ሶማሌ እና ሶማሊያ ….!!!
አቻምየለህ ታምሩ
*…. ያገራችን ሶማሌ ሶማሊያ እንደ አገር ሳይፈጠር ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ አካል የነበረ አንዱ ኅብረ ቀለማችን ነው። ሶማሊያ በኛው ልጆች በነጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ተጋድሎ ነጻ አገር ለመሆን የበቃች የኢትዮጵያ ጎረቤት የአገር ስም ነው። ሶማሌ እንደ ነገድ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቱ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያና ሶማሌላንድ ውስጥ ቢኖርም ከሁሉ በፊት ግን ኢትዮጵያዊ ነበር…!
ያገራችን የፖለቲካ ተንታኝ፣ ምሑር፣ አዋቂና ፖለቲከኛ እየተባሉ በየሜዲያው የሚጋበዙ ሰዎች አብዛኛዎቹ ሶማሌንና ሶማሊያን መለየት የማይችሉ ናቸው። ከመሐመድ ዚያድ ባሬ ባሬ ጋር ተሰልፈው ኢትዮጵያን ይወጉ የነበሩት ኦነጋውያን ሁሉ አብረውት ተሰልፈው የነበረው የሶማሊያ አገዛዝ የፈጸመብንን የግፍ ወረራ ለመግለጽ ሶማሌ ኦሮሞያቸውን እንደወረረ አድርገው ያቀርቡታል። ጋዜጠኛ ተብለው የተሰየሙትም ካድሬዎች በመሆናቸው ሲባል የሚሰሙትን ከመድገም ውጭ ተጠያቂዎቹ ንግግራቸውን እንዲያርሙ እድል የሚሰጡ አይደለም።
ሶማሌና ሶማሊያ አንድ አይደሉም። ሶማሌ ልክ እንደ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ወዘተ የአንዱ የኢትዮጵያ ነገድ ስም ነው። ያገራችን ሶማሌ ሶማሊያ እንደ አገር ሳይፈጠር ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ አካል የነበረ አንዱ ኅብረ ቀለማችን ነው። ሶማሊያ በኛው ልጆች በነጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ተጋድሎ ነጻ አገር ለመሆን የበቃች የኢትዮጵያ ጎረቤት የአገር ስም ነው። ሶማሌ እንደ ነገድ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቱ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያና ሶማሌላንድ ውስጥ ቢኖርም ከሁሉ በፊት ግን ኢትዮጵያዊ ነበር።
የሩቁን ዘመን ትተት የቅርቡን ብንወስድ ወልወል ውስጥ የሶማሌ አርብቶ አደሮች ግመሎቻቸውን ውኃ የሚያጠጡባቸው ወደ 350 የሚሆኑ ጉድጓዶችን እናገኛለን። ሶማሌዎች ራሳቸው በትውፊታቸው እንደሚናገሩት እነዚህን የውኃ ጉድጓዶች በኡጋዴን ምድር የሶማሌ ተወላጅ አርብቶ አደር ዜጎቻቸው ግመሎቻቸውን ውኃ ያጠጡ ዘንድ ያስቆፈሩላቸው ኢትዮጵያን ከ1427 ዓ.ም. – 1461 ዓ.ም. ያስተዳደሩት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ናቸው።
ይህ በሶማሌዎቹ በራሳቸው የሚነገረው ትውፍት የሶማሌን ጥንተ ኢትዮጵያዊነት የሚያሳይ ታሪካችን ነው። ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ በኡጋዴን ምድር ስላስቆፈሯቸው 350 የግመል ውኃ ማጠጫ ጉድጓዶች ታሪክ ተጨማሪ ማወቅ የሚሻ ቢኖር የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ሶማሊላንድ ወሰን ለመደንገግ በሁለቱ አገሮች የተቋቋመው ኮሚቴ የኢትዮጵያው ጸሐፊ የነበሩት ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ “የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ሶማሊላንድ የወሰን መካለል ታሪክ” በሚል በ1927 ዓ.ም. ያሰናዱትን ድንቅ የታሪክ ማኅደር ከገጽ 53 ጀምሮ ያንብብ።
ከዚህ ታሪክ በኋላ የተፈጠሩት የጅቡቲ፣ የሶማሊያ፣ የኬንያና የሶማሌ ላንድ ዜግነት ያላቸው ሶማሌኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የኢትዮጵያ ሶማሌዎች ጎረቤቶችና ኢትዮጵያ ከተፈጠረች ሺህ ዓመታት በኋላ ከሀምሳ ዓመታት በፊት የተፈጠሩ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች ዜጎች ናቸው።
መሐመድ ዚያድ ባሬ በ1969 ዓ.ም. ኢትዮጵያን በግፍ በወረረበት ወቅት የወረረን ሶማሊያ እንጂ ሶማሌ አይደለም። ፋሽስት ወያኔ፣ ናዚ ኦነግ፣ የኢትዮጵያ ጠላቶች አገር በቀል ወኪል የሆነው ኢሕአፓ፣ ወዘተረፈ አብረውት ተሰልፈው ኢትዮጵያ የወጋው ሶማሊያ እንጂ ሶማሌ አይደለም። በተቃራኒው ስመጥሩን የሶማሌ ተወላጅ የኢትዮጵያ አርበኛ ደጃዝማች ዑመር ሰመተርን ከደጃዝማች ዑመር ሰመተር በፊትና በኋላ ለናት አገራቸው ኢትዮጵያ የተዋደቁ የሶማሌ አርበኞች ቁጥር እልቆ ቢስ ነው።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖልም ድረስ ቢሆን ለመሄድ የተማማለውን የፋሽስት ወያኔን ወራሪ አንበጣ ሠራዊት ለመደምሰስ ግንባር ከተሰለፉት ኢትዮጵያውያን መካከል የሶማሌ ልጆች ቀዳሚዎቹ ናቸው። እነዚህን የኢትዮጵያ ልጆች ጎረቤትን ከሆነችው የመሐመድ ዚያድ ባሬዋ ሶማሊያ ወራሪ ሠራዊት መለየት ያስፈልጋል።
ባጭሩ ሶማሌና ሶማሊያ አንድ አይደሉም። ያገራችን ሶማሌዎች ሶማሊያ ከመፈጠሯ ከዘመናት በፊት የኢትዮጵያ ልጆች ሆነው የኖሩ የኢትዮጵያ ድንበር ጠባቂዎች ናቸው። በዚህ ወቅትም ወደ ሰሜን ያገራቸው ክፍል ዘምተው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖል ድረስ ለመሄድ ቆርጦ የተነሳውን የፋሽስት ወያኔ ወራሪ አንበጣ ሠራዊት እየተፋለሙ በየአውደ ውጊያው ኢትዮጵያ እየሆኑ ነው። እነዚህን እናት አገራቸውን ኢትዮጵያን ከብተና ለመታደግ የዘመቱ የቁርጥ ቀን ልጆችንና በመስዕዋትነታቸው ኢትዮጵያ እየሆኑ የሚገኙ የኢትዮጵያ ጠባቂዎችን ኢትዮጵያ በግፍ ከወረረው የመሐመድ ዚያድ ባሬ የሶማሊያ ጦርና ጀሌዎቹ መለየት ያስፈልጋል። ስለዚህ ሶማሌንና ሶማሊያን ለዩ። ኢትዮጵያ በ1969 ዓ.ም. በግፍ የተወረረችው በሶማሊያ እንጂ በሶማሌ አይደለም!