ምኒሊክ ውቃቢ ነው…!!!
ድንበሩ ደግነቱ
*…. ኢሕአደግ ባንዲራዋንም፣ አድዋንም፣ ሚኒሊክንም ሲያንኩዋስስ ቆይቶ፣ በባድመ ጦርነት ወቅት ሙጥኝ ያለው የሚኒሊክ መንፈስ የሆነውን አድዋንና አረንጉዋዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራን ነበር። ሁልጊዜም የሚኒሊክ ውቃቢ ያደረባቸው፣ እንደንብ ያበሩ ኢትዮጵያውያን አገራቸውንም ኢህአደግንም ከአደጋ ከለሉዋቸው።
ውቃቢ በተለይ በኦሮሞ ኅብረተሰብ ዘንድ ጎልቶ ይታወቃል። ውቃቢ በዐካል ታይቶ የማይታወቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ትርክት ያዳበረው፣ ሳይታይ ሳይሰማ የሰዎችን ልመና የማስፈፀም ችሎታ ያለው የመንፈስ ኃይል ነው።
በተቃራኒው ሚኒሊክ በዐካል የነበረ፣ ትዕዛዝ ሰጥቶ ማስፈፀም የቻለ፣ እንደሰው እህል ሳይቀምስ የማይውል፣ የሚናደድ፣ የሚደሰት፣ ስቅስቅ ብሎ የሚያለቅስ፣ ጦር ሜዳ ውሎ አገር የጠበቀ ሰው ወይም የሰው አውራ ነበር። ቢሆንም ግን ሚኒሊክ ኢትዮጵያውያን ላይ የሰፈረ ውቃቢ ነው። ይሄን እኔ አልፈጠርኩትም። ጳውሎስ ኞኞ ሲል የሰማሁት ነው። ጳውሎስ የሚኒሊክ ውቃቢ አድሮብኛል ይል ነበር። በአፉ አልተናገረውም እንጂ ቴዲ አፍሮም በኢትዮጵያውያን ላይ የሚኒሊክ ውቃቢ እንዳደረባቸው አንድ ማሳያ ነው። ቴዲ ለዚህ የሚኒሊክ ውቅቢ ያልገበረው ግብር የለም። በሀሰት ክስ ለዘመናት ፍርድ ቤት ተንከራቶዋል። Solitary confinement ውስጥ ተቀርቅሮ አበሳውን አይቶዋል። ለዚህ ውቃቢ በመስገዱ ምክንያት ትልቅ ገቢ ተሰናክሎበታል። ቢታሰርም፣ ቢጉላላም፣ ሀብት ቢያጣም ቴዲ ውቃቢው ምኒልክን አሁንም ሙጭጭ ብሎዋል።
አድዋ ሚኒሊክ ካበረከተልን ታላላቅ በረከቶች (achievments) አንዱ ነው። ኢትዮጵያውያንን አንድ አርጎ አምኖና ታምኖ ባያሰልፍ ኖሮ፣ አድዋ ድል ሳይሆን የውርደት ቦታ በሆነ ነበር። አድዋ አድዋ ባልነበር፣ ሚኒሊክ እንደ አባቱ ዮሐንስ፣ አንገቱ ተቆርጦ ይወሰድ ነበር፣ ወይም እንደ አባቱ ቴዎድሮስ ሽጉጡን ይቀመቅም ነበር። ምኒልክና የኢትዮጵያ ባንዲራ ከአድዋ ይገዝፉ እንደሆነ እንጅ አያንሱም።
ኢሕአደግ ባንዲራዋንም፣ አድዋንም፣ ሚኒሊክንም ሲያንኩዋስስ ቆይቶ፣ በባድመ ጦርነት ወቅት ሙጥኝ ያለው የሚኒሊክ መንፈስ የሆነውን አድዋንና አረንጉዋዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራን ነበር። ሁልጊዜም የሚኒሊክ ውቃቢ ያደረባቸው፣ እንደንብ ያበሩ ኢትዮጵያውያን አገራቸውንም ኢህአደግንም ከአደጋ ከለሉዋቸው።
ቤተክህነት ከሚሄዱ እህቶቻችን ቀሚስ እጅጌ ላይ ባንዲራችንን ቀፍፈው ያወጡ የታሪክ ባለጌዎች፣ ሚኒሊክ ጡት ቆራጭ ነው ብለው በፈጠራ ወሬ ኢትዮጵያውያን ሲተላለቁ እንዲኖሩ ብዙ ብር አውጥተው ሐውልት ያቆሙ ነውረኞች፣ ጭንቅ ሲይዛቸው ጊዜ በአድዋና በባንዲራው እየተማፀኑ ነው። አሁንም የሚኒሊክ ውቃቢ በናንተ ልክ አይደለም። የሚኒሊክ ውቃቢ ለኢትዮጵያም ለእናንተም ይመክትላችሁዋል። እናንተም በፋንታችሁ አድዋን ጠርታችሁ የምኒሊክን ስም መጥራት አይነቃችሁ። ምኒልክን ይቅርታ ጠይቁትና የአኖሌን ሐውልት አፍርሱት! ለጊዜው ትተርፋላችሁ!
አዳነች አቤቤን ከጣይቱ ያመሳሰላችሁ ሰዎች ግን፣ ጣይቱን ባዋረዳችሁበት ልክ ምግብ ቀርቦላችሁ በልታችሁ ከሆነ ፈንድታችሁ ትሞታላችሁ እንጂ ጣይቱ አትቆሽሽም፣ አዳነችም አትጠራም። ዳግማዊ ጣይቱን እግዚአብሄር ለኢትዮጵያ የሰጣት ቀን፣ የሰው ሕይወት እንደአሁኑ አይረክስም።