የቆማሪው አብይ እያነቡ እስክስታ….!!!
አሳፍ ሀይሉ
የቄሮው ፈጣሪና የበላይ ጠባቂ ነኝ ባዩ ተረኛ ገዢ ቡድን መጀመሪያ “ለውጡን እኔ ነኝ ያመጣሁት” አለ። ሲል አንደኛ የሚያምነው አጣ። ሁለተኛ አመጣሁት ባለው ለውጥ የያዘውን ዙፋን ብቻውን ሊያስጠብቅ ነው። ሲያስበው ደከመው። ፈራ።
ስለዚህ ኃይል ማሰባሰብ ያዘ። ኦነግን ከኤርትራ ጠራ። በሞያሌም በባሌም ጠራ። ሸኔን ጠራ። ቄሮን ጠራ። ኦህዴድን ጠቀለለ። ጋኔኑን ሁሉ ጠራ። ያም ሆኖ ብቻውን አድዋ ድረስ ዘምቶ እንደማይዋጋ፣ አባይንም እንደማይሻገር፣ አቅሙን አወቀ።
ስለዚህ መሸሸጊያ ዋሻ (host) ፈለገ። በመጀመሪያ አጋር ፓርቲዎችን አባል ሆናችኋል አላቸው። ጥቂት ቆይቶ ሁላችሁም ብልፅግና ሆናችሁ ተዋህዳችኋል አላቸው። እና አንዱ ከሌላው በማይለይበት በብልፅግና ጥላ ስር ተሸሽጎ የተረኝነት አምሮቱን በብሔር ብሔሮች ስም ለመቀጠል ተሟሟተ።
ግን ኢህአዴግን የጠላ ሕዝብ በምን አንጀቱ ብልፅግናን ይሸከምለት? በዘመነ ኢህአዴግ የየጎሳው መሳፍንት ናችሁ ተብለው በሞኖፖል በየብሔራቸው ላይ ተሰክተው የቻሉትን ጥቅም የሚመጠምጡትና፣ አሁን “ብልፅግና” የሚባል ግንጥል ካባ የተደረበላቸው የየብሔሩ ጌቶች እንዴት ብለው ይደባለቁ?ተረኛ ነገር ተደበላለቀበት። ድብልቅልቁ አቃተው።
እና ሌላ ተረኝነቱን ማስቀጠያ ምሽግ ሲፈልግ “ኢትዮጵያ” የሚሰኝ መፈክር አገኘ። ዘሎም ተሰካበት። “ኢትዮጵያ” “ኢትዮጵያ” እያለ ቢያንጎራጉር በኢህአዴግ ባልተበላበት ጭልፋ እልፍ መናጆ (ተከታይ) እንደሚዘግን አሰበ።
እና “ለውጡን እኔ ነኝ ያመጣሁት!” ከሚል የኩሽ ፖለቲካው፣ በአንዴ ወደ “ኢትዮጵያዊኛ ፖለቲካ” ተከርብቼዬለሁ ብሎ ለፈፈ። በኢትዮጵያነት ጥላ ተከልሎም ባንድ እጁ እያረደ፣ በሌላ እጁ መንበሩ ላይ ሊሞጭጭ ተጋጋጠ። ይሄም ግን አልሠራለትም። ከጠራቸው ጋኔኖቹም ጋር ተላተመ።
በመጨረሻ ሁሉም ሲስተም እንደተበላበት ሲባንን፣ “የአፍሪካ ነፃ አውጪ ነኝ!” የሚል አዲስ ጭምብል አጥልቆ ደግሞ ወዲህ ወዲያ ደጋፊ ለማግኘት እያዘጠዘጠ ነው።
አሁን የለውጡ ሃዋርያ ነኝ ባዩ ተረኛ ገዢ “አፍሪካዊ መፍትሄ ለአፍሪካውያን!” የሚባለውን የአፍሪካ አምባገነኖች “ሌላው ዓለም በጭራቅነታችን አይግባብን!” ብለው ለመሠረቱት የአፍሪካ መናፍቃን እድር… አፈቀላጤ ሆኖ ለመሰንበት ደሞ ተሟሟተ። “የአፍሪካ ጠባቂ ነኝ!” አለ።
ዓይኑን በጨው እጥብ አድርጎ፣ “አሜሪካና አውሮፓ አይገዙንም!” “እኔ አፍሪካን ወክዬ ነው ከሀያላን ጋር እየተጋፈጥኩ ያለሁት!” ብሎ፣ የሥልጣን ተረኝነት ጥማቱን በአፍሪካዊ ዥንጉርጉር መጋረጃ ሊሸፍነውና በቋመጠበት ቤተመንግሥት ተጣብቆ ሊቀር እየተጋደለ ይገኛል አሁን።
በዚህ አያያዙ ተረኛው ሀይል የቀረው “የዓለም ወኪል ነኝ!” ማለት ብቻ ነው። እሱንም ከቻይና በተውሶ የተገኘን መንኮራኩር ወደ ምድር ዛቢያ አመጠቅኩ ብሎ የዓለሙ ተዋናይ ነኝ ሊል ዳር ዳር ብሎ አፍሮ የተወው ይመስለኛል። ወይ እንደ ሰሜን ኮርያ የሚተኩሰው የኑክሊየር አረር ቢኖረው – ቢያንስ የዓለምን ዓይኖች ለመሳብ ስለሚጠቅመው – ምኞቱ ይሰምርለት ነበር።።
አሁን “የዓለም ጭዌው” ተበልቶበታልና ከቶማስ ሳንካራ ጋር ነው “ጭዌው”። ሰባተኛውን ንጉሥ ቀይ የወታደር መለዮ (ኮፍያ) አድርጎ ፎቶ በማስነሳት ከሆነ አዎ። ከቶማስ ሳንካራ ጋር አንድ ነው።
ግን በየት በኩል? አንድ በሥልጣን መንበር ምኞት አቅሉን የሣተ ተረኛ አረመኔ፣ “አማራ ገዛ፣ ትግሬ ገዛ፣ ጊዜው የኔ ነው!” ብሎ ዘር እየመረጠ የሚያርድና የሚያፈናቅል ጨፍጫፊ ጭራቅ፣ በምን መሥፈርት ነው ከአፍሪካ ነፃ አውጪ ጋር ራሱን የሚያስተያየው? የሚወክለው አፍሪካስ የትኛውን አፍሪካን ይሆን?
“ሳይቸግር ጤፍ ብድር” ሆኖበታል አሁን ተረኛው። “አቤቤ ጣይቱ ነች!” እየተባለች ነው። አዲሳባን ሙልጭ አድርጋ የዘረፈችውና የጣይቱን ሀውልት የከለከለችው፣ የፊንፊኔ ኬኛዋ አቤቤ ጣይቱን ሆናለች። ሰው ግን ትንሽ እንኳን እፍረት shame ምናምን አይቆነጥጠውም?!
የቴዎድሮስን ፅዋ እንጠጣለን የሚሉ፣ ግን የሕዝብ ደም እየጠጡ፣ ከወንበር ወደ ወንበር የሚሽከረከሩት አውታታዎች የተረኛውን መንበር ከበው እያሸበሸቡለት ነው።
በመጨረሻ የተጠመጠመባትን የናፍቆት መንበር ጥሎ ወደተነሳባት ቄሮነቱ መመለሱ፣ አሊያም ያቅሙን ታህል መንበሬን ክብሬን ብሎ መንደፋደፉ የማይቀር ነው።
ሰባተኛው ንጉሥም ወይ ወደ በሻሻ፣ ወይ ወደ አሩሻ፣ (ታንዛኒያ)፣ ወይ ወደ ራሻ (አለች አሻ!) እግሬ አውጭኝ ብሎ ማምለጡ የማይቀር ክስተት እየሆነ ይመስላል። በቅርቡ የቱን ሆኖ እንደሚገኝ በተግባር እናየዋለን።
እስከዚያው ከለውጡ ብቸኛ አምጪ ተረኛ exclusive የብሔር ገዢነት ወጥቶ – “አፍሪካን እጠብቃለሁ” ያለውን አስቂኝም አስደንጋጭም የንፁሃን ዜጎቹን ደም የሚጠጣ ቀልደኛ ቫምፓየር እውነተኛ ፊልም እያዩ አለመደሰትም፣ አለመደንገጥም የሚቻል አይደለም።
ዘመኑ የትራጀዲክ ኮሜዲ (የtragicomedy) ተውኔት በእውን የሚታይበት ዘመን ሆኗል። የተመልካቹ ንቃተ-ህሊና ደግሞ ከተዋናዮቹ ተረኞችም ያነሰ መሆኑ የትዕይንቱን አሳዛኝነትም፣ አስቂኝነትም አጉኖታል።። ምን ይደረግ? ምንም! ትያትሩ ገቢሮቹን ሁሉ አሟጦ እስኪጨርስ እየሣቁና እያለቀሱ መጠበቅ ብቻ!
ዘፋኙ “እያነቡ እስክስታ” እንዳለው ነው የሆንነው። ዓለም ትያትር ነች! ሰዎቿም ተዋናዮች ናቸው። እና ታዳሚዎችም፣ ሰለባዎችም። “እያነቡ እስክስታ”። That’s the Tragicomedy of our time.
መልካም ትያትር!