>

ያልጠረጠረ ተመነጠረ...!!! (እየሩሳሌም  እመዋ)

ያልጠረጠረ ተመነጠረ…!!!

እየሩሳሌም  እመዋ

ጦርነቱ በድንበር ላይ የሚደረግ ውጊያ አይደለም ተበተነ ወይም ተደመሰሰና ለቆ ወጣ እየተባለ ጠላት እየቀረበ ያለ የመሆኑ  ዜና መፈተሽ ያለበት ጉዳይ ነው። ምክንያቱም የወራሪው ኃይል ተደመሰሰ እየተባለ አፍንጫችን ሥር ገብቶ እያየን ስለሆነ ነው።ይህ ብቻም አይደለም አሳዛኙ ክስተት አሸንፈናል ይዘናል የተባሉ ቦታዎች  መልሶ ጠላት ተቆጣጠረው የሚባለው ዝክረ- ዜና የኢትዮጵያን ሕዝብ ልብ እየሰበረው መጥቷል።
ኢጣሊያ  አመታት ተደራጅቶ ከቆየ በኋላ የተከፈተው  የአድዋ ጦርነት በጀግኖች  አባቶቻችን  ቆራጥ ተገድሎ በ6 ሰዓታት ውስጥ የጠላትን ኃይል ድባቅ በመምታት ለወሬ ነጋሪ ያሳጡት “በአፍግፍግ “የጦርነት ስልት ሳይሆን “በግፋ በለው” ቆራጥ ወኔ ነበር እስከዛሬ በዓለም ታሪክ ውስጥ በደማቅ ቀለም ተፅፎ የምናገኘው።
 ዛሬም ኢትዮጵያ የጀግኖች መፍለቂያ እንጂ የአልጫ ወንድ መፈጠሪያ አይደለችም።ነገርግን ሰሞኑን እየተካሔደ ባለው ጦርነት ብዙ ዋጋ ተከፍሎበት ከተያዙ ገዥ ቦታዎች ጦሩ እንዲያፈገፍግ እየተደረገ ከወልዲያ የተጀመረው ማፈግፈግ ሸዋ ሮቢት ደርሷል እየተባለ ነው።ሌላው በቀር የመጣበትን ወራሪ ጠላት ሕዝቡ ተደራጅቶ እንዳይዋጋ እኛ እንበቃለን እናንተ አታስፈልጉም እየተባለ የሕዝቡን ሞራል በማድቀቅ ጭምር የሕዝቡን ተነሳሽነት እንዲቀንስ ከማድረጉም በላይ ጦርነቱ ወደፊት ከመግፋት ይልቅ አካባቢው እየተያዘ የሕዝቡ ሰቆቃ እንዲጨምር መደረጉ በስፋት እየተሰማ ይገኛል።
 ሽፍታውና ዘራፊው ቡድን በ1983 ዓ.ም ኢትዮጵያን ሊቆጣጠር የቻለው  ዛሬም ለመድገም በሚጥራቸው አራት ዋና ዋና ዘዴዎች ተጠቅሞ እንደነበር ያስታውሰኛል:-
 *1ኛው/ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን በገንዘብ ደልሎ አቅጣጫ በማስለወጥ ያልተፈለገ አመራር እንዲሰጥ በማድረግ ገዥ ቦታዎችን ጦሩ እንዲለቅ ወይም እንዲያፈገፍግ በማስደረገ ፣
+2ኛው /የሐሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛትና
+ 3ኛው /በአሜሪካ መንግሥትና በሌሎችም የኢትዮጵያ ጠላቶች እየታገዘ ነው፤
 +4ኛውና የመጨረሻ ዘዴው በከፍተኛ የአመራር ቦታዎች ላይ የራሱ ሰዎችን በማስቀመጥና መንግሥታዊ ሚስጢሮችን በፍጥነት በማግኘት  እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው።
ዛሬም ይህንን ተግባሩን አጠናክሮ እየቀጠለ እንደሚገኝ በግልፅ እየታየ መጥቷል።ምክንያቱም ከራያ ጀምሮ ሸዋ ሮቢት ዘልቆ ሲገባ በምን ምክንያት ነው?የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ የግድ ነው። ብዙ ደጀን ያለው ሕዝባዊ ጦር ወደፊት መግፋት እንዴት አቅቶት ማፈግፈግ ቻለ ለሚለው ጥያቄ መንግሥት በቂ መልስ መስጠት ይጠበቅበታል።ወደድንም ጠላንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ጦርነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተዋግቶ ድል ለማድረግ በከፍተኛ ሞራል ተነሳስቶ በደጀንነት  በተጠንቀቅ ቆሞ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ እንዲህ ያለ ነገር መከሰቱ እጅግ አሳዛኝ ነገር ነው። ይህን ያክል የሕዝብ ማዕበል ተነስቶ ባለበት አገር ውስጥ ጦርነቱ እንዲጓተት የሚያደርጉ አካላት በታሪክ ተጠያቂዎች ቢሆኑም ጦርነቱ ሕዝባዊ ስለሆነ የግድ  በአጭር ጊዜ ውስጥ መቋጨቱ የግድ ነው።ይህን ያክል  ደጀን ሕዝብ በቆራጥነት ተነስቶ አገሬን አላስደፍርም ብሎ በተነሳበት አገርና በበቂ ትጥቅና ስንቅ የተደራጀ  ጦር ባለበት  ጦሩ እንዲያፈገፍግ የሚያደርጉ አካላት በጦሩ የእዝ ሰንሰለት  ውስጥ መኖራቸው ጦሩን የሚያዳክም የጠላት እጅ በጦሩ መሐል የገባ መሆኑን  ያመለክታል። ይህ አካሔድ በዚህ አይነት እየቀጠለ ሲደጋገም ለምን መፍትሔ አልተፈለገለትም የሚለውን ጥያቄ ማስከተሉ የግድ ነው።በዚህ ረገድ የተፈጠረው አሻጥር  በአጭሩ መፍትሔ ያላገኘበት ዋናው ምክንያት በላእላይ መዋቅሩ የጦር አመራሮች አካባቢ ተሰውሮ የተቀመጠ በሁለት ቢለዋ የሚበላ አደገኛ ሰው መኖሩን ያመለክታል።እንዲህ ያሉ ሰዎች እስካሉ ድረስ ጦርነቱ ፈፅሞ ወደፊት ሊገፋ አይችልም። እንዲያውም እንደነዚህ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች አዲስ አበባ ተከባልች ፣ ከፍተኛ የደም መፍሰስ የሚያስከትል የሕዝብ እልቂት ሊኖር ስለሚችል ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ከሚውተረተሩ አገሮች ጋር የተቀናጀ መስመር ፈጥረው በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ የሥለላ መዋቅር ውስጥ  አባል ሆነው ተልዕኮ እያስፈፅሙ ሊሆኑ ስለሚችሉ ምናልባት እስከ መንግሥት ግልበጣ የሚደርስ የሴራ  እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ስለሚችሉ መንግሥት ቶሎ በመንቃት አስቸኳይ መፍትሔ ማፈላለግ ይጠበቅበታል።አሜሪካና እንግሊዝ  በስለላ መዋቅራቸው ስፋት አንፃር እኛ ያልደረስንባቸውን ብዙ ነገሮች ያውቃሉ።ለዚህም ይመሥለኛል ዜጎቻቸውን በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ሲጎተጉቱ የሚታዩት።ወያኔም ይዤአለሁ የሚለውን ቦታ ሁሉ እየያዘ ሸዋ ሮቢት ድረስ ዘልቋል።እስከ ሸዋ ሮቢት የደረሰው በጦርነት የበላይነት አግኝቶ ሳይሆን በአሻጥር እንደሆነ ግልፅ ነው።ነገርግን የአፋርና አማራ ሕዝብ ከምን ጊዜውም በላይ የትግራይ ወራሪን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከምድረ ገፅ አጥፍቶ ለማረፍ  ቆርጦ የተነሳ በመሆኑ ለወራሪው ኃይል ሁኔታዎች ምቹ ሊሆኑለት አልቻሉም እንጂ እንደ ሴረኞቹ ዓላማ ቢሆን ኖሮ እንደፎከሩት አዲስአበባን በተቆጣጠሩም ነበር።የትግራይ ወራሪ ኃይልም ሆነ የሱ አናጓዥ የሆኑ አሜራካና ሌሎች ጠላቶቻችን ይህን ሕዝባዊ የቁጣ ወላፈን ፈፅሞ ሊገቱት አይችሉም። መንግሥትም ለምን ይህ ጦርነት እስከ ሸዋ ሮቢት ድረስ ዘልቆ መግባት ቻለ የሚለውን አካሔድ በፅሞና ገምግሞ የማስተካከያ እርምጃ መውስድ   ይገባዋል።
Filed in: Amharic