>

ይድረስ ለህወሓት መሪዎች! ኤርሚያስ አማረ

ይድረስ ለህወሓት መሪዎች!

ኤርሚያስ አማረ

ህዝባዊነት፤ ፍትሃዊነት፤ እውነት” ለናንተ ምንድን ናቸው?
በትግራይ ጉዳይ እስከ አሁን ያለኝን አቋም በገደምዳሜ ነበር የምፅፈው:: አሁን ግን መነገር ያለባቸው ነገሮች በግልጽ መነገር እንዳለባቸው ውስብስብ የሆኑ ክስተቶች አድገው አሳሳቢ እየሆኑ ስለመጡ፤ እንደዜጋ ግዴታየን ለመወጣት ይህች አጭር ደብዳቤ ለመፃፍ ግድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ውድ የህወሓት መሪዎች ሆይ
የትግራይ ህዝብ በእናንተ በመሪዎቹ የተሳሳተ ስሌት (Miscalculation) ፈቅዶ ባልገባበት ጦርነት ለደረሰበት በደል ራሱን የመከላከል ተፈጥሯዊ፣ ህጋዊና ምክንያታዊ መብቱ የተጠበቀ እንደሆነ ብዙ ሰው ይስማማል። ለዚህም ትግሉን ህዝባዊ ያደርገዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ልሂቁ፣ ሚዲያው፣ ምሁራኑ ፣ ማህበራቱ፣ ሲቪክ ማህበሩ የትግራይ ህዝብ ካለመሪ እንዳይቀር ብሎ ህዝቡን ከእናንተ ጎን እንዲሰለፍ መወትወቱ የሚታወቅ ነው።
እናንተ ግን ያንን በጎ ድጋፍ ከድክመት ቆጥራችሁ በትንሹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባልጠበቁት ሁኔታ ብቸኛ ወኪል ሆናችሁ በአዲስ ስልት ተመልሳችሁ ወደ ስልጣን ለመምጣት እየወሰዳችሁት ያለው “ጦርነቱን በስፋት የማስቀጠሉ እርምጃ” ፍትሃዊ (just war) ሊያደርገው አይችልም።
በዚህ ሂደት የሰላም/ድርድር አማራጭን ዘግታችሁ የፕሮግራም ለውጥ ሳታካሂዱ በፀሃይ ፍጥነት ወደ መሃል አገር ለመድረስ እያደረጋችሁት ያለው ፈጣን ግስጋሴ ዓላማችሁ በውል ምን እንደሆነ ባይታወቅም ለታዛቢው ግን ካለፈው ታሪካችሁ በመነሳት ግስጋሴው ምናልባትም የእናንተን ያልተገደበ የስልጣን ጥም (Insatiable power desire) ፍላጎት ለማርካት ነው ብሎ ቢጠረጥር ኣይፈረድበትም። ስለዚህ ትግላችሁ ከሃሳብ ርቆ “ጉልበት ላይ” ብቻ በማተኮሩ እልህና ቁጭት የተቀላቀለ ስሜት በአገሪቱ እንዲያንዣብብ መንገድ ከፍቷል። በዚህ ምክንያት ህዝቡ “የአገሩን አንድነት በሚያስፈራ ሁኔታ የመፍረስ አደጋ” ስለተሰማው በሌላው ጎራ ያለው ወገንም እንዲሁ “የህልውና ትግል” ሆኖ ስላገኘው ጦርነቱ “ህዝባዊ” ለማድረግ የተገደደ ይመስላል። ሰሞኑን ያየነውም ሰልፍ የዚሁ ስጋት ውጤት ሊሆን ይችላል::
እንደ አውራ ብሄራዊ ድርጅት በቀውሱ ምክንያት የትግራይ ተወላጆች የሞቀው ትዳራቸውና ልጆቻቸውን ትተው ከአገር ተሰደው፣ እንደ ህብረተሰብ ለችግር መዳረጋቸው እናንተ ሃላፊነት ትወስዳላችሁ? የትግራይ ህፃናትና ወጣቶች ለአንድ ዓመት ከትምህርት ርቀው የእናንተን ዓላማ ለማስፈፀም በረሃ ለበረሃ ሲንከራተቱ ሞተው የተረፉትም እንደ ማንኛውም በዓለም ውስጥ የተደረጉ ጦርነቶች ላይ ተካፍለው በህይወት የተረፉ ተዋጊዎች ላይ “በጦርነቱ ምክንያት ትራመታይዝ”  ሆነው “Post Traumatic Stress Disorder” (PTSD) የሚባል በጦርነቱ ሰበብ በኋላ የሚከሰት “የኣእምሮ መቃወስ” ስለሚገጥማቸው ኣይምሮሯቸው ላይ ጫና ስለሚያስከትልባቸው የደከመ ህብረተሰብ እንደሚፈጠርስ አስባችሁት ታውቃላችሁ?
ህብረተሰቡ ከጦርነትና እልቂት መፍትሄ ሊያፈልቁ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ምሁራኖቻችን ስንመለከት ጦርነትን የመጎሰም ፍላጎታቸው እጅግ የላቀ ሆኖ ሳየው ምሁራኑ ከሚያሳዩት ከመጠን በላይ “የጦረኛነት ጥማት” ስመለክት የሚገርም ነው። በቅርቡ የታዘብኩት አንድ የታወቀ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ (ፓለቲከኛ) መምህሩ ካለው የትምህርት ደረጃ አኳያ ሲታይ ከደረጃው ያነሱ “የድጅታል ካድሬዎቸን” ስሜት ለመጠበቅ ሲል “ኣይሰምዕን እየ”  (“ገና ወደ ኤርትራ እዘምታለሁ! እምብየው አልሰማም!”) ” የሚለውን ዘፈን ሲጋብዝ የትግራይ ህዝብ መጻኢው ጊዜም “ዕጣ ፈንታው”  መላው ህይወቱ ከጦርነት ጋር እንዲያያዝ የሚገፋፋ ማቆሚያ የሌለው የጦርነት ጥሪ ሲደረግ አያሳስባችሁም?
ሌላው የሚገርመኝ “እውነት” ከኛ ጋር ነች ስትሉ ብዙ ጊዜ ትደመጣላችሁእን።  “እውነት ከኛ ጋር ነች” ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው? የቱና ምኑን ነው እውነት? ህዝቡ ከላይ በጠቀስኩት ምክንያት የእናንተን “ጥፋት” ወደ “ጎን ትቶ”  የዚህ ቀውሱ ብቸኛ ተጠያቂ “ኢትዮጵያ” ለማድረግ ስለሞከረ “እውነት” ከእናንተ ጋር የሆነች መሰላችሁ?
ሲ ኤን ኤንና ኒው ዮርክ ታይምስ የመሳሰሉ ሚዲያዎች የአሜሪካን ጥቅም ለማስጠበቅና በተለይ ደግሞ የባይደን (ዲሞክራቲክ ፓርቲ) አስተዳደር ፓሊሲ ለመከላከል ሲባል እውነትን ቢደፈጥጡ (suppressing facts) የእናንተን ልክነት ያረጋገጠ መስሏችሁ ከሆነ ተስስታቹሃል::
እስኪ ትንሽ ወደ ወደ ኋላ ወስጄ የነዚህ ሚድያዎች ታሪካዊ ቅጥፈት ላሳያችሁ። ዋልተር ዱራንቲ (Walter Duranty) የተባለ የኒው ዮርክ ታይምስ ሞስኮ ዘጋቢ በ1930 የሶቭየት ህብረት መንግስት ገመና ለመሸሸግ ሲል  በወቅቱ በዩክሬንና ሰሜን ካውካሰስ የተከሰተው ድርቅ ሲዘግብ ‘የመገንጠል ጥያቄ ላለማስተናገድ’ በውሸት “ምንም ድርቅ ወይንም ረሃብ የሚባል የለም ፤ የመከሰት ዕድልም የለም” ብሎ ዘግቧል። ለዚህ ዘገባውም በአሜሪካ የሚገኘው ፑልቲዘር ሽልማት (Pulitzer Prize) ተችሮታል:: የሸለሙበትም ምክንያት ለልህቀቱ ፣ ጥልቅ ዕውቀቱ ፣ ሚዛናዊነቱ ፣ ፍትሃዊ እይታው እና ግልፅነቱ በሚል ነበር (scholarship, profundity, impartiality, sound judgment and exceptional clarity):: ብዙም ሳይቆይ ግን ማልኮም ማገሪጅ (Malcolm Muggeridge) የተባለ እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ ሲዘግብ “የዩክረይን ሰው ሰራሽ ረሃቡ በታሪክ ትልቁ ሃጥያት” ሲል ገልፆታል:: ከአስርት ዓመታት በሃላ በወጣው ጥናታዊ ፅሁፍ ወደ 6 ሚልዮን ሰው እንደሞተ ይነገራል::
ስለእውነት እንነጋገር ከተባለ ላለፈው ጊዜ ለፈፀማችሁት ጥፋት ዕዳውን መቸ ከፈላችሁት? የትግራይ ህዝብ የእኩይ አስተሳሰብ መጣያ ወይም ማጠራቀሚያ የማድረጉ ተከታታይ ክስተት ያለ ምንም ጊዜ መውሰድ አስቸኳይ እርማት ተደርጎ በጊዜ መቀጨት ይኖርበታል::
ብዙ ሰው ላያስታውሰው ይችል እንደሆነ እንጂ “እውነትን” ተቆጣጥሮ/አፍኖ/አዛብቶ ስልጣን ላይ መቆየት በእናንተ አልተጀመረም:: በ1922 ሌኒንን ተክቶ ሩስያን ለ32 ኣመት የመራት (ያደቀቃት) ጆሴፍ ስታሊን “Control the truth” (እውነቱን ተቆጣጠር) በሚል ፈሊጥ ነበር። ከስንት ግዜ በሃላ የወጣው አወዛጋቢው የሰብኣዊ መብት ጥሰት ጣምራ ምርመራ ሪፓርት ስንመለከተው ምናልባትም የስታሊን ጥበብ ተጠቅማቹሃል ብሎ ለሚጠረጥር መፍረድ ይከብዳል። ለነገሩ እንጂ ርዕየተ አለማዊ ፍልስፍና መመሪያችሁ (ዲሞክራቲክ ሴንትራሊዝም እና አብዮታዊዴሞክራሲ) ከዚያው ዓለም የተቀዳ አይደል?
ደጋግማችሁ የምትናገሩት ሂሳብ የማወራረድ ጉዳይ አለ። እርግጥ ነው እናንተ ከአማራ ልሂቃንና ከብልጽግና አመራሮች የምታወራርዱት ሂሳብ ይኖራችሁ ይሆናል። የኢትዮጵያ ህዝብ (የትግራይ ህዝብን ጨምሮ) ደግሞ ከናንተ ጋር ያላወራረደው ሂሳብ አለው። ይህ እውነታ ሲነሳ “እውነት” ከናንተ ጋር እንደሆነች በምን መለኪያ ልታካክሱት ትችላላችሁ?
ገና አስተዳደሩ ሳይጀምር “ፋሽስት አብይ” እያላችሁ ህዝቡን ስታደነቁሩት ነበር፡: ህዝቡ “ሰውየው እናንተ በቀደዳችሁለት ቦይ ተጓዘ እንጂ ምን የተለየ ነገር አደረገ?”ብሎ ቢጠይቃችሁ መልሳችሁ ምንድነው?
እኔ እንደምረዳው የኢትዮጵያ ህዝብ የአብይን ስልጣን ማስቀጠል ጉዳዩ አይመስለኝም። ሰዓቱ ሲደርስ ያሽቀነጥረዋል። እውነታው ግን ህዝቡ በእናንተ የበላይነት የሚመራው የኢህአዴግ አስተዳደር (Dynasty) “አንገሽግሾት” እንደገፋችሁ ከአንደበታችሁ ሰምተናል። የአገሬው ሰው የምሬት ድምጽ ከረሳችሁት ደግሞ ‘ፈረንጁ ጀፍሪ ፊልትማን (Jeffery Filtman)’ በቅርብ ሊያስታውሳችሁ ህዝቡ “Meles Style Rule” ኣይፈልግም ያለውን ታስታውሳላችሁ። አሌክስ ድወል (Alex De Waal) ደግሞ ህዝቡ እናንተ ላይ እምነት የለውም ሲል ፅፏል:: ስለዚህ አገሪቱም እናንተም በሥርዓት የምትዳኙበትና ፍትህ የሚሰፍንበት ረጋ ያለ ሕሊና መፈተሽ ለናንተም ለህዝቡም ባጠቃላይ ዘላቂ መፍትሄ ማፈላለጉ ብታተኩሩ እንጂ አስተዳዳራችሁ ለ27 አመት አይቶት በቃችሁ ያላችሁን ህዝብ ወደ ጦርነት መማገድ ለሁሉም ወገን ጤና አይሰጥም።
በዚህ ልደምድም። ስለ ውግያው ጉዳይ እንድታውቁት የሚገባው ነገር እየተዋጋችሁ ያለው በዋናነት ከመከላከያ ጋር እንዳልሆነ ልባችሁ ያውቀዋል።  ከመንግስት ሀይል ጋር ውግያ ቢሆን ኑሮ ድሮ አዲስ አበባ ገብታችሁ ነበር። ግን ያለምንም ቅድመ ዝግጅት የእናንተን ወደ አዲስ አበባ መመለስ ምን ሊያመጣ እንደሚችል ስላወቃችሁ ሌሎች ካርዶች  ለመጫወት እየጣራችሁ ነው:: እሱ ለማንም ኣይጠቅምም:: አካሄዳችሁን ኣስተካክሉ::
አሁንም ከልብ ሰላም ለማስፈን ፍላጎት ካላችሁ አልረፈደምና ሃላፊነት የተሞላውን ስራ ለመስራት ፍላጎት ካሳያችሁ የህዝብ ልብ ማረጋጋት ይቻላል። ሞክሩ:: አዎንታዊ የሆነ ህዝባዊ ግንኙነት የተሞላበት ጥበብ ሳታክሉበት “ጉልበት” በደረቁ ዘላቂነት የለውም የትም አያደርስም። ኢትዮዽያ ከመሪዎቿ በላይ ነች:: የህዝቡን የቆየ የመጋመድና አብሮ የመኖር ፤ በሉኣላዊነቱ የማይደራደር እሴቱን ከግምት ውስጥ አስገብታችሁ ተንቀሳቀሱ:: በድፍረት የኢትዮዽያን ህዝብ ወክየ መናገር የምችለው ነገር ቢኖር ውግያ በቅቶታል::
በዚሁ ኣጋጣሚ የኢትዮዽያ መንግስትም ለትግራይ ህዝብን አስቦ የአገር መሪነቱን ሃላፊነት እንዲወጣ ማስታወስ እወዳለሁ::
ሰላም ለኢትዮዽያ!!
ኤርሚያስ ኣማረ
Filed in: Amharic