>

"የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ አካል እንጅ የህዉሃት ርስት ወይም የአዳነች ጭሰኛ አይደለም....!!!" ( ሸንቁጥ አየለ)

“የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ አካል እንጅ የህዉሃት ርስት ወይም የአዳነች ጭሰኛ አይደለም….!!!”
ሸንቁጥ አየለ

 *,… ቁርጡን እወቁት ትግራይ አትገነጠልም። ህዉሃትም ሆነ ኦህዴድ ከነ ጎሳ ህገ-መንግስታችሁ ከኢትዮጵያ ትነቀላላችሁ። ኢትዮጵያም እናንተ ስትጠፉ ረፍት ታገኛለች” ሲል የኢትዮጵያ ህዝብ ፍርዱን በልዩ ልዩ መልክ ገልጿል:-
 
ሀገር ለመመስረት ስንት ዋጋ እንደተከፈለ የካዱት የኦህዴድ እና የህዉሃት ፖለቲከኞች ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ያላቸዉ ግንዛቤ በጣም ያሳዝናል።
የኢትዮጵያን ዋጋ የሚለኩት እነሱ ህገ መንግስት በሚሉት ወረቀት መሆኑ ያስገርማል። በዚህ ጉዳይ ላይ ኦህዴድም ህዉሃትም ያላቸዉ ግንዛቤ አንድ ነዉ። ዛሬ የአዳነች አበቤ ንግግር ብዙ ሰዉን ቢያስገርምም ርጉሙ መለስ  ልክ እንዳዳነች ሁሉ ህገመንግስቱን እየጠቀሰ “ኦሮሚያ ከፈለገ በህገመንግስቱ መሰረት መገንጠል መብቱ ነዉ” እያለ ይቀናጣ ነበር።
አሁን ደግሞ ተራዉ የአበቤ ሆነና ህዉሃት ከፈለገች እራሳቸዉ ባወጡት ህገመንግስት መሰርት ጥርግ ይበሉ እያለች  በሰፊዉ ፈገግ እያለች በህዉሃቶች ላይ ተሳልቃባቸዋለች። መለስ ዜናዊ ድሮ የሚያስፈራራዉ አማሮችን ነበር። ኢትዮጵያን እናፈርስላችኋለን እያለ። ሆኖም ታሪክ ስላቅ እና በቀል ይችላል እና ዛሬ ኦህዴድ የመለስ ፓርቲን በህገመንግስታችሁ መሰርት ሂዱልን ባይ ሆኗል። ይሄኛዉ ሰዓት ግን አዳነችን አበቤ ማንንም እያስፈራራች ሳይሆን ካልተገነጠልኩ እያለ ቡራ ከረዩ የሚለዉን ህዉሃትን ከፈለግህ ሂድ እስከማለት ዘልቃለች። የታሪክ ስላቅ እና በቀል ማለት ይሄ ነዉ።
እነ አዳነች ከዚህ በኩል ከፈለጋችሁ ትግራይን ገንጥላችሁ ሂዱልን ይላሉ። በወዲያ በኩል  ኢትዮጵያን በታትነን ትግራይን ገንጥለን እንሄዳለን እያሉ ኢትዮጵያዊነት ላይ ብዙ ስድብ ያዘንቡ የነበሩት እነ እስታሊን ደግሞ በአዳነች አበቤ ንግግር ብስጭት ብስጭት ብለዉ “የትም አንሄድም የትም አንገነጠልም። አንሄድም አንሄድም ” እያሉ ብራ ከረዩ እያሉ ነው።
======
እኔን ታዲያ ፈግግ ብዬ እንድጽናና ያደረገኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁለቱንም የገሰጠበት ስልት ነው። ” አዳነች አንችም ልክ አይደልሽ። ሀገር ትዳር ነዉ እንዴ ዝም ብሎ ሂጂ ሂድ ይባላል እንደ?” ብሎ አዳነች መሳሳቷን ገስጿል።
ይሄዉ ህዝብ ደግሞ ዞር ብሎ እነ እስታሊንንም በቁጣና በርግማን ልካቸዉን ነግሯቸዋል። ” እስታሊን ሁላችሁም ህዉሃቶች ተገንጥለን እንሄዳለን ፡ ኢትዮጵያን እናፈርሳለን እያላችሁ ከበሮ ስትደበድቡ አልነበር እንዴ? እና ዛሬ አበቤ ሂዱ ስትላችሁ ምነዉ ተናደዳችሁ?
ለማንኛዉ የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ አካል እንጅ የህዉሃት ርስት ወይም የአዳነች ጭሰኛ አይደለም ። ትግራይ አትገነጠልም። ህዉሃትም ሆነ ኦህዴድ ከነ ጎሳ ህገመንግስታችሁ ከኢትዮጵያ ትነቀላላችሁ።ኢትዮጵያም እናንተ ስትጠፉ ረፍት ታገኛለች” ሲል የኢትዮጵያ ህዝብ ፍርዱን በልዩ ልዩ መልክ ገልጿል።
አዳነች አበቤንም እስታሊንንም  ህዝብ ገስጿል። የሀገር ምስረታ ታሪክ እንዲህ የጎሳ ፖለቲከኞች እንደሚያስቡት ሂድ ፡ ና  የሚባል ጉዳይ እንዳልሆነም ህዝብ  የፖለቲካ ትምህርት አስተምሯል። ህዝብ ህዉሃትም ሆነ ኦህዴድ እንደማያደምጡት ቢያውቅም ሌሎች ይማሩበት ዘንድ ብይኑን አስቀምጧል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለኦህዴዷ አዳነች አበቤ እና ለህዉሃቱ ስታሊን ካሁን ብኋላ ስለ ቅድስት ኢትዮጵያ በሚነጋገሩበት ጊዜ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።ይሄ ማስጠንቀቂያ ግን ለአዳነች አበቤና ለስታሊን ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ነዉ። ኢትዮጵያን የሚጻረር ሀሳብ ላላቸዉ ሃይሎች ሁሉ ነዉ እንጅ።
————–
 ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች እንዳለ ቅዱሱ መጽሃፍ ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይጠብቃት
Filed in: Amharic