>

አሁን ላይ የሚያስፈልገን ዐዋጅ ...!!! (ዘመድኩን በቀለ)

አሁን ላይ የሚያስፈልገን ዐዋጅ …!!!

ዘመድኩን በቀለ

 

*…. ኢትዮጵያዊ መሪ ካገኘን እናቸንፋለን ‼ ፒኮካም ሳይሆን አንበሳ የሆነ መሪ ካገኘን እናቸንፋለን ‼ መሪው አፈ ቅቤ ሆደ ጩቤ ሆኖ እንደ ይሁዳ አሳልፎ በመሳም ቢሸጠንም እናቸንፋለን ‼ እንደ ጃንሆይ ወደ ሎንዶን፣ እንደ መንጌ ወደ ሀራሬ ጥሎን ቢፈረጥጥም እናቸንፋለን ‼ እንደ አጤ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ፣ እንደ አጤ ዮሐንስ መተማ ላይ ቢሰዋም እናቸንፋለን ‼ የዐረቡ መንቀዥቀዥ፣ የነጮቹ መንበዛበዝ፣ የጥቁሮቹ መንቦቅቦቅ ኢትዮጵያን አሸናፊ ከማድረግ አያግዳትም!!!
 
…የጥንቶቹ ቅኝ ገዢዎች ዘመኑን በዋጀ በአዲስ መልክ ሜካፓቸውን ተቀባብተው መልካቸውንም ለዋውጠው ተኳኩለውም በገሀድ በቀን ብርሃን ዓለሙ ሁሉ እያያቸው፣ እየተመለከታቸውም በድጋሚ የመምጣታቸው ነገር እውን እየሆነ የመጣ ይመስላል። ፋሽስት ኢጣልያን በአክሱም ጽዮን፣ እንግሊዞችን በእንዳ ማርያም ተቀብለውና አዝለው ወደ ኢትዮጵያ አስገብተው ያስወጓት የያኔዎቹ ባንዳዎች የልጅ ልጆች የሆኑት ህወሓት የሚባሉቱ መርዘኞችም አሁንም ኢምፔሪያሊስት አማሪካንን አዝለው በፋሽስቷ አማሪካና አጋሮቿም ታዝለው ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ዳግም ቅኝ ሊገዙን እየተጋጋጡም ይገኛሉ።
…የቀደሙቱን ቅኝ ገዢዎች ለመመከት የሃገሪቱ መሪዎች ዕውቀት፣ የአመራር ጥበብ፣ ብስለት፣ ታማኝነት፣ እምነታቸው ጭምር ወሳኝ ነበር። ህዝብን በአንድ በማስተባበር፣ የተጣሉትን በማስታረቅ። ቅሬታ የነበረባቸውንም ቅሬታቸውንም በግልፅ በመፍታት ለአንድ ዓላማም በማሰለፍ ድል አድርገው ነፃ ሃገር ከነፃ ህዝብ ጋር አስረክበውናል። አሁን ያጣነው እንደዚያ ዓይነት እንደቀደሙቱ አበው ያለ በፍፁም ልብ ሃገሩን የሚወድ፣ ህዝብ አንድ አድርጎ የሚያስተባብር መሪ ነው ያጣነው። በምላስ ሳይሆን ከአንጀት ከልቡ ሃገሩንና ህዝብን የሚወድና የሚያፈቅር መሪ ነው ያጣነው። በህዝብ ከፋፋዩ በወያኔ ድርሰት፣ ሕግና ደንብ፣ መመሪያም ሕገመንግሥት ተብዬው የሞት ሰነድ እየመራ ወያኔን አሸንፋለሁ የሚል ዳተኛ መንግሥት ነው የገጠመን። ከፋፋይ  ‼ ራሱ ዘረኛ ‼ ስለጎጡ ብቻ የሚጨነቅ ደንታቢስ መሪ ነው የገጠመን ‼
… ተነሥ፣ ታጠቅ፣ ዝመት አይባልም እያለ ጠላት እንደ ፍልፈል መሬትም ሰውም እያረሰ ሸዋ ድረስ እስኪገባ የሚጠብቅ መልኩንም በሜካፕ እያሳመረ፣ በውበት ሳሎን ተቀምጦ ሲኳኳል ጊዜ ሰዓቱንም እያጠፋ፣ አደንዛዥ ስብከት እየጋተ ወደ ኋላ የሚጎትተን ፒኮካም መሪ ይዘን አናቸንፍም። አንበሳ መሪ የያዘ ነው የሞያቸንፈው። ወያኔ 10 ያደረገችውን ክልል እሱ 12 አድርሶት ያረፈ፣ ያልታወቀበት ከፋፋይ፣ በጣጣሽ፣ መሪ ይዘን አናቸንፍም። ሕገ መንግሥቱን አቅፎ፣ ደግፎ ተንከባክቦ ለወያኔ ለማስረከብ በታማኝነት እያገለገለ ያለ መሪ እኮ ነው የተቀመጠብን። ሃገርን ማዳን ለዐማራና ለዐፋር ሰጥቶ እርሱ ኩታገጠም እርሻ ሲጎበኝ የሚውል ቀልደኛ መንግሥት እኮ ነው የገጠመን። ከመዲናዋ በመቶ ኪሎ ሜትሮች ውስጥ ጦርነት እየተካሄደ ለወታደሩ የውጊያ ትእዛዝ የማይሰጥ እንደ ሙሴ አሻጋሪ፣ እንደ ኢየሱስ አዳኝ ነኝ እያለ የሚያላግጥ መሪ እኮ ነው የገጠመን። እሱን አትናገረው ይባልልኛላ!  ኣ…
…ወደድንም ጠላንም አሁን ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት መሪ እንደ እምዬ ምኒልክ ዓይነት አንበሳ የሆነ መሪ ነው። ወንድ የወንዶች ቁና የሆነ መሪ ነው። ተረት ወሬ የማያበዛ፣ ቆፍጠን ሰብሰብ ያለ፣ ኩልና ቻፒስቲክ ተቀብቶ እዩኝ እዩኝ የማይል። አማኝ የእግዚአብሔር ሰው። ችግኝ እየተከለ ሰው የማይነቅል። የህዝብ መራብ፣ መሞት፣ መገደል፣ መሰቃየት፣ መታረድ የሚያንገበግበው፣ ህዝብን በአንድ የሚያስተባብር። ቁማርተኛ፣ ዋሾ፣ ሙልጭልጭ፣ ተልባ ያልሆነ፣ በሁሉ ለመወደድ፣ ለመደነቅ፣ ለመፈቀር የማይላላጥ፣ በቃሉ የሚታመን፣ ለንግግሩ ለከት ደርዝም ያለው። ቁርጠኛ የሆነ መሪ ነው የሚያስፈልገን። አጤ ምኒልክን ዛሬ በወያኔና በኦነግ የሃሰት ትርክት ተነሥተህ ልትጠላው ትችላለህ። አፍጋኒስታን ገብታ አፍጋኒስታንን ያደቀቀችው አማሪካ ኢትዮጵያ ስትገባልህ ቅቤ የምትቀባህ፣ እርጎ ማርና ወተት የምታጠጣህ የሚመስልህ ካለህ ጊዜው ሲደርስ ዋጋህን ታገኛለህ።
… አዎ አሁን “ማርያምን” ብሎ መማሉ እንኳ ቢቀር ልክ እንደ አጤ ሚኒልክ “ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስከ አሁን አላስቀየምኽኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበትም የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ አልተውህም፤ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም።” ብሎ በይፋ ሃገር በአንድነት የሚያንቀሳቅስ መሪ ነው የሚያስፈልገን።
… ዐማራን ብቻ በአገኘሁ ተሻገር ጊዜ 3 ጊዜ፣ በአዲሱ አስተዳዳሪ ሁለት ጊዜ ክተት ማሳወጁ ፌር አይደለም። ክተቱን ሰምቶ የዘመተውን ግምባር ላይ ከምሮ መቀመጥም ፌር አይደለም። ጦርነቱን ማራዘምም ፌር አይደለም። እንደ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ መሪ ለመሆን ሲጋጋጥ የነበረው ሰው በይፋ የክተት ዐዋጅ ዐውጆ የተንዛዛውን አሰልቺ ጦርነት የሚቋጭ መሪ ነው የሚያስፈልገን። የዐማራን ወንድ ብቻ ወደ ጦር ግንባር ወስዶ መማገድም፣ አሰልችቶ ያለውጊያ ማስቀመጥም ፌር አይደለም። “አልታዘዝንም” እያለ የሚፈረጥጥ መከላከያ ይዞም ማሸነፍ አይታሰብም። የኦሮሞን ልዩ ኃይል ጦር ሰውሮ አስቀምጦ በዐማራ፣ በደቡብና በአፋር ልጆች እልቂት ብቻ ድልን መጠበቁም ፌር አይደለም። በሰላማዊ ሰልፍና በዶክመንተሪም ማሸነፍ አይቻልም።
… አሁን ለኢትዮጵያ ልክ እንደ የእምዬ ምኒልክ ዓይነቱ ዐዋጅ ነው የሚያስፈልገን። ተነሥ፣ ታጠቅ፣ ዝመት አያስፈልግም ብሎ ውሽልሽል፣ ሽባ የሚያደርገን ቃል የሚያሰማን መሪ ሳይሆን “ተከተለኝ” የሚል የእምዬ ምኒልክ ዓይነት የወንድ ዐዋጅ ነው የሚያስፈልገን።
• የእምዬ ምኒልክ ዐዋጅ 
… ‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስከ አሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስከ አሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። አሁንም አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል። እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰዉን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስከ አሁን አላስቀየምኽኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበትም የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ አልተውህም፤ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ፡፡››
… ኢትዮጵያዊ መሪ ካገኘን እናቸንፋለን ‼ ፒኮካም ሳይሆን አንበሳ የሆነ መሪ ካገኘን እናቸንፋለን ‼ መሪው አፈ ቅቤ ሆደ ጩቤ ሆኖ እንደ ይሁዳ አሳልፎ በመሳም ቢሸጠንም እናቸንፋለን ‼ እንደ ጃንሆይ ወደ ሎንዶን፣ እንደ መንጌ ወደ ሀራሬ ጥሎን ቢፈረጥጥም እናቸንፋለን ‼ እንደ አጤ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ፣ እንደ አጤ ዮሐንስ መተማ ላይ ቢሰዋም እናቸንፋለን ‼ የዐረቡ መንቀዥቀዥ፣ የነጮቹ መንበዛበዝ፣ የጥቁሮቹ መንቦቅቦቅ ኢትዮጵያን አሸናፊ ከማድረግ አያግዳትም።
…የደኅንነት ሓላፊ በነበረ ጊዜ ለሽፍታው ኦነግ በድብቅ ይሠራ እንደነበረ ሳይሳቀቅ፣ ሳይሸክከው በገሃድ የነገረን ሰውዬ አሁንም በድብቅ ለአማሪካም፣ ለህወሓትም አይሠራም ብዬ ለማመን እቸገራለሁ።
• ኢትዮጵያ ግን ታቸንፋለች ‼
Filed in: Amharic