>

አቢይ መራሹ የብልጽግና መንግስት ከወያኔ ጋር ሁለንተናዊ ድርድር ጀመረ -ዲፕሎማቶች የስምምነት ተስፋ አለ ይላሉ! *** ወንድወሰን ተክሉ

አቢይ መራሹ የብልጽግና መንግስት ከወያኔ ጋር ሁለንተናዊ ድርድር ጀመረ -ዲፕሎማቶች የስምምነት ተስፋ አለ ይላሉ!
 ወንድወሰን ተክሉ

 የብልጽግና እና ወያኔ ድርድር –
የአቢይ መራሹ ብልጽግና ከትህነግ ጋር እያደረገ ያለውን ድርድር ወደ ስምምነት ደረጃ  ላይ እንደ ደረሰ ምንጮቻችን ይገልጻሉ።
ምንጮቹ የአቢይ መንግስትና የትግራይ መንግስት ወደ ስምምነት ደረጃ እየተቃረቡ ነው ብለን እንድንናገር የሚያስችሉ የአቌም መሻሻሎችን በሁለቱም በኩል አይተናል ብለዋል። ይህ የተሻሻለው አቌም ምን እንደሆነ ለመግለጽ አልፈለጉም።
በብልጽግና ቡድን እና በትህነግ በኩል ለስምምነት ያበቃውን ወሳኝ ነጥብ ፓርቲዎቹ እራሳቸው የሚገልጹት ይሆናል በማለት እነዚህ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ተናግረዋል።
ሆኖም በርካታ አማራዊያን ድርድሩ ከአማራና አፋር ክልል መንግስታት እውቅና ውጪ እየተፈጸመ ያለ ምስጢራዊ ድርድር ስለሆነ ውጤቱ ጥሩም ሆነ መጥፎ የሁለቱን ክልል ህዝብ አይወክልም በማለት እያስተጋቡት ያለውን ጉዳይ ለማጣራት የዲፕሎማቲክ ምንጫችንን በድርድሩ ላይ የሁለቱን ክልል መንግስታት እውቅና ያለው ድርድር ስለመሆ አለመሆኑ ይነግሩን ዘንድ ላቀረብነው ጥያቄ የድርድሩ ዋና አላማ በሀገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን አስከፊ የእርሰበርስ ጦርነት በሰላም ለምፍታት ያለመ በመሆኑና ሁለቱ ክልሌች ደግሞ በጦርነቱ ሰለባነትና ተሳታፊነት ከመንግስት ቀጥሎ ትልቁን ድርሻ የያዙ ስለሆነ እነሱንም ያካተተ ነው በማለት ከገለጹ በኋላ በድርድሩ ዝርዝር ነጥቦች ላይ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በአፍሪካ ህብረት የተወከሉት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጎን አባሳንጆ ከተመድ ተወካይ ማርቲን ግሪንፊትዝ ጋር በመሆን ወደ ትግራይ መቀሌ በመጔዝ ከዶ/ር ደብረጺዮን እና ባለስልጣናቱ ጋር ውይይት በማድረግ ላይ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን የመንግስት ቃለ አቀባይ አቶ ሬድዋን ሁሴን «መንግስት የኦሊሴጎን አባሳንጆን መልስ በመጠባበቅ ላይ ነው» በማለት ይህንኑ ድርድር ሁኔታ ሲገልጽ የትህነጉ ጌታቸው ረዳ በበኩል ከመሸ በኋላ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደብረጺዮን እጅግ ደስ የሚልና ውጤታማ የሆነ ውይይት ከናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ኦሊሴጎን አባሳጆ ጋር አድርገዋል በማለት እየተካሄደ ያለውን ድርድር አረጋግጧል።
ሆኖም ከሁለት ቀናት በፊት የፍትህ ምኒስትሩ ዶ/ር ጢሞቲዎስ ወያኔ በሃይል ከያዛቸው የአማራና የአፋር ግዛቶች ለቅቆ ካልወጣ መንግስት ከወያኔ ጋር አይደራደርም በማለት ለቪ ኦ ኤ ከገለጸው አቌም ጋር እጅግ በተቃረነ መልኩ የአቢይ መንግስት የአማራና የአፋር ግዛቶች በወያኔ ወረራ ስር ባሉበት ሁኔታ ከአማራ ክልል ብአዴን በኩል አቶ ደመቀ ሞኮንን አቶ ተመሰገን ጥሩነህ ሙሉ ተሳታፊ በሆኑበት ደረጃ ድርድሩን እያካሄደ እንደነበረ ነው ዛሬ ላይ ያገኘንው መረጃ እሚያመለክተው።
 የድርድሩ አጣዳፊነት
የአቢይ መራሹ መንግስት በወያኔ ያላይ ያለውን አቌምና ውሳኔን የለወጠው ወያኔን ማሸነፍ አቅቶት ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ካስወጣበት ግዜ ጀምሮ እንደሆነ የሚገልጹ ጭምጭምታዎች የሚያስረዱ ሲሆን ትልቁ ተቃዋሚና የአቢይን አዲስ አቌም አልቀበልም ያለው የኢሳያስ አቌም ለአቢይ እንደ ትልቅ  እንቅፋት ሆኖ እንዳስቸገረ ይገልጹና በአማራ አመራሮች በኩል ከሙሉ ትብብር በስተቀር ተቃውሞ እንዳልቀረበ ይናገራሉ።
ሆኖም የመከላከያው በትግራይ ተመትቶ ከትግራይ መውጣት የአቢይን ወያኔ ሙሉ በሙሉ መጥፋት አለባትን ቀደም ብሎ ከኢሳያስ ጋር የተስማማበት ውሳኔያዊ አቌም እንዲለውጥ ያስገደደው ቢሆንም ለዛሬው አጣዳፊያዊ የድርድር ሂደት ላይ እንዲደርስ ያስገደደው ግን ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በኩል ከቀረበለት ተጽእኖ ይልቅ በጦር ግንባሮች የደረሰበት ከባድ ወታደራዊ ሽንፈት ጫና ውጥረት ውስጥ እንዳስገባውና ስልጣናዊ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን በግልጽ ያየበት ሁኔታ ለድርድሩ ትልቁን አስተዋጾ አድርጋል ይላሉ።
የትህነግ ደሴ ኮምቦልቻና ከሚሴ መድረስ በኋላ የአቢይ መንግስትና የአማራ ክልል መንግስት የተናጥልና የጋራ ክተት ጥሪ ዘመቻ ያወጁ ሲሆን ለጥቆም የፌዴራሉ መንግስት ለስድስት ወር የሚጸና የአስቸኴይ ግዜ አዋጅ በማወጅ መላው የኢትዮጲያ ህዝብ የግል መሳሪያውን ይዞ እንዲዘምትና ለቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት በሙሉ የጥሪ ግባዣን ከማስተላለፍ ጀምሮ ባህር ዳር ላይ «የወያኔን ሀገር የማፍረስ ዘመቻን በመደበኛ ወታደራዊ አደረጃጀት መቀልበስ ስለማይቻል ጦርነቱን ህዝባዊ ጦርነት ማድረግ ይገባል» ብሎ እሰከመግለጽ በደረሰበት ሂደት ውስጥ የብልጽግናን መንግስት ወታደራዊ ሃይል ሚዛን ተንኮታኩቶ መዛባትን ያየንበት ሆኖ ነው የሚታየው።
በጦርነት ግንባር ከባድ ሽንፈት የገጠመው የብልጽግናው መንግስት በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የተፈጠረው አመጽ እና የሰራዊቱ አብዛኛ ክፍል አምጾ መፍረስ አቢይን እንቅልፍ ነስቶ ወደ ድርድሩ እንዲያማትር አድርጎታል ብለን እንድንገምት ያደርገናል።
በወሎ ግንባር ያለው የመከላከያ ሰራዊት ሙሉ በሙሉ መፍረስ ይህ ጸሀፊ ባለፈው ሳምንት የገለጸው ጉዳይ ሲሆን የወያኔን ወደ አዲስ አበባ ግሥጋሴን ለማስቆም አቢይ የግል ጠባቂዎቹን ሪፐብሊካን ጋርድ የሚባሉትን እስከመላክና በጦርነቱም አብዛኞቹ የመደምሰስና የመማረክ እጣ እንደገጠማቸው ምንጮቼ ገልጸዋል።
ከእነዚህ የሪፐብሊካን ጋርድ ውስጥ የአቢይ አህመድ የግል ጠባቂ /ቦዲጋርድ በመሆን ቤተመንግስት የነበሩና በየሚሄድበት አብሮ በመጋዝ የሚታወቁ ጭምር ተማርከው በወያኔ እንዳሉ ማረጋገጥ የቻልኩ ሲሆን በአዲስ አበባ ዙራያ በደቡብና በወለጋ መጠነ ሰፊ ግዛት ውስጥ በግልጽና በይፋ መቆጣጠርና መንቀሰቃስ የቻለው የኦነግ ጦር የፈጠረበት ስጋት የወያኔንና ኦነግን ወደ አዲስ አበባ ግስሴን በጦር ኋይል ማስቆም አልችልም ብሎ እንዲያስብና እንዲያምን አድርጎታል ብለን እንድንገምት ካላደረገን  በስተቀር ከአሸባሪ ጋር አንደራደርም፣ በወረራ ከተያዘው የአማራና የአፋር ግዛት ካልወጡ አንደራደርም እያለ የአስቸኴይ ግዜ አዋጅ አውጆ የክተት ጥሪ የወጀ ሰው ድንገት ከወያኔ ጋር እየተደራደረ ነው የሚል መረጃን ከመንግስት ሳይሆን ከውጪ ዲፕሌማቶች በኩል መስማት አስደንጋጭ ይሆንብናል።
የአማራ እጣፈንታ
እንደ የዲፕሎማት ምንጮቼ  መረጃ ከሆነ በአቶ ደመቀ ሞኮንን በእቶ ተመስገን ጥሩነህና መሰል የድርድሩን ሂደት ውስጥ መሳተፍን ሁኔታ በመመስረት የክልሉ መንግስት ስለድርድሩ በቂ መረጃና ተሳትፎም አለው ብሎ በድፍረት መግለጽ ቢቻለኝም የተሳትፎውን መጠንና የመደራደሪያ ነጥቦችን መስጠት መቻል አለመቻሉን ማወቅ አልተቻለም። ሆኖም እስካሁን በእጃችን በገቡ መረጃዎችና ብሎም ምድር ላይ ከተፈጠሩት ክስተቶች አንጻር  መገመት የምንችለው የአማራ ክልል መንግስት ማለትም ብአዴን የወሎን ህዝብ እጣፈንታ ላይ ግልጽ የሆነ ክህደታዊ ቁማር እየቆመር ስለመሆኑ ከግምት በላይ በሆነ ሁኔታ እስረግጦ መናገር ይቻላልና ብአዴንና አለቃው ብልጽግና ወሎን በምን መልኩ እንደሸጠ ዝርዝሩን ማቅረብ ባንችልም ስለመሸጡ ግን በእርግጠኝነት መግለጽ ይቻላል።
ይህንን የወሎን አማራ ለሽያጭ ያቀረበ ድርድር ነው እንድንል ካደረገን በርካታ ነጥቦች ውስጥ ሁለቱን ብቻ መጥቀስ በቂ ሆኖ አይተነዋል።
እነዛህም ሁለት ነጥቦች ፦
፨ 1ኛ – በወሎ ግንባር ያለውን አጠቃላይ የውጊያውን ሂደታዊ ሁኔታ-ማለትም ከምእራቡ የአማራ ግዛት የጎንደር ግንባር ጋር በንፅር ስናየው የወሎው ግንባር ላይ የመከላከያው ሚና ምን ያህል ለወራሪው ወያኔ ያደለ ሆኖ መገኘትና በዚህም የመከላከያው ሁለንተናዊ ትብብር የወያኔ በቀላሉ ከሚሴ መድረስ መቻል።
፨ 2ኛ – የፋኖ ተዋጊዎችን ወደ ወሎ እንዳይዘምቱ አግዶ ወሎ በአጠቃላይ በተያዘ ሳምንት የመንግስት ሙሉ በሙሉ ወደ ድርድሩ ዘሎ መግባትን ገዳይ በዋነኝነት ይጠቀሳል።
ይህንን የወሎን አማራ አሳልፎ በመሸጥ ለመደራደሪያነት መጠቀም ደረጃ በግንባር ቀደምትነት አቢይና ብአዴን ስም ሲገለጽ አብሮ መጠቀስ ያለበት አብን ድርጅትና አመራሮቹም በዚህ ክህደታዊ ተግባር ላይ የመሳተፋቸውን ሚና መገለጽ ይገበዋል።
ይህ ከላይ የተዘረዘረው በሙሉ የመንግስታዊው የብልጽግና ጎራ ዘንድ የሚታወቅ ሂደትን ሲሆን ሰፊው የአማራ ህዝብም ሆነ አጠቃላዩ የኢትዮጲያ ህዝብ ግን ይህንን ሁኔታ የሚያውቅ መሆን ይቅርና ወያኔ የምትባል ጭራቅ ከምድረ ገጽ እስክትጠፋ ጦርነት ይቀጥላል -የአቢይ መንግስት ይህንን ዘመቻም በመምራት ለድል ያበቃናል በሚል እምነት ለቀረበለት ክተት ጥሪ ዘመቻ ምላሽ እየሰጠ ያለበትና እሁድ በመስቀል አደባባይ መንግስትን ደግፎ ወያኔና ኦነግን አውግዞ እንደመሥሳቸዋለን በሚል መፈክር  ሰልፍ የዋለበትን ሁኔታ ስናይ በህዝቡና በመንግስት መካከል የድብብቆሽ ጨዋታ አይነት እየተካሄደ ያለ ተግባር መሆኑን ነው የምናውቀው እንጂ ህዝቡ ይህንን ድርድር የማያውቅ ብቻ ሳይሆን ድርድር ይካሄዳል እንኴን ብሎ እራሱን ያላዘጋጀ መሆኑን ነው ያወቅነው።
እሁድ ህዳር 7ቀን 2021 በመስቀል አደባባይ ወያኔንና ኦነግን አውግዞ ህዝብ ሰልፍ በወጣበት እለት መንግስት እያወገዘው ካለው ጠላቱ ጋር እየተደራደረ ነው ብሎ ፈጽሞ የገመተ አይደለም። መስቀል አደባባይ የወጣው ህዝብ ወያኔና ኦነግን እውግዞ ጦርነቱን ደግፎ ሰልፍ የወጣ ሆኖ ሳለ የአቢይ መንግስት ግን የበረዶ ያህል የሆነ መልእክትን በአንድ ዲሽታ ጊና የተባለ ዘፋኝ በኩል «እርቅ ያስፈልገናል ብረት ይበቃናል» የሚል ይዘት ያለው ሰላምና እርቅ ጠያቂ በማስተላለፍ በህዝቡ ላይ በርዶ ቸልሶ ሲያጯጩህ ታይታል።
የአማራ ህዝብ ወኪል በሌለበት ሁኔታ ይህ ድርድር በምስጢር እየተካሄደ ሆኖ ሳለና ይህንንም ድርድር ብአዴንና አብን አይተውና ሰምተው በውስጥ ተዋቂነት የተስማሙበትም ሆነው ሳለ ህዝቡ ግን ብአዴንና ብልጽግና አመራር ስር ሆኜ መብትና ህልውናዬ ይከበራል በሚል እምነት የራሱን ነጻና አማራዊ የሆነ ሃይል ሲፈጥር አልታየምና ዛሬ የአማራ ህዝብ ተክዷል ብዬ መግለጽ ይቸግረኛል።
ሆኖም ይህ ብልጽግናዊ አቌምና አዲስ ውሳኔ የሚፈጥራቸው በርካታ አዳዲስ ኩነቶች በቀጣይ ሲፈጸሙ የምናይ ሲሆን የአማራ ህዝብ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚይዘው አቌምና ውሳኔ ህልውናውን የሚወስን ስለመሆኑ መናገር ይቻላል። ያንንም እርምጃውን በቀጣይ የምናየው ይሆናል።
Filed in: Amharic