አቻምየለህ ታምሩ
ይህ ወቅት ከስሜት ሳይሆን ከምክንያት ተነስተንና ቀልብን ሰብሰብ አድርገን የምናስብበት ጊዜ ነው። የፋሽስት ወያኔ ወራሪ አንበጣ ሠራዊት የከፈተብንን የግፍ ጦርነት እንደ ዓድዋና ማይጨው ጦርነት ዘልሎ በመግባት የምንመልሰው አይደለም።
ፋሽስት ወያኔ እያካሄደ ያለውን የግፍ ወረራ ለመቀልበስ የሰለጠነ ወታደር፣ ደፍጥጦ የሚያነድና ረጅም ርቀት የሚገኝን ኢላማ የመምታት ብቃት ያለው ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ ተዋጊ ያስፈልጋል። በመንግሥትነት የተሰየመው አካል ዋነኛ ሥራው የወገን ጦር በትጥቅና በስልጠና በሙሉ ቁመና ላይ እዲገኝ ማድረግና እመራዋለሁ የሚለው መንግሥት ወረራውን ለመቀልበስ አቅሙን ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀም ማድረግ ነው።
ይህ እስካሁን ድረስ እንዳልተደረገ እሙን ነው። በመንግሥትነት የተስየመው አካል ይህን ኃላፊነቱን ሳይወጣና እስካሁን ድረስ ስናየው የከረምነውን አንድ አይነት ጥፋት ሳያርም ለውትድርና ያልሰለጠነን ሕዝብ [በባዶ እጁና በቁመህ ጠብቀኝ] ግንባር ላይ እንገናኝ የሚል ሌላ ዙር ክተት ስላወጀ ብቻ በኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት የሰለጠነውና በዲሽቃ፣ በስናይፐር፣ በብሬንና መሰል ከባድ የቡድንና የግል መሣሪያዎች እያጠቃ ያለውን የፋሽስት ወያኔ ወራሪ አንበጣ ሠራዊት በቀላሉ ድል አደርጋለሁ ብሎ ካሰበ ከኮረም እስከ ሸዋሮቢት ድረስ ከተፈጸሙት አሳፋሪ ጥፋቶች አለመማሩን ብቻ ነው የሚያሳየው።
ለፋኖ መሳሪያ ነፍጎ ጥይት ከልክሎ “ግምባር እንገናኝ” ታላቅ ፌዝ ነው!
እኒህ አርበኛ አባት እስካሁን ድረስ የተደረጉት ብአዴን የመራቸው ዘመቻዎች ለምን ውጤታማ እንዳልሆኑና ብአዴን የሚባለው ዘግናኝ ፍጥረት ዘመቻው ውጤታማ እንዳይሆን ያደረገውን በሙሉ በግልጽ አስቀምጠውታል። ዝመቱ ብሎ ያዘመታቸው ገበረዎች ስለ ዘመቻው እንዲህ አይነት አቤቱታ ሲያሰሙ ብአዴን የሚባለው ዘግናኝ ፍጡር ኃላፊነት ተሰምቶት እመራዋለሁ ለሚለው ሕዝብ የሚሰጠው ማብራሪያና መልስ ይኖረው ይሆን?