«ትህነግ ራያን ሲወር እነ ታማኝ በየነ የት ነበሩ? እነ ነአምን ዘለቀ የት ነበሩ? እነ አንዳርጋቸዉ ጽጌ የት ነበሩ?»
ዶ/ር ደረጀ ከበደ አንተስ የት ነበርክ?
ሃራ አብዲ
አዲሱ ምልምል ተቃዋሚ ደረጀ ከበደ ከሰሞኑ የለቀቀዉን ቪዲዮ ተመልክቼ ተደንቄአለሁ። ተደንቄአለሁ የሚለዉ ባይገልጸዉም ይህን ለማለት ብቅ ብያለሁ። ተናጋሪና ጸሀፊ በበዛበት ዝምታዉ ይበጅ ነበር። ታዲያ ምን ያደርጋል አንዳንዱ ዝም አያሰኝም።
በመጀመሪያ ደረጃ፤ ደረጀ ከበደ ምንም የተናገረዉ አዲስ ነገር የለም። ሌሎች፤ ዘመኑን የማይዋጁና ሀገር ያለችበትን ሁኔታ ከመጤፍ የማይቆጥሩ ተቃዋሚዎች (አብይ- ጠሎች) በየቀኑ ከሚረጩት ረብ-የለሽ ፕሮፓጋንዳ የተለየ አይደለም። እነ ኤርምያስ ለገሰ brain wash ያደረጒቸዉና መርዘኛ ሃሳባቸዉን ያጋቡባቸዉ ሰዎች ከእነርሱ ሊብሱ ግድ ነዉ።
የሰዉ ልጅ ክፉ ከሰራ የቀድሞ ጽድቁ እንደማይታሰብለት ሁሉ፦ መልካም ከሰራ ደግሞ የቀድሞ ሃጢአቱ እንደማይቆጠርበት መጽሀፍ ቅዱስ ያስተምራል። አልፎ አልፎ ይህን ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ መረዳት ይቸግራል። ይህ እውነት የተገለጠልኝ የደረጀ ከበደን ዘባተሎ ንግግር ካዳመጥኩ በሗላ ነበር።
ደረጀ በወጣትነቱ ዘመን በዘመራቸዉ መዝሙሮች የብዙዎቻችንን ልብ ለእግዚአብሄር ያስገዛ ተወዳጅ ዘማሪ መሆኑ አንድና ሁለት የለዉም። በጎልማሳነቱም ዘመን ፦ከመንፈሳዊነቱ ጎራ ወጣ ገባ እያለም ቢሆን በንስሃ የዘመራቸዉ መዝሙሮች ሳይቀሩ እንከን አልባ ናቸዉ።
በስራዎቹ ደረጀን አከብረዋለሁ። ስለስጦታዉም እግዚአብሄርን አመሰግናለሁ።ዛሬም የደረጀ ከበደ መዝሙሮች ለእኔ ጣፋጭ ናቸዉ። ለወደፊቱም የማዳምጣቸዉ፤ የምጽናናባቸዉ ዝማሬዎች ናቸዉ።የዛሬዉን ደረጀ ከበደን ሳየዉ ግን ፣ የቀደመዉ ጽድቅ አይቆጠርም የሚባለዉ እንዲህ አይነት ነገር ሲያጋጥም ነዉ በሚል ተረዳሁት።
ዶ/ር ደረጀ «ሀገር አልተወረረችም» not even close» ይላል። «ዝይገርም ሻሸመኔ»እንዲሉ- ሀገር ተወረረች የሚባለዉ ታዲያ መቼ ነዉ? ወያኔ ሸዋ ሮቢትን አልፎ ደብረሲና ላይ ህዝባችንን ሲወጋና ወደ ርእሰ-መዲናዋ ለመግባት ጥቂት ሲቀረዉ ሀገር ተወረረች ያልተባለ መቼ ሊባል ነዉ? What is he talking about?
ለነገሩ ደረጀ የሚጠይቃቸዉን ጥያቄዎች አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ይጠይቃል። እኔም እጠይቃለሁ። ከመጠየቅም አልፎ እበሳጫለሁ፤ እናደዳለሁ። ጦሩ ለምን ማፈግፈግን ብቻ የዉጊያ ስልት አድርጎ ይጠቀማል ስልም ጠይቄአለሁ። ዛሬም ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉኝ። ይሁንና በባህር ዳሩ ውይይት መንግስት « በመደበኛዉ ዉጊያ ብቻ ወያኔን ማሸነፍ እንደማይቻል በይፋ ግልጽ ሲያደርግ አእምሮ ያለዉ ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ ሊያስብ ይገደዳል። አንዳንዶቹን ጥያቄዎች በይደር ይይዛል። ያልተመለሱት ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነዉ በተገለጠልን ልክ ግን ሀገራችንን ከወያኔ ዳግም ወረራ ለመታደግ ማድረግ ያለብንን ሁሉ ማድረግ ምርጫ የሌለዉ ምርጫ ሆኖ አግኝተነዋል።
የት ነበሩ ይላል? ደረጀ።
ደረጀ ለመሆኑ እስከዛሬ የት ነበር? ወያኔን ከስልጣን ለማዉረድ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለዉን ሁሉ ወርዉሮ የወያኔን ስልጣን ባፍጢሙ ሲደፋዉ ደረጀ ከበደ ያደረገዉ አስተዋጽኦ ምን ነበር? እስኪ ለኢትዮጵያ ህዝብ- በተለይም እናገርለታለሁ ለሚለዉ የአማራዉ ማህበረ-ሰብ ያደረገዉን አስተዋጽኦ ይግለጽ።ሌላዉ ቀርቶ በምድረ- አሜሪካ ወያኔን በመቃወም በተደረጉ እልፍ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ የተሳተፈበትን ፤ድምጹን ከፍ አድርጎ ለአማራዉ ወገኑ ተሟጋችነቱን ያሳየበትን አንዲት ቁራጭ ፎቶ ያሳየን። ቤት ንብረታቸዉ በግፍ ለተቃጠለባቸዉ የአማራ ተወላጆች፤ ቤተሰባቸዉን በሞት ለተነጠቁት ከኪሱ መዝዞ ወይንም ህዝብ አስተባብሮ እርዳታ አሰባስቦ ለችግራቸዉ ደራሽ የሆነበትን አንድ አጋጣሚ ይግለጽ። መቹም የክርስትያን ወጉ አይቀርምና ቀኜ የሰጠዉን ግራዬ አላየም ሊለን ይችላል።
እነታማኝ ግን ይኸን ሲያደርጉ ነበር። (ለዝርዝር መረጃ ግሎባል አልያንስን ጠይቅ)
ወደ ነገሩ እምብርት ስገባ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ወደ ጦርነት መዝመት አጣጥሎ፣ አበሻቅጦ የገለጸበት መንገድ፣ የአማራ ምሁራንንና የአዲስ አበባን ህዝብ ማፈሪያ ናችሁ ያለበትን ንግግር ለሚሰማ «ሲያልቅ አያምር» ከማለት ሌላ ምን ሊል ይችላል?
ደረጀ ከበደ እንደዚህ አይነት ዘበዘብ ፦ወራዳ አስተሳሰብ ያለዉና ለከት የለሽ አሽሟጣጭ መሆኑን ስመለከት እኔ ደግሞ፤ ደግሜ ደጋግሜ አፈርኩበት። አንድ ሁለት ቪዲዮዎቹን አይቻለሁ። ሃሳብን በመግለጽ ሙሉ ለሙሉ የማምን ብሆንም የደረጀ መርዛማ ቅስቀሳዎች ሀሳብን በነጻነት መግለጽ የሚባለዉ መርህ አይገልጻቸዉም።ተራ ፤ርካሽ፤ እዚህ ግባ የማይባል ፍሬ ከርስኪ ንግግሮች ናቸዉ።የጥንቱ ዘማሪ ደረጀ ከበደ የዛሬዉ የኢትዮ 360 አዲስ ምልምል ለካ መዘመር እንጂ መናገር አትችልም ኖሯል።እግዚአብሄር በስጦታዉ አይጸጸትምና ዛሬም ያ- መረዋ ድምጽህ አልተለየህም ብዬ አምናለሁ።እባክህ « ከአድማስ ማዶ ያለች ሀገር የማስባት» ብለህ ዘምርላት። ለአማራዉ ያልሆነች ኢትዮጵያ ለኔ ምኔም አይደለችም ያልከዉን ወደር የለሽ የሀገር ዘለፋ ያስተሰርይልህ ይሆናልና። በመርዛማ አስተሳሰብ የአማራዉን ማህበረ-ሰብ ለማነሳሳት የተዉተረተርክበትን እርባና ቢስ ንግግር ለኢትዮ 360 መልማዮችህና ለዚያ ዘመድኩን ለሚባል ሰዉ ተዉላቸዉ።እነርሱ አዛኝ ቅቤ አንጒችነቱን በሂደት ተክነዉበታል።
ወያኔ በጦር ሲወጋን ፤ሀገርን በፕሮፓጋንዳ ከመዉጋት በሚገኝ እንጀራ የለወጡ ክፉዎች የቱንም ያህል ሊያጥላሉ ቢሞክሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታሪክ የጣለበትን ሀገር የማዳን ዘመቻ በመምራት ላይ ይገኛል። ገና አፍ የከፈተ እምቦቃቅላ የማይናገረዉን ንግግር መናገር ራስን ያስገምታል እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አይጎዳዉም። እስኪ በየት ሀገር ነዉ የአንድ ሀገር መሪ እዚህ ደርሳችሁ፣የማስተዳድረዉን ህዝብ ገሚሱን ፈጅታችሁ ትመለሳላችሁ ብሎ ከሀገር አፍራሾች ጋር የሚዋዋለዉ? ጠላቶቹ እንደሚሉት ለስልጣኑ ሟች የሆነ ሰዉስ ማንም ሳያስገድደዉ ስልጣኑን ለምክትሉ አስረክቦ ጦር ሜዳ ይሄዳል ወይ?
በመጨረሻም ፤ ትህነግ ራያን ሲወር እነ ታማኝ በየነ የት ነበሩ? እነ ነአምን ዘለቀ የት ነበሩ ? እነ አንዳርጋቸ,ዉ ጽጌ የት ነበሩ?ላልከዉ መልሴ አንተ የት ነበርክ የሚል ይሆናል።ለነገሩ እነርሱ የነበሩበትንም ልነግርህ እችላለሁ።
ለማይቀረዉ የህልዉና ጦርነት እየተዘጋጁ ነበር።
አንተ በጎደፈ ንግግር ያጣጣልካቸዉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ባለፉት ዘመናት ያለአንዳች መታከት በእዉቀታቸዉ፤ በሙያቸዉ በገንዘባቸዉ እና በጊዜአቸዉ ለሀገራቸዉና ለህዝባቸዉ ከትህነግ የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ መላቀቅ ከፍተኛ ድርሻ ያበረከቱ ናቸዉ። እንደሁኔታዉ አስገዳጅነትና እንደ ትግሉ ጥልቀት የሞቀ ቤታቸዉን ትተዉ ሀገራቸዉ በምትፈልጋቸዉ መስክ ሁሉ ተሰማርተዉ እጅግ የከበረ ተጋድሎ ፈጽመዋል።በዚህ ምክንያት በወያኔ ጥርስ ተነክሶባቸዉ አንዳንዶቹ በሌሉበት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል አንዳንዶቹ በባእድ ሀገር ከአዉሮፕላን ላይ ተጠልፈዉ ሰዉ በሌለበት ጭለማ ክፍል ታስረዉ መከራ ወርዶባቸዋል። አሁን ደግሞ ወያኔ ኢትዮጵያን ዳግም ልግዛት አለያም ልበትናት ብሎ ጦር ሰብቆና በህዝብ ማእበል ታጅቦ ሀገራችንን የደም ምድር ባደረጋት ጊዜ ቤት ንብረቴን ክብሬንና ልጆቼን ሳይሉ ወደ እናት ሀገራቸዉ በመትመም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ጦር ሜዳ ናቸዉ።
እንግዲህ እነታማኝ፣ እነ አንዳርጋቸዉና እነ ነአምን የት እንደነበሩ ከነገርኩህ ዘንዳ አንተ ደረጀ ከበደ ደግሞ የት እንደነበርክ ንገረን።ዛሬስ የት ነዉ ያለኸዉ?
ይቅርታ አድርግልኝና የቀደመ የዘማሪነት ዝናህን መያዣ አድርገህ እንደአቅምህ አፍራሽ ተጽእኖ ፈጣሪ ለመሆን ዳዴ እያልክ ይመስላል። ወደ ልቦናህ ተመለስ።የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ ግፍና መከራ ተቀብሏል። አማራዉ ደግሞ በከፋ ደረጃ ግፍና መከራ ተቀብሏል። ሆኖም መብቱ የሚከበርለት እናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ስትኖር ስለሆነ ያንተን ዝባዝንኬ ሰምቶ ለሀገሩ ዘብ ከመቆም አይመለስም።
ዝማሬዉ ከሰለቸህ ሌላ hobby ፈልግ። ፖለቲካዉን ወይ በደንብ አታዉቀዉም ወይም ሸፍጠኛ ነህ።