>

ለኢትዮጵያ የምንሰጣት እንጂ የምንሸጥባት ደም የለንም፤ አይኖርምም!!! (እንዳለጌታ ከበደ)

ኢትዮጵያ የምንሰጣት እንጂ የምንሸጥባት ደም የለንም፤ አይኖርምም!!!
(እንዳለጌታ ከበደ)

በዚህ ዘመን፣ እኛ ኢትዮጵያውያን፣ ለኢትዮጵያ ነጻነትና ክብር ብለን፣ የምንከሰክስላት አጥንት፣ የምንናፈርስላት አካል እና የምናፈስላት ደም እንጂ፣ ለጉዳት የሚያጋልጣት እና ለከንቱ ፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ የሚሆን፣ የምንሸጥባትም ሆነ የምንሸጠው ደም የለንም፡፡ ሊኖረንም አይገባም፡፡
ኢትዮጵያችን እንደዘበት ሲበርደን የምንደርባት፣ ሲሞቀን የምናወልቃት የክትም ሆነ የአዘቦት ልብስ አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያችን ‹ጊዜ አጋደለባት፤ ጨለማው ጋረዳት› ብለን የምንሸሻት፣ ‹ቀኑ ተቃናላት፤ ጸሃይ ወጣላት› ብለን የምንቀርባት አይደለችም፡፡ በመከራ ጊዜ ማቃሰቷ ያመናል፤ መረበሽዋ ይረብሸናል፤ በደስታ ጊዜ ደግሞ እልልታዋ ያተጋናል፤ ንቃቷ ያነቃናል፡፡ እናም እንላለን፡- ኢትዮጵያ ማለት፣ ‹ኢትዮጵያዊ ነኝ!› ብለን ለምናምን የተሰጠች በረከት ናት፤ ምስጢር ናት፤ ምትሃት ናት፤  ‹ፈረሰች ተፈረከሰች› ስትባል እምትቆም የጽናት ተምሳሌት ናት!
እኛ እኛን የሆንነው በእሷ ነው፡፡ እኛ አለ እሷ  ምንድነን? እሷው ናት ሕመማችን፤ እሷው ናት ቅመማችን!
በዚህ ዘመን፣ በየትኛውም መንገድ ይሁን – አንድ ኢትዮጵያዊ በሙያው፣ በዕወቀቱ፣ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ ዋጋ መክፈል ያለበት – ነገ ከነገ ወዲያ ‹እኔስ ምን አደረግሁ?› በሚል ጥያቄ ኅሊናው እንዳይወቅሰው ብቻ አይደለም፤ የማይሞት ታሪክ እንዲኖረውና ቀጣዩ ትውልድ ሐውልት እንዲያቆምለት ብቻም አይደለም፤ የእሳት ልጅ አመድ ተብሎ እንዳይዘበትበትም አይደለም – ለነጻነቱ የሚሰጠውን፣ የሚከፍለውን ዋጋ ለራሱ ለማሳየትም ጭምር እንጂ፡፡ ዋናው ነጻነት ነው፡፡ ከባርነት፣ ከሚገፉንና ከሚተፉን፣ ከሚከፍሉንና ከሚከፋፍሉን፣ ከሚግጡንና ከሚያጋግጡን  ‹ነጻነትን ከማያውቁ ነጻ አውጪዎች› ለመላቀቅ በምናደርገው መከላከልና ማጥቃት ማንነታችን ይመዘናል፡፡ ነጻነት ነው ትልቁ ነገር፡፡ (መናቅን ‹በቃኝ!›፣ ባርነትን ‹በቃኝ!›፣ ዘረኝነትን ‹በቃኝ!› ማለትን የሚያውቁ እነርሱ ብጹዓን ናቸው – ለነጻነታቸው የሚሰጡን ዋጋ ተገንዝበዋልና!)
ነጻነት ነፍሳችን የምትመገበው፣ የምትለብሰው፣ የምታጌጥባት ልብሷ ነው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ጥንትም ቢሆን የሚያጸናንም የሚያጽናንም ነጻነታችን ነው፤ አልበገር፣ አላጎበድድ ባይነታችን ነው፡፡ መቼም፣ የትም ከልብ ‹ኢትዮጵያዊ ነን!› ብለን ለምናምን፣ የነፍሳችንን ልብስ ገፍፈው እርቃኗን ሊያስኬዷት ከሚፈልጉት ጋር ኅብረት የለንም፡፡ ይህም ዘመን የፈተነው ሀቅ ነው!
ነጻነቱን አሳልፎ ለመስጠት ከጠላቱ ጋር በየወንዙ የተማማለ እና በገዛ እጁ ለአደጋ በሚያጋልጥ ቦታ የተገኘ ባንዳ ባህርያቸው አንድ ነው፤ ለራሳቸው ክብር አይሰጡም፤ የሚያደርጉትን አያውቁም፤ ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅ ያለ ነው፤ ለራሱ ዝቅ ያለ ግምት ያለው ሰው ደግሞ አደገኛ ነው፤ እንዲህ ያለ ሰው ሰው ማደርያውና መተዳደርያው ሀገርን ከሚሸቅጡና ደሟን ከሚሸጡ  ጋር ነው፡፡ ጠባችንም ከእነዚህ ጋር ነው፡፡ ሀገር አትሸቀጥም፤ ሀገር አትለወጥም፤ ሀገር ለሚዘባበቱባት ተላልፋ የምትሰጥ እጅ መንሻ አይደለችም፡፡
እናም እኔም፣ ቤቴም፣ ወገኔም እንዲህ እንላለን፡- ‹‹ለኢትዮጵያ የምንሰጣት እንጂ የምንሸጥባት አንዳችም ደም የለንም፤ አይኖረንምም!!!!!!!››
Filed in: Amharic