>

ኬንያና አሜሪካ እየመከሩልን ወይስ እየዶለቱብን....!!!   (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

ኬንያና አሜሪካ እየመከሩልን ወይስ እየዶለቱብን….!!!  

ኢትዮጵያ ኢንሳይደር


የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚል እምነት እንዳላቸው የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ራይቼል ኦማሞ ይህን እምነታቸውን የገለጹት፤ ከአሜሪካ አቻቸው አንቶኒ ብሊንከን ጋር ዛሬ ረቡዕ ህዳር 8 በናይሮቢ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

በሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መግለጫ የታደሙ ጋዜጠኞች ያነሷቸው ጥያቄዎች በዋናነት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ነበሩ። የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “ለዚህ ቀውስ መፍትሔ ለማግኘት ኢትዮጵያ ባላት አቅም እናምናለን። ተኩስ ማቆም ይቻላል ብለን እናምናለን” ሲሉ ተናግረዋል።

አንቶኒ ብሊንከን ከኬንያ አቻቸው ጋር በጋራ መግለጫ ከመስጠታቸው አስቀድሞ ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አሁሩ ኬንያታ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። አሁሩ ባለፈው እሁድ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር መምከራቸው ይታወሳል።

አሁሩ እና ብሊንከን የኮሮና ወረርሽኝ፣ የከባቢ አየር ለውጥ እንዲሁም የቀጠናውን ሰላም እና ጸጥታ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ እንደተወያዩ የኬንያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። የኬንያው ፕሬዝዳንት እና የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዚሁ ውይይታቸው፤ “የቀጠናውን ግጭቶች ለመፍታት እና በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም በማምጣት ረገድ” ሊተባበሩ የሚችሉባቸውን ዕድሎች እንደፈተሹ መግለጫው ጠቁሟል።

Filed in: Amharic