>

"እኔ ኢየሱስ ነኝ" ባዩ ...!!! (ጎዳና ያእቆብ)

“እኔ ኢየሱስ ነኝ ” ባዩ …!!!

ጎዳና ያእቆብ

 

*…. የማዕበሉ ታሪክ ነግሮን አብሬአችሁ በጀልባው ላይ ነኝ እንጂ ደልቶኝ የሆነ ቦታ ሶፋ ላይ አልተቀመጥኩም የሚል ነውና በስሱ እንፈትሸው:: 
አብይ አህመድ  <<ደሴ ሲያዝ ኮምቦልቻ ሲያዝ ጠቅላይ ሚንስትሩ የት አሉ? ሲሉ የነገርኳቸውን ታሪክ ነግሬአችሁ እጨርሳለሁ>> ብሎ የነገራቸው ታሪክ እነሆ! ከማን ጋር እንዳሉና ጌታቸው ምን ማድረግ ይችላል የሚለውን ከዚያን ጊዜ በፊት አያውቁም ነበረ ለሚለው አውድ እንዲሰጥ በማለት ነገር ከዘፍጥረት ነውና የማቲዎስ ወንጌል ከቁጥር አንድ ጀምሮ ከታች አቅርቤዋለሁ::
(1)  ለምፅን በዳሰሳ ብቻ መፈወስ መቻሉን ማወቃቸውን ብዙም ሳትርቁ ቁጥር ሁለት ላይ ታገኙታላችሁ::
 (2) ሽባን በቃሉ ብቻ መፈወስ የሚችል መሆኑን ቁጥር 13 ላይ እንዲሁም
 (3) በንዳድ የምትሰቃየውን የሐዋሪያው ጵጥሮስን አማች የፈወሰበትን
ቁጥር 14-15
(4) አጋንንትን ማስወጣት ቁጥር 16-17 ላይ ያዩትን ሰዎች ነው አብይ አህመድ ማን እንደሆነ አላወቁትም ነበር ያለን::
ማን መሆኑን እሺ አላወቁም ነበር የሚለውን ብንቀበል እንኳን ምን ማድረግ እንደሚችል ግን ሲያዩ መዋላቸውን አብይ አህመድ ሊነግረን ከፈለገው መልእክት  ጋር አይሄድምና ዘሎታል::
በመጨረሻም የማዕበሉ ታሪክ ነግሮን አብሬአችሁ በጀልባው ላይ ነኝ እንጂ ደልቶኝ የሆነ ቦታ ሶፋ ላይ አልተቀመጥኩም የሚል ነውና በስሱ እንፈትሸው::
ጌታችን መድሀኒታችን የምትሰምጠው ጀልባ ላይ እንጂ ሌላ ጀልባ ላይ እንዳልነበረ ሁሉ አብይ አህመድ በከበባ በወረራ በረሀብ በእንግልት በፍርሃት ካሉት ከደሴና ከኮምቦልቻ ማኅበረሰብ መካከል ሆኖ አብሮ እየተንገላታ ነው ወይስ በ4 ኪሎው ቤተ መንግስት በሪፐብሊካን ጋርድ እየተጠበቀ?
የቴሌዋ ሴትዮ ኔትዎርክ ቆርጣበታለች? የስልክ አገልግሎት ተቋርጦበት የቤተሰብ ዜና ጠፍቶበት በሀሳብና ጭንቀት ላይ ነው ወይስ ባማረ ሆቴል ምቾቱ ተጠብቆለት ንግግር እያደረገ? በረሀብ እንደ ደሴና ኮምቦልቻ ህዝብ በረሀብ ላይ ነው? ቤቱ እየተዘረፈ ነው? ልጆቹ እየተገደሉበት ነው? ሴቶቹ እየተደፈረበት ነው?
የነዚህ ሁሉ መልስ አይደለም! የሚል ሆንል ሳለ ከደሴና ከኮምቦልቻ ህዝብ ጋር በአንድ ጀልባ ላይ ነኝ ማለቱ ክፉ ስላቅ ነው:: ነገር ግን አብይ አህመድ እንኳን አሁን ላይ ሊክደው የማይችለው ሀቅ ቢኖር እሱም ኢትዮጵያ የምትባል  እየተናወጠች ያለች ባህር ላይ መሆኑንና <<ንፋስና ወጀብ የሚታዘዙለት ይህ ሰው ምንድነው (ማቲዎስ ወንጌል)? ማን ነው (ማርቆስ ወንጌል) የሚያስብል ልዩ ተስጦ ኖሮት እንደዛተው እጃችንን በአፋችን የሚያስጭን ሀይል ከሌለው በስተቀር ታንኳይቷን አስጥሞ ሲጨርስ በተመሳሳይ ባህር ላይ ያለችውን የአብይ አህመድን የምቾት መርከብ የሆነችውን ቤተ መንግስት ማናወጥ መጀመሯ የማይቀር ነው::
መከራው ደጁን ማንኳኳቱ የማይቀር ነው::
መስዋእትነት ከፍላችሁ  እና ተዋግታችሁ ባህሩን እናንተ ፀጥ እሰኙትና እኔ ከዛ መጥቼ የተቀባሁና መሲህ መሲህ የሚያጫውተኝ መሪያችሁ ክንዴ ይህችን አደረገች ብዬ ሸልላለሁ የምትል ቁማር አታዋጣም::
ስለዚህ መሲህ መሲህ መጫወቱን ትተህ የአማራን ወጣት እስከአፍንጫው አስታጥቅ:: ህዝባዊ ሀይሉን በስርህ ለማስገዛትና ለማስከበር አትዳክር:: ፋኖን ማሳደዱን ተው::
እነዘመነ ካሴን ፍርድ ቤት ለፍርድ ቤት ማንከራተቱን ትተህ በሚመጥናቸው የጦርነት አውድማ ላይ ውለው ጀግንነታቸውን እንዲያሳዩ ተዋቸው:: እንቅፋት አትሁንባቸው::
ታንኳይቷን ሊያሰምጣት ከተነሳው ወጀብ የሚያድኗት ባለ ተአምራቶች እነሱ እንጂ አንተ አይደለህምና ከመንገዳቸው ፈቀቅ በል:: ያን ብታደርግ ሀገርንም ምናልባትም እራስህንም ታድን ይሆናል:: አዳኞቹ እነሱ እንጂ ቤተ መንግስት በጥበቃ ተከበህ ያዙኝ ልቀቁኝ የምትለው አንተ አይደለህም::
ወሬን ላንተ ጀግንነትን ደግሞ ለነዘመነ ካሴ የሰጠው ፈጣሪ በስጦታው አይፀጸትምና የወሬ ዘመን እስከሚመጣ ድረስ ጥግህን ያዝ:: ጊዜው የስራ ነውና ጀግኖቹ ስራቸውን ይስሩበት:: ያን ብታደርግ ምናልባትም ትተርፍ ይሆናል::
አይ ካልክ ግን <<ላም ገመዷን በጠሰች ቢሉ የራሷን አሳጠረች>> ተብሎ ተፅፏልና (ተረትና ምሳሌ ላይ ነው የተፃፈው ደግሞ መፅሀፈ ምሳሌ ላይ ስትፈልጉ እንዳትውሉ) ወጀቡ ያንተንም ቤተ መንግስት ያንኳኳል::
የማቲዎስ ወንጌል ምእራፍ 8
1 ከተራራም በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።
2 እነሆም፥ ለምጻም ቀርቦ፡— ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ፡ እያለ ሰገደለት።
3 እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና፡— እወዳለሁ፥ ንጻ፡ አለው። ወዲያውም ለምጹ ነጻ።
4 ኢየሱስም፡— ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ፡ አለው።
5 ወደ ቅፍርናሆምም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ፡— ጌታ ሆይ፥
6 ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሣቀየ በቤት ተኝቶአል፡ ብሎ ለመነው።
7 ኢየሱስም፡— እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ፡ አለው።
8 የመቶ አለቃውም መልሶ፡— ጌታ ሆይ፥ በቤቴ ጣራ ከታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል።
9 እኔ ደግሞ ለሌሎች ተገዥ ነኝና፥ ከእኔም በታች ጭፍራ አለኝ፤ አንዱንም፡— ሂድ፡ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም፡— ና፡ ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም፡— ይህን አድርግ፡ ብለው ያደርጋል፡ አለው።
10 ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ለተከተሉት እንዲህ አለ፡— እውነት እላችኋለሁ፥ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም።
11 እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤
12 የመንግሥት ልጆች ግን በውጭ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
13 ኢየሱስም ለመቶ አለቃ፡— ሂድና እንዳመንህ ይሁንልህ፡ አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ።
14 ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን በንዳድ ታማ ተኝታ አያት፤
15 እጅዋንም ዳሰሰ፥ ንዳዱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለቻቸው።
16-17 በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ በነቢዩ በኢሳይያስ፡— እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ፡ የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ መናፍስትን በቃሉ አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ።
18 ኢየሱስም ብዙ ሰዎች ሲከቡት አይቶ ወደ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዘ።
19 አንድ ጻፊም ቀርቦ፡— መምህር ሆይ፥ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ፡ አለው።
20 ኢየሱስም፡— ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም፡ አለው።
21 ከደቀ መዛሙርቱም ሌላው፡— ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ እንድሄድ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ፡ አለው።
22 ኢየሱስም፡— ተከተለኝ፥ ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፡ አለው።
23 ወደ ታንኳም ሲገባ ደቀ መዛሙርቱ ተከተሉት።
24 እነሆም፥ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ በባሕር ታላቅ መናወጥ ሆነ፤ እርሱ ግን ተኝቶ ነበር።
25 ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፡— ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን፡ እያሉ አስነሡት።
26 እርሱም፡— እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ? አላቸው፤ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፥ ታላቅ ጸጥታም ሆነ።
27 ሰዎቹም፡— ነፋሳትና ባሕርስ ስንኳ የሚታዘዙለት፥ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? እያሉ ተደነቁ
Filed in: Amharic