>

የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደሮች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እያከበሩ አይደለም...!!!  (ባልደራስ )

የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደሮች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እያከበሩ አይደለም…!!!
 ባልደራስ 

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት አቶ ስንታየሁ ቸኮል የገጠማቸውን የኩሊላት ህመም በግል ሆስፒታል እንዲታከሙ ብይን መስጠቱ ይታወሳል።
ይሁን እንጅ  የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የፍ/ቤቱን ትዕዛዝ አክብሮ አቶ ስንታየሁ ቸኮል በግል ሆስፒታል እንዲታከሙ ማድረግ ሲገባው ይህንን ለመፈፀም ፈቃደኛ አልሆነም። ፍ/ቤት የሰጠውን ትዕዛዝ ተከትሎ አቶ ስንታየሁ ቸኮል የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደሮችን ወደ ግል ሆስፒታል ሄደው ህክምና እንዲያገኙ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ማረሚያ ቤቱ አሻፈረኝ ብሏል።
በመሆኑም አቶ ስንታየሁ ቸኮል የማረሚያ ቤቱ አስተዳደሮች የፍ/ቤቱን ትዕዛዝ አለማክበርን ተከትሎ በሚደርስባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት/በህይዎት የመኖር መብት/ክልከላና እና ማንኛውም አይነት ጉዳት ሃላፊነቱን የማረሚያ ቤቱ አስተዳድሮች የሚወስዱ ይሆናል።በተጨማሪም የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ሚዲያዎች፣የሲቪክ ማህበራት እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዮ ትኩረት እንዲያገኝ የበኩላቸውን ግፊት እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።
በተመሳሳይ የባልደራስ ለዕውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋን  ደብዳቢ ቡድን አደራጅተው በመላክ ያስደበደቡትን አካላት ክስ ለመመስረት ቢጠይቅም ይህንንም ለማስተናገድ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ምንም እንኳን እስክንድር ነጋን “የደበደበህን አካል መክሰስ ትችላለህ” ቢሉትም አቶ እስክንድር ግን “ደባዳቢውን ሳይሆን አስደብዳቢዎቼን ነው የምከሰው” ማለቱ ይታወሳል። በዚህ መሰረት ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ደብዳቢዎችን አደራጅቶ የላከውን አካል አቶ እስክንድር ለመክሰስ ቢጠይቅም ማረሚያ ቤቱ ይሁንታውን ነፍጓል።
የኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት በየጊዜው እንዲህ እየቀለለ መምጣቱ ዕጅግ አሳሳቢ ሆኗል። በተለይም በፍርድ ቤት የሚሰጡ ትዕዛዞችን  በተደጋጋሚ በመንግስታዊ ተቋማት አልታዘዝም ባይነት የሚደረጉ ማናቸውም ተግባራት ሰላማዊ ትግሉን እና ታጋዮችን የበለጠ ወደ ኋላ የሚመልስ እንዳይሆን ያሰጋናል።
Filed in: Amharic