዐይን አማርኛ የመረጃ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሲሰበሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
ህብረቱ በምስራቅ አፍሪካ የተለያዩ ሀገራት ያጋጠሙ የጸጥታ ችግሮችን እንዲያሸማግሉ የወከላቸው ኦባሳንጆ ትናንት ወደ ትግራይ አቅንተው በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር መወያየታቸው ተሰምቷል፡፡ አቶ ጌታቸው ረዳን መሰል የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችም ይህንኑ አሳውቀዋል፡፡
በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ በተሳተፉበት በዚህ ስብሰባ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከመከረና የኦባሳንጆን ገለጻ ካደመጠ በኋላ ያለው ወይ ያስቀመጠው ቀጣይ አቅጣጫ እንዳለ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱ የተሰበሰበበትን ጉዳይ የተመለከተ መግለጫን እንደሚያወጣ ለአል ዐይን ገልጿል፡፡
Filed in: Amharic