ሱሌይማን መሀመድ
“….አፍሪካውያን በጠራራ ፀሃይ ወጥተው መሪዎቻቸውን የሚመርጡት የመረጧቸው መሪዎች ለሚሰሩት ስራ ሃላፊነትን እንዲወስዱ፣ ተጠያቂ እንዲሆን እና የሚመሩትን ህዝብ ሁለንተናዊ ህይወት እንዲያሻሽሉለት እንጂ ከአሜሪካ እና አውሮፓ ገንዘብ ለምነው እንዲቀልቡት አይደለም! የአፍሪካ መሪዎች መማር ያለባቸው የልመና ጥበብን ሳይሆን በራሳቸው መንገድ እንዴት ህዝባቸውን ከድህነት ማውጣት እንደሚችሉ ነው። የሚገርመው የአፍሪካን ችግር የሚያጠኑት ነጮቹ ናቸው! የአፍሪካ ኢኮኖሚ በምን መልክ መመራት እንዳለበት አቅጣጫ የሚሰጡን ነጮቹ ናቸው! ጥናታዊ ፅሁፍ የሚሰሩልን ነጮቹ ናቸው! ምን ያህል ገንዘብ እንደሚረዱንም የሚወስኑት እነሱ ናቸው! እርዳታ የአፍሪካ መሪዎች ዋነኛ ሃላፊነታቸውን እንዲዘነጉ እና እንዲሰንፉ አድርጓል! የአፍሪካ ሃገራት የእርዳታ ሱሰኛ እስኪሆኑ ዳርጓቸዋል።
አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሃገራት የአመት በጀታቸውን ሳይቀር የሚሸፍኑት ከእርዳታ በሚገኝ ገንዘብ ነው! ነጮቹ “…አፍሪካ በወባ በሽታ አለቀች!..” ብለው ብዙ ሚልዮን አጎበሮችን ገዝተው በእርዳታ ይሰጡናል! ነገር ግን ይህንን አጎበር በጥራት መስራት የሚችሉ የአፍሪካ የንግድ ተቋማት አሉ! ለምን ገንዘቡን ሰጥተዋቸው እነሱ እንዲያመርቱ አያደርጉም? ለምን የስራ እድል ለአፍሪካውያን አይፈጥሩም? አጎበሮቹን ግን የሚገዙት ከራሳቸው የንግድ ተቋማት ብዙ ሚልዮን ዶላሮችን ከፍለው ነው! ያ ገንዘብ አፍሪካ መጥቶ ገበያ ውስጥ ቢገባ ሁለንተናዊ ጥቅም ነበረው! ያንን ግን በጭራሽ አያደርጉም! የሚያሳዝነው በቀን ሶስት ሺህ እና በአመት 1 ሚልዮን አፍሪካውያን በወባ ምክንያት እስካሁን ያልቃሉ! ከዓለም 90% በወባ ምክንያት ሟቹ እዚሁ አፍሪካ ውስጥ ነው!