>

ኦህዴድን ማገዝ እና ማጀገን ከኦህዴድ አጋሮች የሚጠበቅ የቤት ስራ...!!! ( ሸንቁጥ አየለ )

ኦህዴድን ማገዝ እና ማጀገን ከኦህዴድ አጋሮች የሚጠበቅ የቤት ስራ…!!!
ሸንቁጥ አየለ

በ1984/5/6 ዓም የወልቃይት እና ራያ አማራዎች እጅግ አሰቃቂ የማፈናቀል የጭፍጨፋ እና የዘር ማጥፋት በደል በወያኔዎች  ይፈጸምባቸዉ ነበር።በወቅቱ ይሄን የተመለከቱት የመአህድ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አስራት ለትግራይ ህዝብ፡ ለመላዉ የአማራ ህዝብ፡ ለመላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ እና ለመላዉ የአለማቀፍ ማህበረሰብ ይሄ ወንጀል እንዲቆም ጥሪ አቅርበዉ ነበር።
በጣም እስካሁን የሚገርመኝ ነገር ታዲያ የፕሮፌሰር አስራትን ጥሪ በትምክህተኝነት፡ በዘረኝነት ፡ ወቅቱን ያልጠበቀ ጥሪ ነዉ ፡ በትግራይ ህዝብና በአማራ ህዝብ መሃከል ቅራኔ የሚፈጥር ሃሳብ ነዉ እያሉ ያጣጣሉት በወቅቱ የአማራ ብሄረተኝነት ይለምልም ይሉ የነበሩት በኣዴኖች ነበሩ። በአዴኖች በጣም ፈሪ ስለሆኑ ለራሳቸዉም ህዝብ ሆነ ለራሳቸዉ ግለ ሰብዕና የሚገባዉን ዋጋ ስለማይሰጡ አፋቸዉን በመለጎም ሁሉንም ነገር ለማሳለፍ ይሞክራሉ። ልክ ጅቡ የኔን እግር እየበላዉ ነዉና ሌሎቻችሁ ዝም በሉ እንዳለችዉ ሴት። እናም ያኔ ዝም በሉ ባዮች፡ ዝም አሳባዮች እና ስለ ህዝባቸዉ የሚጮሁትን አድነዉ ገዳይ አስገዳዮች ነበሩ። መርሃቸዉ በአማራ ፍጅት ላይ የአማራ ብሄረተኝነት ይለምልም የሚል መፈክር ከመጻፍ አይዘልም ነበር።
አስገራሚዉ ነገር ታሪክ እራሱን ገልብጦ ደገመ።ዛሬ ብአዴኖች ከኦህደእድ ጋር ግንባር ፈጥረዋል። ግን በወለጋ በምዕራብ ሸዋ በመተከል የአማራ ህዝብ በኦነግ ሸኔ ሲጨፈጨፍ የነሱ የትግል አጋር ኦህዴድ ቆሞ ሲያስተዉል ኦህዴድን ዞር ብለዉ አይቆጡትም። የአማራን ፍጅት ኦህዴድ በሚያስተዳድርበት ቦታ እንዲያስቆም አይከራከሩትም።ኦህደእድ አቅም ካጣህ እኛ እናግዝህ አይሉትም።ኦህዴድም ለራሳቸዉም ለመጡበት ነገድም ክብረ ቢስ እንደሆኑ ስለሚያዉቅ አማሮች ሲፈጁ ቆሞ ይመለከታል።
 ኦህዴዶችን በእኩያ መንፈስ ከማስተማር ከመከራከር እና ትክክለኛ የፍትህ ስራ እንዲሰሩ ከማድረግ ይልቅ የእነ ሽመልስ አብዲሳን “ነፍጠኛን ሰበርነዉ” ንግግር የዛሬዎቹ ከአማራ ብሄረተኛ ነኝ ባይ ተቃዋሚ እስከ ግለሰብ ተወዳዳሪ ነኝ ባይ  ዳንኤል ክብረት ብሎም እስከ ዋናዉ ብአዴን ” የአፍ ወለምታ ነዉ” ብለዉ በአደባባይ ስለ ኦህዴድ መሪዎች ተወክለዉ ይከራከራሉ። ስለሚያልቀዉ አማራም ባላዬንም ከማለፍም በላይ ሌሎች እንዳይናገሩ ይሳደባሉ ያስፈራራሉ ይፈርጃሉ።
 ብአዴንነና ቀሪዉ የአማራ ብሄረተኛ ነኝ ባይ እንዲሁም እንደ ኢዜማ አይነቱ አጭበርባሪ የአንድነት ሀይል ነኝ ባይ ሀይል እዉነት ስለፍትህ ፡ ስለዜጎች ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ቢገዳቸዉ ኖሮ ተጋግዘዉ እና ተባብረዉ አጋራቸዉ ኦህዴድ የአማሮችን እልቂት እሱ በሚያስተዳድርበት ቦታ ሁሉ እንዲያስቆም ጫና ያደርጉበት ነበር።
ኦህዴድም ካልቻለ “በኦነግ ሸኔ የሚጨፈጨፈዉን ያልታጠቀ  አማራ በማስታጠቅ ኦነግ ሸኔን የመዋጋት ሂደቱን ዉጤታማ ያደርገዋል::ኢትዮጵያንም አሸናፊ ያደርጋታል!” የሚል ምክረ ሀሳብ በማቅረብ ኢትዮጵያን የማዳን ሂደቱን ያፋጥኑት ነበር። ግን ይሄ ሁሉ አስመሳይ እና ፈሪ ስለሆነ ኦህዴድን ማገዝ እና ማጀገን ብሎም ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ማምጣት አልቻሉም።ኦህዴድ ቆምጨጭ ያለ ወዳጅነት እንዲሁም ትክክለኛ የወዳጅ ምክረ ሀሳብ ቢቀርብለት ተግባራዊ ያደርገዋል። ስለሆነም አሁን ሳይታጠቅ እየተጨፈጨፈ በነገዱ ብቻ ለሚያልቀዉ ህዝብ ተጠያቂዉ ኦህዴድ ብቻ አይደለም።
አሁንም ኦህዴድን በማገዝ እና በማጀገን ትክክለኛ ዉሳኔን ማሳለፍ ብቻ የኢትዮጵያን ድህነት ያፋጥነዋል።ይህዉም በኦነግ ሸኔ የሚጨፈጨፈዉን ያልታጠቀ  አማራ ማስታጠቅ ኦነግ ሸኔን የመዋጋት ሂደቱን ዉጤታማ ያደርገዋል::ኢትዮጵያንም አሸናፊ ያደርጋታል::
መደምደሚያ:-
—-‐—-
በኦነግ ሸኔ የሚጨፈጨፈዉን ያልታጠቀ  አማራ ማስታጠቅ ኦነግ ሸኔን የመዋጋት ሂደቱን ዉጤታማ ያደርገዋል::ኢትዮጵያንም አሸናፊ ያደርጋታል::
Filed in: Amharic