“የኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ በምጥ ተይዛ ጭንቅ ላይ ያለችና ወልዳ ለመሳም ጥቂት ቀናት ከቀሯት ሴት ጋር ትመሳሰላለች ….!!!” ዶ/ር ዮናስ አደይ
ዋቅሹም ፍቃዱ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና የደህንነት ጥናት ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዮናስ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ምንምኳ ዛሬ አገሪቱ እውነትን ይዛ የብዙ ጫናዎች ሰለባ ብትሆንም፣ የያዘችው እውነት ዘላቂ ነውና የጠላት የውሸት ክምር ራቁቱን ቀርቶ የኢትዮጵያ አሸናፊነት የሚገለጥበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።
እንደ ዶክተር ዮናስ ገለጻ መንግሥት በሆደ ሰፊነት አገሪቱን በሰላምና በይቅርታ ለማሻገር የሃይማኖት አባቶች፣የአገር ሽማግሌዎች፣አባ ገዳዎችና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች ወደ መቀሌ በተደጋጋሚ ሄደው ለሽምግልና ቢቀመጡም አሸባሪው ሕወሓት ግን በበላይነት እንጂ በእኩልነት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መኖር የሚፈልግ ባለመሆኑ ሽማግሌዎችን አሳፍሮ መልሷል። ቡድኑ ይባስ ብሎ ለዘመናት የክልሉን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ህዝቡን በፍጹም ታማኝነት ሲያገለግሉ የነበረው የሰሜን ዕዝን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ጨፍጭፏል።
አሸባሪ ቡድኑ ደጋፊዎችም አገር ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳውን ቡድን ሥርዓት ለማስያዝ ብሎም የአገር ህልውና ለማስቀጠል የኢትዮጵያ ህዝብ ተገዶ የገባበትን ጦርነት በማናናቅ ይባሱንም ተበዳዩን በዳይ አድርጎ በማቅረብ ኢትዮጵያ ላይ የተቀናጀ ዘመቻ ማድረጋቸው አሳዛኝ ክስተት ነው ያሉት ዶ/ር ዮናስ፤ የውጭ ኃይሎች አሸባሪ ቡድኑ በግንባር ያጣውን ጦርነት በፈጠራ ወሬ ለማካካስ የሀሰት ወሬ በማራገብ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በየትም አገር ሰላምና ጸጥታን የማስከበር ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑ ሁሉም የሚስማማበት ጉዳይ መሆኑን ያስገነዘቡት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ያለ ሰላም የሚፈጸሙ አንዳች ነገር ባለመኖሩ መንግሥት ጸረ ሰላም ኃይሎችን አደብ ማስገዛት ቀዳሚ ትኩረት አድርጎ መስራቱ ሊበረታታ የሚገባ ተግባር መሆን ሲገባው በምዕራባውያን ዘንድ እንደጥፋተኛ መቆጠሩ የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ምን ያህል የተዛባ አቋም እንደያዙ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በጥቅሉ የህዝቡ ተሳትፎና አገሪቱ ያላት እውነት ውሎ ሳያድር ኢትዮጵያን ለድል እንደሚያደርሳት፣ አሁናዊ ጭንቀቶችና ትርምሶች ምዕራፋቸው ተዘግቶ ሰላም የሰፈነባትና የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት ሩቅ እንደማይሆን ዶ/ር ዮናስ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። (