>
5:30 pm - Thursday November 2, 2344

ጊዜው ደርሶ እስክንነቃ ድረስ ዘመኑን ሁሉ ሞተን ኖረናል!  (መላኩ ብርሀኑ)

ጊዜው ደርሶ እስክንነቃ ድረስ ዘመኑን ሁሉ ሞተን ኖረናል! 
መላኩ ብርሀኑ

አሜሪካ “የበረሃው ማዕበል” በሚል ስያሜ የጠራችውን ወታደራዊ ዘመቻ (ወረራ ትክክልኛ ቃሉ ነው) በኢራቅ ላይ ከማድረጓ በፊት እሰጥ አገባ ላይ ሳለችም ሆነ ወረራውን ስታደርግ የዓለም ሚዲያዎች ሁሉ አይንና ጆሯቸውን ሳይከድኑ ከጠዋት እስከማታ ኢራቅ እና ሳዳም ሁሴን ላይ ተጣብቀው ከሚበቃን በላይ መረጃ ሲግቱን ከርመዋል። የተጠና ውጤቱ የተሰላ እና በውጤቱ የሚገኘው ጥቅም የተረጋገጠ መረጃ።
በዘመኑ የሆሊውድ ፊልሞች የደነዘዝን እኛ ደግሞ እንዲህ ማህበራዊ ሚዲያ ሳይኖር በፊት የኢትዮጵያ ራዲዮ ጌጣችን፣ የአለምነህ ዋሴ ዘገባ ዋና ምንጫችን ነበር።ሰዓት እላፊ እንደታወጀበት ህዝብ ሁሉም በየቤቱ ከትቶ የበረሃውን ማዕበል ትዕይንት ከአለምነህ ዋሴ አስገምጋሚ ጉሮሮ ስር ይጠባ ነበር።
ማታ ዜና ሲጀምር ከየትኛውም የሃገር ውስጥ ጉዳዮቻችን ቀድሞ የዘገባ እድል የሚያገኘው የበረሃው ማዕበል ዘመቻ ነበር።(ዛሬ ድረስ ይገርመኛል የዓለም ፖለቲካ ተጽዕኖ መጠን)
አለምነህ ዋሴ “…እነሆ ኢራቅ ወደዶግ አመድ ልትቀየር ቀኗን መጠባበቅ ይዛለች…የአሜሪካ ፈርጣማ ክንድ ሊደቁሷት ቀርቧል…ሳዳም ሁሴን ሊያበቃላቸው ቀናቸው እየተቆረጠ ነው…የበረሃው ማዕበል ተጀመረ!! ” ምናምን ብሎ ሲጀምር በጉጉት እንቁነጠነጣለን…በአየር በባህር በምድር የሚምዘገዘጉ ሚሳኢሎች ኢራቅን ሲቀጠቅጡ አንጀታችን ቅቤ ይጠጣል…ደንዝዘን ነበር። ሞተን ነበር።
አለምነህ ሲተርክ ከዘመኑ ፊልሞች ሁሉ እጅግ አጓጊ የሆነ ፊልም እንደሚተረክለት ሰው ጆሯችንን ቀስረን ትረካውን እናዳምጣለን። አለምነህ በምዕራባውያን ሚዲያ የተሳለለትን የሳዳም ጭራቅነትና የዓለም ሰላም ጠላትነት አምኖና እንደወረደ ተቀብሎ ፣ በርሱም ተጠምቆ ለእኛም ከሲኤንኤን በላይ ያንን ምስል ግቶናል። አልፈርድበትም…ያነበበውን ነው የተረጎመነው…ምንጩን ነው ያሰፋው…ዘመኑ ነው የሸወደው።
በዘመኑ አለምነህ ስምና ዝና ያገኘበት ይኼው ዘገባ ሳዳምን አንተ ብሎ እስከመጥራት እና አሜሪካኖቹን የሰላም ጠበቃ አድርጎ እስከመሳል፣ በሳዳም እስከመሳለቅ ሲያደርሰው እኛንም እሱንም በአሜሪካ ሃያልነት እስከመደነቅ አብቅቶናል።
አሜሪካ በሰላም ሃገር ኢራቅን እንደዚያ ዶግአመድ አድርጋ፣ ሳዳምን አዋርዳና ሰቅላ እስትገድል ድረስ ማንአለብኝ ባይ ነበረች (አሁንም ነች)  ።መላውን አለም በሃሰት መረጃ አታልላና የአለም ፖሊስነቷን እንዲያወድሰው አድርጋ ለዚህ ዘመቻ ያመቻቸችው በሚዲያዎቿ ነበር። እንደእኛ ያሉ ጥቃቅን ሃገራት ሳይቀሩ ጋዜጠኞቻቸውና ሚዲያዎቻቸው በዚህ አስማት ፈዝዘው “ቪቫ አሜሪካ” በማለት ጦርነቱን ደግፈዋል። ያ ጦርነት ግን ምንም የማያውቀውን የኢራቅ ህዝብ ከፍ ያለ ስቃይና መከራ አልብሶታል። የገዛ ሃገራቸውን በሚገባቸው መንገድ እየመሩ የነበሩትን ሳዳም ሁሴንም ከአለም አደባባይ በውርደት እና በስቃይ አጥፍቷቸዋል።
ያኔ ዓለም ተኝቶ ነበር፣ አፍሪካ ተኝታ ነበር፣ ሁላችንም ተኝተን ነበር…ነግ በኔ አላልንም።
እነሆ እንደገና ፓንአፍርካኒስቱ ኮሎኔል መሃመድ ጋዳፊ አልመች ያሏት አሜሪካ ሰበብ ፈልጋ ያቺን ምርጥና የዜጎቿ ገነት የሆነች ሃገር ድምጥማጧን ስታጠፋትም አልነቃንም። ጋዳፊን አዋርደውና አሰቃይተው ፣ አስጎትተውና አሳቅቀው ሲገድሏቸውም በሳዳም እንዳደረግነው በርሳቸውም አላግጠናል። ስቀናል። ይህቺ ተንኮለኛ  ሃገር በሚዲያዎቿ ዓለምን በአብዛኛው ከጎኗ አድርጋ ሊቢያን ላትነሳ አፈራርሳት ሄዳለች።
እነሆ ያቺ የበረሃ ገነት ፣ ሊቢያ አረብ ጀማሃሪያ ዛሬ የት ናት? ሳዳም ለአሜሪካኖች አልገዛ ቢሉ ተገደሉ፣ ጋዳፊ ለአሜሪካኖች አልገዛ ቢሉ ተገደሉ። ሃገሮቹ ፈራርሰው ህዝቦቹ የመከራ ቋጥኝ ገፊ ሆኑ። ያኔ አልነቃንም…የኒዮሊበራል ፖለቲካ አልገባንም…አሜሪካን ደግፈን በርቺ ብለናል…ነግ በኔ አላልንም። አፍሪካንና የአፍሪካ ህብረትን በጽኑ ድጋፋቸው ያቆሙ ጋዳፊ ሲወድቁ (ከነችግራቸውም ቢሆን) አፍሪካ ህብረት እንኳ ድምጽ አላወጣም። ሳዳም ሲሳደዱ የአረብ ሃገራት ዝም አሉ። አሜሪካ የዓለም ፖሊስነቷን አሳየች!! ተኝተን ሳይሆን ሞተን ነበር።
የመን ፣ ሊቢያ፣ የላቲን አሜሪካ ሃገራት ወዘተ የዚህ ሰለባ ነበሩ…አደንዛዦቹ ደግሞ ሚዲያዎቻቸው።
ይኸው እንግዲህ….ተስቦ ተስቦ ነገሩ እኛ ጋ ደረሰ። ኢትዮጵያውያን ዳግም ኢራቅ ፣ዳግም ሊቢያ ፣ዳግም የመን ፣ ዳግም….እንሆናለን ወይ ነው ጥያቄው።
አይመስለኝም። ከተኛንበት ነቅተናል። አፍሪካ ነቅታለች። አንድ ጸሃፊ በትዊተር ፖስቱ ላይ ለአሜሪካ እንዳለው
“ኢትዮጵያውያን እያዩዋችሁ ነው፣ አፍሪካውያን እያዩዋችሁ ነው፣ ዓለም ሁሉ እያያችሁ ነው”
ዛሬ እስክንንቃ ድረስ ለዘመናት ሞተን ነበር።የሚዲያ ዘመቻን ተከትሎ የሚደረግ ወታደራዊ ዘመቻ ተነቅቶበታል ወይም ጊዜ አልፎበታል። አሁን አለም ሌላ ምንጮችም ሌላ አንደበቶችም አሉት። አሜሪካ ሁልጊዜ ልክ የሆነችበት ዘመን እያከተመ ነው። ለዚህ ተቃውሟችን ዛሬ ዋጋ ብንከፍልም ነገ ሉዓላዊነታችን ራሱ ይክሰናል። አሜሪካውያኑ ራሳቸው መልሰው ይመጣሉ። ምክንያቱም አለም ሁልጊዜም ከአሸናፊዎች ጋር ትወግናለችና። ተሸናፊዎች ከራሳቸው በቀር ማን መሆናቸውን  የሚያስታውስላቸው ማንም የላቸውም!!
Filed in: Amharic