>

በኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ አውሮፕላን በደረሰበት የመከስከስ አደጋ ቦይንግ ካምፓኒ ካሳ ለመስጠት ተስማማ...!!! ( ቆንጅት ስጦታው)

በኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ አውሮፕላን በደረሰበት የመከስከስ አደጋ ቦይንግ ካምፓኒ ካሳ ለመስጠት ተስማማ…!!!

ቆንጅት ስጦታው


ቦይንግ መጋቢት 01/2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ አየር መንገድ 737 ማክስ አደጋ ከሞቱት 157 መንገደኞችና የበረራ ሠራተኞች ቤተሰቦች ጋር ስምምነት ላይ ደረሰ።

የአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ በአደጋው ለሞቱት ሰዎች ኃላፊነቱን እንደሚወስድና ተጠያቂነቱንም እንደሚቀበል በቺካጎ ከሚገኘው የፍርድ ቤት ሰነዶች መረጃ ማግኘት ተችሏል።

በምላሹም የተጎጂ ቤተሰቦች ኩባንያው ላደረሰው ጉዳት በፍርድ ቤት ቅጣት እንዲታልበት አይጠይቁም።

የተጎጂ ቤተሰቦች ጠበቆች እንዳሉት ቦይንግ ለአደጋው “ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ይሆናል” ሲሉ ስምምነቱን እንደ ትልቅ ምዕራፍ ተቀብለውታል።

ከዚህም ዜና ጋር ተያይዞ የቦይንግ አክሲዮኖች ድርሻ 1 በመቶ፣ ወደ 218.50 ዶላር ወርዷል።

ስምምነቱ ከአሜሪካ ውጪ ያሉ እንደ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ባሉ አገራት ያሉ የተጎጂ ቤተሰቦች በአገራቸው ሳይሆን በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ካሳ እንዲከፈላቸው መንገድ ከፍቷል።

ካሳው የሚፈጸመው በየአገራቸው ቢሆን የበለጠ ሁኔታውን ፈታኝ እንደሚያደርገውና ክፍያውም ዝቅተኛ ይሆናል።

በአደጋው ሳም የተባለ ልጃቸውን ያጡ እንግሊዛዊው ማርክ ፔግራም “ለእኛ ዋናው አዎንታዊ ሁኔታ ቦይንግ ተጠያቂነቱን አምኖ ጥፋተኝነቱን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ፓይለቶች ላይ አለማሳበቡ ነው። ስህተታቸውን እንዲያምኑ እንፈልግ ነበር” ብለዋል።

የሳም እናት ዴቢ በበኩላቸው ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ከዚህ ከሚገኘው ማንኛውም የካሳ ገንዘብ መስራት የምንፈልገው በሳም ስም የበጎ አድራጎት ድርጅት ማቋቋም ብቻ ነው። ይህንን በጎ ሥራ መስራት ብቻ ነው የምንፈልገው ሳምም ይህንን ነው እንድናከነውን የሚፈልገው ብለዋል።”

የቦይንግ ዋና መሥሪያ ቤት በሆነው በቺካጎ ኢሊኖይ የተደረሰው ስምምነት የካሳ ክፍያ ጥያቄ እንዲቀርብ መንገድ ይከፍታል።

ሆኖም ስምምነቱ በአሁኑ ወቅት ለተጎጂ ቤተሰቦች ምንም ዓይነት የተለየ የካሳ ክፍያን ባያስቀምጥም፣ ስምምነቱ የቀጣይ ሂደቶችን መጠን እና ወሰን ይገድባል።

የሕግ ባለሙያዎች የአሁን ወይም የቀድሞ የቦይንግ ሥራ አስፈፃሚዎች በፍርድ ቤት የመመስከር እድል በጣም ያነሰ ያደርገዋል ይላሉ።

“ቦይንግ በአደጋው የሚወዷቸውን ያጡ ቤተሰቦች ሙሉ በሙሉ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለደረሰባቸው ጉዳት ካሳ እንዲከፈላቸው ቁርጠኛ ነው” ሲል ኩባንያው በመግለጫው አትቷል።

ኩባንያው “ኃላፊነቱን በመውሰድ፣ ቦይንግ ከቤተሰቦቹ ጋር ያደረገው ስምምነት ተዋዋይ ወገኖች ለእያንዳንዱ ቤተሰብ ተገቢውን ካሳ ለመወሰን በሚደረገው ጥረት እንዲያተኩሩ ያስችላቸዋል” ብሏል።

የተጎጂ ቤተሰቦች ጠበቆች በበኩላቸው ባወጡት መግለጫ በስምምነቱ መሠረት ቦይንግ “737 ማክስ አውሮፕላኑ ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ እንደነበረ እና ለጥፋቱ ማንንም ለመወንጀል እንደማይሞክር አምኗል” ብለዋል።

“ይህ የተጎጅ ቤተሰቦች በቦይንግ በደረሰው አደጋ ፍትህ እንዲያገኙ እያደረጉ ባሉት ጥረት ትልቅ ምዕራፍ ነው። ምክንያቱም ሁሉም በፍትሃዊነት እንዲስተናገዱ እና በኢሊኖይ ሕግ መሰረት ከሙሉ ጉዳታቸው የሚያገግሙበትን መንገድ ያረጋግጣል። በዚህም በስምምነትም ሆነ ወደ ፍርድ ቤት በማቅረብ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ መንገድ ከፍቷል” ብለዋል ጠበቆቹ።

ቃላቶች ከፍተኛ ቦታ አላቸው እናም በዚህ ስምምነት መሰረት ቦይንግ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 አደጋ ኃላፊነቱን ወስዷል። በዚህ አደጋ ከ35 የተለያዩ አገራት የተውጣጡ የ157 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።

ዓለም ዘንግቶት ሊሆን ይችላል እንዲሁም ቦይንግ 737 ማክስ እንደገና ይበር ይሆናል ነገር ግን በዚህ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች ሃዘናቸው አሁንም ቢሆን ጥልቅ ነው ገና ቁስላቸው አልሻረም።

በ737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሱ ሁለት አደጋዎችን ተከትሎ ቦይንግ የአብራሪዎቹን አቅም ጥያቄ በማስገባትና ጥፋቱን ወደ ሌሎች አካላት በማዛወር ትችት ሲቀርብበት ነበር።

እናም በአሁኑ ወቅት ኃላፊነት መውሰዱና ተጠያቂነትን መቀበሉ ትልቅ ነገር ነው።

ለቦይንግ ስምምነቱ የተወሰነ ጥበቃ ያደርግለታል፤ የተጎጅ ቤተሰቦች ከፍተኛ ቅጣት እንዲጣልበት መጠየቅ የማያስችል ከለላ ሰጥቶታል። የአሁኑ እና የቀድሞ ስራ አስፈፃሚዎች በፍርድ ቤት ለምስክርነት እንዳይጠሩ ማድረግ ችሏል።

ነገር ግን ኩባንያው የካሳ ጥያቄዎች በአሜሪካ ህግ መሰረት እንዲፈጸሙ ተስማምቷል፤ ይህም በሌሎች በርካታ ሃገራት ተፈፃሚ ከሚሆነው እጅግ የላቀ የካሳ ክፍያን ይደነግጋል።

አደጋው በደረሰበት ወቅት 737 ማክስ አውሮፕላን በቦይንግ ከፍተኛ ሽያጭ የነበረው ምርት ነበር።

ነገር ግን በአምስት ወራት ውስጥ ለበርካታ ሰዎች እልቂት የሆኑ ሁለት አደጋዎች ደረሱ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ናይሮቢ የሚያደርገውን ጉዞ ከጀመረ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ነበር አደጋው የደረሰው።

ከዚያም ቀደም ብሎ የኢንዶኔዥያው ላየር ኤይር ጄት በኢንዶኔዥያ ባሕር ላይ መከስከሱ በአውሮፕላኖቹ ላይ ከባድ ችግሮች እንዳሉ አሳይቷል።

አደጋዎቹን ተከትሎ አውሮፕላኖቹ ምርመራ እየተከናወነ በነበረበት ወቅት ለ20 ወራት አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርጎ የቆ ሲሆን ኩባንያው በሶፍትዌሩ እና በስልጠናዎች ላይ ከፍተኛ ለውጥ ካደረገ በኋላ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ተፈቅዶላቸዋል።

Filed in: Amharic