>

የዐብይ አሕመድ የድርድር ተውኔትና የደመቀ መኮንን ሚና (መስፍን አረጋ)

የዐብይ አሕመድ የድርድር ተውኔትና የደመቀ መኮንን ሚና

 

መስፍን አረጋ


የዐብይ አሕመድ ዋና አማካሪ ኦቦ ሌንጮ ባቲ እንደፎከረው ከሆነ ‹‹ኦሮሞ ሦስት ሺ ዓመት ይገዛል››፡፡  ይህ ማለት ደግሞ፣ ዲሞክራሲ፣ አንድ ሰው አንድ ድምጽ፣ የዜግነት ፖለቲካ የሚባል ቀልድ የለም ማለት ነው፡፡  ኦሮሞ ያልሆንክ ሁሉ ብዙሃንም ሆንክ ንዑሳን፣ ወደህም ሆነ ተገደህ ሁለተኛ ዜግነትህን አምነህ ለሦስት ሺ ዓመት በኦነጋዊና በኦነጋዊ ብቻ ትገዛለህ ማለት ነው፡፡  

ዐብይ አሕመድ ደግሞ ስልጣን ከያዘበት ዕለት ጀምሮ እየሠራ ያለው የዋና አማካሪውን የሌንጮ ባቲን ፉከራ እውን ለማድረግ ነው፡፡   በዚህ ረገድ ደግሞ የኢትዮጵያን ሐበሻዊ አሻራ በማጥፋትና አማራንና ትግሬን በፖለቲካና በኢኮኖሚ በማዳከም ብዙ ርቀት ተጉዟል፡፡  ዐብይ አሕመድ የኦነጋውያንን ዓላማ ለማሳካት በሦስት ዓመት ብቻ የተጓዘው ርቀት፣ ኦነጋውያን በመቶ ዓመት እንጓዘዋልን ብለው ሊያስቡት ቀርቶ ሊያልሙት የማይችሉትን ነው፡፡   

ዐብይ አሕመድ የኦቦ ሌንጮ ባቲን ፉከራ እውን የሚያደርገውና አሮሞ ሦስት ሺ ዓመት የሚገዛው፣ አማራና ትግሬ ሙሉ በሙሉ አዳክሞ ሙሉ በሙሉ ከጨዋታ ውጭ ካደረጋቸው ብቻ ነው፡፡  ይህን ለማድረግ ግን በኦነጋዊ ሠራዊቱ ሊተማማን አይችልም፡፡  የዐብይ አሕመድ ኦነግ ወይም ሸኔ አማራና ትግሬ ተዳምረው ይቅርና ካንዱ ፊት ሊቆም እንደማይችል ራሱ ዐብይ አሕመድ በደንብ ያውቃል፡፡   በዚህ ረገድ የኦነጋውያንን ምንነት ጠንቅቆ የሚያውቀው ወያኔው ሰየ አብርሓ ‹‹ኦነግን ከሳንቲም አንቆጥረውም›› በማለቱ ምንም አልተሳሳተም፡፡  

አሁን ላይ ደግሞ ዐብይ አሕመድ አማራን እጎዳለሁ ብሎ ኦነጋዊ ሠራዊቱን ሽሽት ስላስተማረውየለመደ ጦጣ ሁልጊዜም ፍርጠጣ ስለሆነ፣  የሺመልስ አብዲሳ ሠላሳ ዘር ስልጡን ከሠላሳ ሳንቲም እንደማይቆጠር ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡  ዶሮ ፊት ፈንግል አይወራም፡፡   ወታደርን ደግሞ አስፈላጊ ከሆነ እንዲያፈገፍግ አንጅ እንዲሸሽ ማዘዝ ቀርቶ ሽሽት የምትለውን ቃል ካንደበቱ እንዲያወጣ ሊፈቀድለት አይገባም፣ አንዴ መሸሽ ከጀመረ ሁሌም ይሸሻልና፡፡  ዐብይ አሕመድ ግን አማራን በሻሻ ለማድረግ ሲል ላኮመልዛ (ወሎ) ላይ የፈጸመው ይህን ትልቅ ወታደራዊ ስህተት ነው፡፡  አማራን አንኮታኩታለሁ ብሎ በሽመልስ አብዲሳ በኩል ብዙ የደከመበትን ሆልቆ መሣፍርት የሌለውን ኦነጋዊ ሠራዊቱን ከንቱ አደረገው፡፡  ባህያ ቆዳ የተሠራ ቤት፣ ይንኮታኮታል ጅብ የጮኸ ለት፡፡    

ስለዚህም፣ ዐብይ አሕመድ የሌንጮ ባቲን ፉካራ እውን ማድረግ የሚችለው፣ በኦነጋዊ ሠራዊቱ ክሂሎት ሳይሆን አማራንና ትግሬ እርስበርሳቸው እንዲዳከሙ በማድረግ ብቻ ነው ማለት ነው፡፡  ይህን ማድረግ የሚችለው ደግሞ የሚደነቅለትን ከፍተኛ የማጭበርበር ችሎታውን፣ በከፍተኛ ደረጃ በመጠቀም ነው፡፡ 

በመጀመርያ ወያኔን መጣሁብሽ፣ ልመጣብሽ ነው እያለ በባዶ ዛቻ በማስፈራራት ውስጥ ለውስጥ ቆስቁሶ፣ በሰሜን እዝ የሚገኙትን የአማራ የጦር መኮንኖች እንድትጨፈጭፍ አነሳሳት፡፡  በዚህም የአማራ ሕዝብ የጦር መሪ እንዳይኖረው አደረገ፡፡  ቀጠለና ደግሞ የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት በከፍተኛ መስዋእትነት ወያኔን ከሞት አፋፍ እስኪያደርሳት ድረስ ከጠበቀ በኋላ፣ ሕግ በማስከበር ሰበብ በትግራይ ላይ ዘመቶ ትግራይን በሻሻ አደረጋት፡፡  ትግራይን በሻሻ ካደረገ በኋላ ደግሞ ትግራይ ላይ በሾማቸው ብልጽግናወች አማካኝነት ከወያኔ ጋር ውስጥ ለውስጥ እየተገናኘ፣ ወያኔ እስከ ደብረብርሃን ድረስ በመውረር የአማራን ክልል በሻሻ እንድታደርገው ተስማማ፡፡  በስምምነቱ መሠረት ደግሞ ቃሉን አክብሮ ወያኔ ደብረብርሃን ደጃፍ እስከምትደርስ ድረስ ማድረግ የሚችለውን እገዛ ሁሉ አደረገላት፡፡

የወያኔን አጭበርባሪነት በደንብ የሚያውቀውን አጭበርባሪውን ዐብይ አሕመድን አሁን ላይ የሚያስጨንቀው አንድና አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡   እሱም እኔ ቃሌን አክብሬ ወያኔን ደብረብርሃን እንዳደረስኳት፣ እሷም ቃሏን አክብራ ደብረብርሃንን ከመዘበረች በኋላ እዛው ትቆማለች ወይስ ቃሏን በልታ ወደ ኦሮምያ ትገፋለቸህ የሚለው ጭንቀቱ ነው፡፡  ዐብይ አሕመድ እንደራደር የሚለው ይህን ጭንቀቱን ለማስወገድ ነው፡፡  በሌላ አባባል ዐብይ አሕመድ ድርድር ሲል፣ እንደራደር ማለቱ ሳይሆን አስቀድመን በሕቡዕ የተደራደርነውን ላለማፍረስ በዓለም ሕዝብ ፊት በይፋ ቃል እንገባባ ማለቱ ነው፡፡  

ወያኔ ቃሏን ካከበረችና ከደብረብርሃን ካላለፈች በወረራ ያገኘችውን ሁሉ በስምምነት መልክ ሙሉ በሙሉ ሊያጸድቅላት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነው፡፡  ቃሏን ካላከበረችና ወደ አዲስ አበባ እገፋለሁ ካለች ደግሞ ለይልማ መርዳሳ ቀጭን ትእዛዝ ይሰጥና ሥራ ፈትተው የተቀመጡትን ድሮኖችና ጀቶች አስነስቶ የቻለውን ያህል ይቀጠቅጣታል፡፡  ከጥቂት ወራት በፊት በአፋር ግንባር በኩል በጀቶችና በድሮኖች የቀጠቀጣት፣ በስምምነታቸው መሠረት ደብረብርሃን ስትደርስ ካልቆመች ምን እንደሚጠብቃት አስቀድሞ ሊያስፈራራት ነው፡፡  አለበለዚያማ በጀትና በድሮን ዶግ አመድ ልትደረግ የምትችለው በአፋር ተረራሮች (ጠልጣል) ላይ ሳይሆን፣ በራያ አውላላ ሜዳወች ላይ ነበር፡፡ 

ዐብይ አሕመድና ደብረጽዮን ተካካዱ አልተካካዱ የራሳቸው ጉዳይ እንጅ የአማራ ጉዳይ አይደለም፡፡  ለአማራ ሕዝብ ወሳኝ የሆነው ጉዳይ ግን ዐብይ አሕመድና ደብረጽዮን ቃላቸውን አክብረው ድርድር በሚሉት ተውኔት (ሺጣራ) አስቀድመው በሕቡዕ የተስማሙትን ስምምነት በይፋ ከተፈራረሙ፣ ዐብይ አሕመድ ራሱን ከወንጀሉ ነጻ ለማድረግ በአማራ ሕዝብ ስም እንዲፈርሙ ያዘጋጃቸው እነማንን ነው የሚለው ነው፡፡  እንደምንሰማው ደግሞ የአማራ ተወካዮች ነን በማለት የአማራን ውርደት በፊርማ ለማረጋገጥ የዐብይ አሕመድን ትእዛዝ በተጠንቀቅ እየተጠባበቁ ያሉት አቶ ደመቀ መኮንንና አቶ ተመስገን ጡሩነህ ናቸው፡፡  እሳት በሌለበት ጭስ አይኖርምና፣ የምንሰማው ውነት ከሆነ ደግሞ የነዚህን ሁለት ግለሰቦች ማንነት ወደ ኋላ መለስ ብሎ መቃኘት ግድ ይላል፡፡   

እነዚህ ሁለት ሰወች ወደውም ሆነ ተገደው (convinced or confused) በሰኔ አስራምስቱ የባሕርዳር ጭፍጨፋ ላይ በተጫወቱት ወሳኝ ሚና አማካኝነት የዐብይ አሕመድ እስረኞች እንደሆኑና፣ ዐብይ አሕመድም የወንጀል ግብራበሮቹ መሆናቸውን እንደ ማስፈራርያ በመጠቀም ሲጠራቸው ወዴት፣ ሲልካቸው አቤት የሚሉ፣ አፋሽ አጎንባሹ የሆኑ፣ ፍጹም ታዛዥ ሎሌወቹ እንዳደረጋቸው የታወቀ ነው፡፡ 

በተለይም ደግሞ አቶ ደመቀ መኮንን ነገረ ሥራው ሁሉ ወሎ የኦሮሞ ነው በሚለው በኦነጋዊው በዐብይ አሕመድ ስብከት ታውሮ ወደ ኦነጋዊነት የተቀየረና የኦነጋውያንን ፀራማራ አጀንዳ የሚያራምድ ያስመስልበታል፡፡  በኔ በኩል ደግሞ አማራ መስሎ አማራን የሚያስበላ ሕቡዕ ኦነጋዊ ሁኗል ብየ ከደመደምኩ ቆየሁ፡፡  አለበለዚያማ እመራዋለሁ የሚለው የአማራ ሕዝብ የዐብይ አሕመድ ኦነጋዊ መንግሥት በሚፈጽመበት ደባ ሳቢያ ይህ ሁሉ የመከራ ዶፍ ሲወርድበት፣ ቢያንስ ቢያንስ ስልጣኑን በፈቃዱ ይለቅ ነበር፡፡  በዚህ ረገድ ደግሞ ትንሹ ሰው አባዱላ ገመዳ በወያኔ ዘመን ያደረገውን አስታውሶ እንደ ምሳሌ ሊጠቀምበት ይችል ነበር፡፡  

የፈረንጅ ምሳሌ አስፈልጎት ቢሆን ኑሮ ደግሞ የሩሲያው ቦሪስ የልትሲን (Boris Yeltsin) ያደረገውን አያጣውም ነበር፡፡  ምዕራባውያን በቦሪስ የልትሲን አማካኝነት ሩሲያን አዋረዷትና በሩሲያውያን ላይ ለተወሰኑ ዓመታት ተጨማለቁባቸው፡፡  የልትሲን ግን ሩሲያን ለምዕራባውያን የቀን ጅቦች አሳልፎ ቢሰጣትም፣ በስተመጨረሻ ግን ከቀን ጅቦቹ የሚያስጥላትን ሩሲያዊ አንበሳ በቦታው ተክቶ፣ ላገሩ ትልቅ ውለታ ውሎ፣ የቆሸሸውን ታሪኩን አጽድቶ፣ በክብር አለፈ፡፡  ሩሲያም ባጭር ጊዜ ውስጥ አንሰራራችና፣ ያምሷት፣ ያተራምሷት የነበሩት ምዕራባውያን አመሰችን፣ አተራመሰችን እያሉ ይወቅሷት፣ ይከሷት ጀመር፡፡  የተሳለቁባትን ምዕራባውያንን በተራዋ ተሳለቀችባቸው፡፡

አቶ ደመቀ ደግሞ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚጨማለቀውን፣ እዚህ ግባ ይባል ያልነበረውን ኦነጋዊውን ዐብይ አሕመድን ሰማይ ለመስቀል ያንበሳውን ሚና የተጫወተ፣ የአማራ ሕዝብ ዋና ተወካይ ነኝ የሚል ብአዴናዊ ነው፡፡  ስለዚህም ብአዴናዊ ቦታውን ለአማራዊ ፑቲን በመልቀቅ፣ ዐብይ አሐመድን ከአማራ ጫንቃ በማውረድ ረገድ ያንበሳውን ሚና መጫወት ይችል ነበር፡፡  እንደሚችልም ተደጋግሞ ተነግሮት ነበር፡፡  አውቆ ስለተኛ ቢቀሰቅሱት አልሰማ ብሎ እንጅ፡፡  ዐብይ አሕመድ በተጭበረበረ ምርጫ ስልጣኑን ከማደላደሉ በፊት ደመቀ መኮንን ብአዴንን ይዞ ከብልጽግና ቢወጣ ኖሮ፣ የዐብይ አሕመድ ፀራማራ መንግሥት በማግስቱ ይፈርስ ነበር፡፡   

አቶ ደመቀ መኮንን፣ እስኪ እንደገና እንንገርህና በድጋሚ አስበው፡፡  እመራዋለሁ የምትለው የአማራ ሕዝብ በዚህ ደረጃ ከተዋረደና ከታረደ በኋላ በመሪነትህ የምትቀጥለው በምን መመዘኛ ነው?  እኔ ነህ ብየ እንደምገምተው በአማራነት ስም አማራን የምታስበላ ሕቡዕ ኦነጋዊ ካልሆንክ በስተቀር፣ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል አማራዊ ቁጭት ቢኖርህ፣ አማራን ከሚያዋርደውና ከሚያሳርደው ከኦነጋዊው ዐብይ አሕመድ ጋር ላንድ ቀን እንኳን እንዴት አብረህ ትሰራለህ?  ሰፊ ዝግጅት አዘጋጅቶ፣ የሚዲያ ሰወችን ጠርቶ፣ ድንኳን ጥሎ የመሚመረቀውን የሸኔን ሠራዊት የሚያስታጥቀው ዐብይ አሕመድ መሆኑን አወቀህ እንዳላወቅህ ለምን ትሆናለህ?  እሺ፣ ድፍን አገር የሚያውቅውን አንተ አታውቅም እንበል፡፡  ዐብይ አሕመድ የኢትዮጵያ መሪ ነኝ እስካለ ደረስ፣ መሪነቱ ለአማራ ሕዝብም ጭምር ስለሆነና በሱ አመራር በአማራ ሕዝብ ላይ ለደረሰው ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ ተጠያቂ ስለሆነ፣ ከስልጣኑ ባፋጠኝ መወገድ እንዳለበት እንዴት ይጠፋሃል?  ባመራር ብቃት ማነስም ሆነ በሻጥር በሚመራው ሕዝብ ላይ ይህን ሁሉ ጥፋት ያደረሰ መሪ፣ በመሪነቱ ሲቀጥል ያየኸው የት አገር ላይ ነው?  አዘዋለሁ የሚለው ጦር በዚህ ደረጃ የተሸነፈበት ጠቅላይ የጦር አዛዥ ማምራት የነበረበት ወደ ጦር ፍርድቤት አይደለም ወይ?       

ዐብይ አሕመድ የሦስት ሺ ዓመት አገር በሦስት ዓመት ያፈራረሰ ኦነጋዊ ጀግና ስለሆነ፣ አባ ገዳወች ሺህ ዓመት ንገሥ ብለው፣ ስኒ ደርድረው፣ ቄጠማ ጎዝጉዘው ቢመርቁት አያስገርምም፡፡  በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ እግዚአብሔር እያፈረሰ፣ ቤተ ፓስተር እየገነባ ስለሆነ፣ ቤተ ፓስተራቸውን አስገንብተው የዋህ መንጎቻቸውን ሙልጭ እርገው እየዘረፉ በብርሃን ፍጥነት የናጠጡት ፓስተሮች እየሱስ የቀባው ነው እያሉ ቢሰብኩለትና ቢጸልዩለት አይፈረድባቸውም፡፡  አንተ አቶ ደመቀ መኮንን ግን እመራዋለሁ የምትለውን አንበሳውን የአማራን ሕዝብ በወያኔና በኦነግ ጅቦች ያስበላህ፣ ቢያንስ ቢያንሰ በአመራር ፈተና የወደቅክ፣ ለቋንቋየ ይቅርታ ይደረግልኝና ውድቀታም (loser) ነህ ብትባል አግባብ አይመስልህም?   

የአቶ ደመቀ በዚሁ ይብቃንና፣ በዐብይ አሕመድ የድርድር ተውኔት ላይ ትልቅ ሚና ሊጫወት ወደተዘጋጀው ወደ አቶ ተመስገን እንዙር፡፡  ይህ ግለሰብ ነገረ ሥራው ሁሉ የረዥም ጊዜ ባልደረባው የነበረውን ዐብይ አሕመድን ለማስደሰት ጠብ እርገፍ ማለት ስለሆነ፣ ከዐብይ አሕመድ ጋር የተለየ ግንኙነት ያለው ያስመስልበታል፡፡  ለዚህ ይሆናል ወዳጁ ዐብይ አሕመድ ከባሕርዳሩ ጭፍጨፋ በኋላ ለሱ በማይገባው በዶክተር አምባቸው ወንበር ላይ ያስቀመጠው፡፡  በዲባቶ አምባቸው ወንበር ላይ በተቀመጠ ማግስት ደግሞ ፋኖን እያሳደደ መግደልን ዋና ሥራው አድርጎ ተያያዝከው፡፡  የጀነራል አሳምነውን ልዩ ኃይል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በማፈራረስ፣ የአማራ ብሔርተኝነት ያሰጋኛል ያለውን ዐብይ አሕመድን ለማስደሰት ብዙ ርቀት ተጓዘ፡፡  ሽመልስ አብዲሳ የዝዋይና የሻሸመኔ አማሮችን ቆዳ ስላስገፈፈ ብቻ አድናቆቱን ለመግለጽ ባሕርዳር ድረስ ጠርቶ ካባ ሸለመው፡፡  የአማራን ሕዝብ እነ ሽመልስ አብዲሳና ታየ ደንድኣ የሚዘልፉት ሳይበቃ፣ እሱ ደግሞ ‹‹ወንጀለኞችን የሚያወድስ ማሕበረሰብ›› በማለት በብአዴን ምክር ቤት ውስጥ ተሳለቀበትና፣ የአለምነው መኮንንን ስድብ ደገመው፡፡     

ወያኔና ኦነግ እስካፍንጫቸው በሚታጠቁበት ጊዜ የአማራ ሕዝብ ራሱን ለመከላከል እንዳይታጠቅ አንቆ መያዝ ብቻ ሳይሆን፣ የታጠቀውንም እንዲፈታ የቻለውን ሁሉ አደረገ፡፡  ይህን ሁሉ ካደረገ በኋላ ደግሞ የአማራ ሕዝብ ዱላ ይዞ ድሽቃ ከታጠቀው ከወያኔ ጋር ሲፋለምና እንደ ቅጠል ሲረግፍ ለማየት የቋመጠ ይመስል፣ ከጦርነቱ አስቀድሞ ወያኔን እንሰብረዋለን እንቀብረዋለን እያለ የፌስቡክ ጉራውን እያከታተለ ነዛ፡፡  በዚያ ደረጃ ሲፎክር የነበረው ሰው ደግሞ፣ ወያኔ ሸዋን ከወረረ በኋላ ከወያኔ ጋር ለመደራደር አቆብቁቦ የዐብይ አሕመድን ትእዛዝ በተጠንቀቅ ይጠባበቅ ጀመር፡፡  በዚህ ቀውጢ ወቅት እንኳን በመረጃ ድርጅት ኃላፊነቱ ሙሉ ትኩረቱን ያደረገው በወያኔና በሸኔ ላይ ሳይሆን የአማራ ገበሬ የታጠቀውን ነፍስ ወከፍ መሣርያ በመመዝገብ ላይ ነው፡፡  ዓይኑ ደም የሚለብሰው የኦነግን ድራጉኖቭ ወይም የወያኔን ድሽቃ ሲየይ ሳይሆን የአማራን ጓንዴ ሲመለከት ነው፡፡  ባጭሩ ለመናገር ይህ ግለሰብ የዐብይ አሕመድ ጃንደረባ ነው፡፡  በዚያ ላይ ደግሞ ከጦር ሜዳ የማይገኝ ከቀለብ የማይጠፋ ቱሪናፋ ነው፡፡

ስለዚህም አቶ ደመቀና አቶ ተመስገን ሁለቱም በአማራ ሕዝብ ላይ ትልቅ ወንጀል የፈጸሙ ወንጀለኞች እንጅ የአማራ ሕዝብ ተወካዮች አይደሉም፣ ሊሆኑም አይችሉም፡፡  ባለመሆናቸው ደግሞ በአማራ ሕዝብ ስም ከጠላቶቹ ጋር ይቅርና ከወዳጆቹም ጋር የመደራደር መብት የላችውም፡፡  በመጀመርያ ደረጃ የአማራ ሕዝብ ከወያኔ ጋር አይደራደርም፣ አጥፊና ጠፊ ናቸውና፡፡  የአማራ ሕዝበ ከዐብይ አሕመድና ከብኣዴናዊ ሎሌወቹ ከተላቀቀ ደግሞ፣ ከወያኔና ከአማራ ሕዝብ ማንኛው ጠፊ ማንኛው አጥፊ እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡  

ስለዚህም ለአቶ ደመቀና ለአቶ ተመስገን ለሁለታችሁም የሚበጃችሁ፣ ተደራደሩልኝ ብሎ ባልጠየቃችሁ በአማራ ሕዝብ ስም በዐብይ አሕመድ የድርድር ተውኔት ላይ በመሳተፍ ከዚህ ቀደም በፈጸማችሁት ከፍተኛ ወንጀል ላይ ከፍተኛ ወንጀል ባትጨምሩበት ነው፡፡  አለበለዚያ ግን አማራ እጅ ላይ የወደቃችሁ ጊዜ ማጣፊያው ያጥራችኋል፡፡  እንደ ሸንኮራ አገዳ የሚያኝካችሁ ዐብይ አሕመድ ጣማችሁ ሲያልቅ አንቅሮ ተፍቶ አሳልፎ እንደሚሰጣችሁና አላውቃችሁም እንደሚላችሁ ደግሞ በደንብ ታውቃላችሁ፡፡ 

ለአማራ ሕዝብ የሚበጀው ደግሞ አቶ ደመቀ መኮንንና እና አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንዲሁም ዳግማዊት ሞገስንና ብናልፍ አንዷለምን የመሳሰሉት የነሱ ብአዴናዊ ጀሌወች፣ በአማራ ሕዝብ ላይ ለፈጸሟቸው ከባድ ወንጀሎች ጊዜው ሲደርስ የሚጠየቁ ወንጀለኞች እንጅ፣ የአማራ ሕዝብ ወኪሎቹ እንዳልሆኑና በነሱ የተፈረመን ማናቸውንም ስምምነት እንደማይቀበለው ማወቅ ለሚገባቸው ሁሉ አስቀድሞ ማሳወቅ ነው፡፡ 

 Email’; መስፍን አረጋ mesfin.arega@gmail.com

 

Filed in: Amharic