>
5:09 pm - Wednesday March 3, 3660

ይካአሎ ለምን ተመልሶ መጣ? (ኦሀድ ቢንአን)

ይካአሎ ለምን ተመልሶ መጣ?

ኦሀድ ቢንአን

 

*…. ምጽዋ የካቲት 1፣ 1982 ዓ.ም፤  
በወፍ በረር አንዴ ወደኋላ ደረስ ብለን እንመለስ፤ ዘመቻ ፈንቅል የካቲት 1፣ 1982 ዓ.ም ምጽዋ፤ የቀይ ባሕር ዳርቻ፤ የይካአሎ አሻራ ያረፈበት ጦርነት፤
ሞቃታማው አየር ከተማዋን አወብቋታል፤ የጉርጉሱም የመዋኛ ዳርቻ በሰዎች ተሞልቶ ውሏል፤ እነዳንስ ማሪያ ለምሽቱ መርከበኞችና ሌሎች እንግዶቻቸው እየተዘጋጁ ነው፡፡ ነገር ግን የሕዝባዊ ግንባር 52ኛ 70ኛ  85ኛ እና 96ኛ ክፍለጦሮች ሌሊቱን ሲገሰግሱ አድረው በምጽዋ ዳርቻዎች ላይ ተጠግተዋል፤ ከተማዋን ይጠብቅ የነበረው የ6ኛ ነበልባል ክፍለ ጦር አካላት በነበሩት ሶስት ብርጌዶች ላይ ጦርነት ሊከፈቱ ነው፡፡ ተራዋ የደረሳት የምጽዋ ከተማ የመጀመሪያዋን ጥይት ሰማች፤ ከባድ መሳሪያዎች ተከታትለው እያረፉባት ህንጻዎቿና ነዋሪዎቿ ተንቀጠቀጡ፤ መስታወቶች መነቃነቅና መርገፍ ጀመሩ፡፡
የይካአሎ ሰራዊቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ የክፍለጦሩን መምሪያ ተቆጣጠሩ፤ ይካአሎም በጦርነቱ ውስጥ ከስትራቴጂስትነት እስከ አዋጊነት እንዲሁም ተዋጊነት ቦታ እና ሁኔታ እየለዋወጠ የድርሻውን ይወጣል፡፡ ጦርነቱ ቀጠለ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከአስመራ ሠራዊት ከማንቀሳቀሱ በፊት የሕዝባዊ ግምባር ወታደሮች የካቲት 2 የአስመራ-ምጽዋን መንገድ ዘጉና የምጽዋ አውሮፕላን ማረፊያ የአማራጭነቱን ሚና እንዳይጫወት ጥቃታቸውን አጠናከሩ፤ የተዘጋውን የአስመራ ምጽዋ መንገድ ለማስለቀቅ ዝነኛው የ18ኛ ክፍለጦርና ከ16ኛው ክ/ጦር ጋር ቢገሰግሱም የምፅዋ መንገድ ለመጨረሻ ጊዜ ተዘግቶ ቀረ፤ ራስ አሉላ አባ ነጋ ጣሊያኖችን የደቆሱባት ዶግኣሊም የአንድ መቶኛ ዓመት የድል በዓሏን ካከበረች ከሶስት አመታት በኋላ በሕዝባዊ ግምባር እጅ ወደቀች፤ የካቲት 4 ይካአሎና ጓዶቹ ወደቡንና የባሕር ኃይሉን ማዕከላዊ ትዕዛዝ ማጥቃት ጀመሩ፡፡ እስከ የካቲት 10 ድረስ ጦርነቱ ቀጠለ፤ አውደውጊያው የብዙ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ውድ ህይወት ወሰደ፤ ብ/ር ጀነራል ተሸመ ተሰማና በርካታ ጓዶቻቸው የአጼ ቴድሮስን ቀን ይስጠኝ ብለው እስከመጨረሻው አቅማቸው ተዋጉ፤ ምጽዋ በሕዝባዊ ግምባር እጅ ውስጥ መግባቷ አይቀሬ ሲሆን ጀነራል ተሾመና ጓዶቻቸው የሽጉጦቻቸውን አፈሙዞች ራሳቸው ላይ እየቀሰሩ ምላጮቹን ሳቡ፤ የነይካአሎ የአስር ቀናት አውደ-ውጊያ በዚህ ተጠናቀቀ፡፡
ይካአሎና ጓደኞቹ በርካታ ምርኮኞችንና እና አስከ 163 የሚደርሱ ታንኮችና ብረት ለበስ መሳሪያዎችን፣ 391 ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች፣ 62 የጭነት መኪናዎች፣ 131 መድፎች ከ16ሺህ ገደማ ጥይቶቻቸው ጋር፣ 26 መካከለኛ መድፎች፣ 14 ባሊስቲክ ሚሳይል (አርባ ጎራሽ) ተኳሽ መኪኖች፣ 76 ሞርታሮች፣ 157 ፀረ-ታንክና 131 ፀረ-አውሮፕላን መሳሪያዎች ከ200 ሺ በላይ ጥይቶች ጋር፣ 10 ሺ የሚጠጉ አውቶማቲክ መሳሪያዎች ከ11 ሚሊዮን ጥይቶች ጋር እንዲሁም ሌሎች የጦር ሜዳ ግብኣቶችን ገሚሱን ገቢ አደረጉ፤ ገሚሱን አወደሙ፤ የነይካአሎ ሜካናይዝድ ወታደሮች የማረኳቸውን ታንኮች እዛው መልሰው ለማጥቃት ተጠቀሙቧቸው፡፡ ከምጽዋ በኋላ አሥመራን ከቦ ቀለበት ውስጥ የማስገባቱን ዘመቻ ተያያዙት፤ ወደ ሰላሳ አመት የሚጠጋ ልምዳቸውን ይዘው በታሪካቸው ከፍተኛ የሆነውን ወታደራዊ አውደ-ውጊያ ፈጽመው ድልን ተቀዳጁ፤ በኮለኔል መንግሰቱ አመራር ተስፋ የቆረጠው የኢትዮጵያውያ ሠራዊት ልቡ ተሰበረ፤ ዘመቻ ፈንቅልን አጠናቅቀው እነይካአሎ ትግላቸውን ሲቀጥሉ ስትራቴጂክ አጋር የነበረውን ህወሓትን አግዘው አዲስ አበባ ድረስ አስገቡና በትረሥልጣኑን አስጨበጡ፡፡ የኤርትራም መገንጠል ቅርብ ቢሆንም አሜሪካኖች አንድ አዲስ ሃሳብ አመጡ፡፡
ኢትዮጵያን ግዙ  
እነይካኦሎን ሔርማን ኮሔን “አሁን አትገንጠሉ፤ ሕዝበ-ውሳኔውን ቢያንስ አንድ አምስት አመት አቆዩት፤ አሁን እናንተ የምትመሩት ጥምር መንግስት አቋቁሙ፤ እኛም እናግዛችኋለን፤” አሉ፡፡ እነይካኣሎ የሔርማን ኮሄንን ሃሳብ አልተቀበሉትም፡፡ “እኛ የተዋጋነው በኢትዮጵያ ላይ ለመሾም ሳይሆን ኤርትራን ነጻ ሃገር ለማድረግ ነው፤ ይህን አማራጭ ከተቀበልን የሰላሳ አመቱን ትግላችንን በዜሮ ያባዛዋል፤” አሉና አስመራ ላይ ሆነው ሁኔታውን መከታተል ቀጠሉ፤ ሕዝበ-ውሳኔው ተካሄደ፤ አዲሲቷ አፍሪካዊት አገር ተወለደች፤ በመጀመሪያዎቹ አራት እና አምስት አመታት ኤርትራ አስደሳች የሆነ ሁለንተናዊና ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት እድገት አስመዘገበች፤
ባድመን ትመልሱልን?
የህወሃት መንግስትም መሃል አገር ውስጥ ያለበትን የተወሳሰበ ሁኔታ እስኪያረጋጋና እስኪረጋጋ ለ7 አመታት ጠበቁና ኤርትራውያን “በሉ እንግዲህ አሁን ደግሞ በበረሃው ስምምነታችን መሰረት የባድመን እና ሌሎች ወደኢትዮጵያ የተካተቱ መሬቶችን መልሱልን፤” አሉ፤ እንደተጠበቀው ህወሓት አሻፈረኝ አለና የኢኮኖሚስት መጽሔት “በማበጠሪያ የሚጣሉ የሁለት መላጣዎች ጦርነት፤” ያለው ግጭት ተለኮሰ፤ ይካአሎም እንደገና አብሮ ዘመተ፡፡
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነና ነገሩ በመላው ኢትዮጵያ ለአሰርታት ኑሮ መስርተው ይኖሩ የነበሩ ኤርትራውያንም “የአይናችሁ ቀለም አላማረንም” ተብለው በትጋት በጥረትና በንጹህ ላባቸው ያፈሩዋቸውን በክብር የያዟቸውን ንብረቶቻቸውን ቅጥ ሳያስይዙ እየታፈሱ መባረር ጀመሩ፡፡ ድብቁን የህወሓትን ማንነትንና ምንነትን ያሳየው አጋጣሚ ተከሰተ፤ ወርቅ ላበደረ ጠጠር ሆነና ነገሩ የህወሓት ክህደት ይካአሎንና ጓዶቹን በጣም ጎዳቸው፤
ምክንያት አልባ የተባለውና ህወሓት በ17 አመታት ውስጥ ከሰዋቸው ታጋዮቹ በላይ በአስራ አምስት ቀናት ጦርነት ከሰባ ሽህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን የማገደው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ፈንጅ ጠራጊ የሆኑበት አሳፋሪው ውጊያ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ቢጠናቀቅም የማሰሪያው ድሉ ግን የኤርትራ ሆነ፤ “ኦፕሬሽኑ ስኬታማ ነበር፣ ነገር ግን ታካሚው ሞቷል፤” እንደተባለው አለም አቀፉ ፍርድ ቤት መሬቶቹን የኤርትራ መሆናቸውን አስረግጦ ፈረደ፤ ስዩም መስፍን አይኔን በጨው ብለው ለኛ ነው የተፈረዱት የሚለውን ጋዜጣዊ መግለጫቸውን ሰጥተው ሕዝቡን በሓሰት ጮቤ አስረገጡ፤ ነገር ግን አተኩሮ ቃለምልልሳቸውን ላስተዋለው ስዩም አፋቸው ደርቆ ምላሳቸውን ከትናጋቸው ማላቀቅ እየተቸገሩ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነበር፤ ውሸት የህወሓት ባሕሪ መሆኗን ለሚያውቀው ይካአሎ ያ ቀን የተበሳጨበትና ለኢትዮጵያ ሕዝብም ያዘነበት ቀን ነበር፤
 ሰላም-የለሽ-ጦርነት-የለሽ (No peace-No war)
እውነታው ሌላ ነው፤  የአልጀርሱ ስምምነት ቦታዎቹን ለኤርትራ የመመለስን ግዴታ ቢያስቀምጥም ህወሓት ወይ ፍንክች፤ ይካአሎና ጓዶቹ በብይኑ ደስተኛ ቢሆኑም ህወሓት ግን መሬቶቹን የመመለስ ቅንጣት ያክል ፍላጎት እንደሌለው መገመታቸውና ያላለቀውን የቤት ሥራ መጨረስን ማቀድ ነበረባቸው፡፡ ህወሓትን ያውቁት አደለ፡፡ የህወሓትን እርምጃዎች በሙሉ የክህደትና የክፋት መልካቸውን ያጋለጠው የፍርድ ቤት ውሳኔ ለምን ኤርትራን በዚህ ደረጃ መጉዳት እንዳስፈለገ ለይካአሎና ጓዶቹ ጥያቄን ፈጠረ፤ አዲስ ሰላም-የለሽ-ጦርነት-የለሽ (No peace-No war) የተባለው ምዕራፍ ተከፈተ፤ ነገሩን ቶሎ በሰላም ቋጭቶ ከመገላገል ይልቅ ትግራይንም ክፉኛ የሚጎዳ እቀባ መራዘም ለምን አስፈለገ፤ ሞት የቀደማቸው መለስ ያውቁት ይሆን? ምንአልባት ወደፊት በምትበተነው ኢትዮጵያ ትግራይን ጨምሮ ከሚፈጠሩት አዳዲስ አገሮችና ጎረቤቶቿ በላይ እንዳትሆን ከወዲሁ እራስን እየጎዱ የኤርትራን የመስበር ምቀኛነታዊ አላማ ያለው ይሆን? ይህን አለመጠርጠር ለኤርትራውያኑ የዋሕነት ሆነ፡፡
ይካኣሎ በሁኔታው ቢያዝንም እና ቢበሳጭም የማታ ማታ እውነት አሸንፋ እንደምትነሳ አምኖ መጠበቅን መረጠ፤ ፍጻሜው መቼ እንደሆነ በማይታወቅበት ሁኔታ ቀጣዮቹ አመታት ይዘውት የመጡት ፈተናዎች ከበድ ያሉ ሆኑ፤ ፈተናዎቹ የኤርትራን ኢኮኖሚ የሚያሽመደምዱ በእቀባዎች ጋጋታ የተሞሉ ነበሩ፡፡
የዕቀባ ሴራዎች 
ወያኔ በአንድ ወቅት ህወሓት በረሃ እያለ ከሕዝባዊ ግምባር በእርዳታ ያገኛቸው የነበሩትን መሳሪያዎች ከተከማቹበት መጋዘን አውጥቶ በድብቅ ለአልሸባብ አሸባሪዎች እንዲደርሱ አደረገ፡፡ የአልሸባብ ወታደሮች በሚማረኩበት ጊዜ የመሳሪያዎቹ መለያ ቁጥር በሻዕቢያ ይዞታ የተመዘቡ መሆናቸው ይታወቅ ስለነበረ “ለካ ኤርትራ ነች የምታስታጥቃቸው፤” ተብሎ የማሳጣቱ ክፋት ተሳካለትና የእቀባው ማነቆ ጠበበ፤ ኢኮኖሚያዊ ትስስሯ ባሕሪያዊ ሆኖ ከኢትዮጵያ ጋር የበለጠ እንድትወዳጅ ቢያስገድዳትም ደንቀራው ህወሓት የጉሮሮ አጥንት ሆኖባት ቀጠለ፤ ኢኮኖሚያዊው ጫና አጉረምራሚዎችን ቢፈጥርም ኤርትራውያን የችግራቸውን ምንጭ ስለሚያውቁ ከባዱን ዘመን በትዕግስት ማሳለፍ ወሰኑ፤ ኤርትራዊ በኤርትራዊ ላይ መሳሪያ አንስተን አንዋጋም ብለው በአንድ አቋም ጸንተው ቀጠሉ፡፡
 ህወሓት በድንጋይ ውርወራ
ኤርትራ በዲፕሎማሲ ኢከኖሚያዊና ፖለቲካዊ እቀባዎች ተቀፍድዳ ዘመናት አለፉ፤ የተባበሩት መንግስታት አሉታዊ ፍረጃ ጫናውን አክብዶባት መለማመጡን አላደርገውም ብላ ከብዙ አለም አቀፍና አካባቢያዊ ትሩፋቶች ታግዳ ዘመናትን አስቆጠረች፤ ይካአሎም ከህወሓት መራሹ መንግስት ጋር የሚዋጉ ኢትዮጵያዊ አካላትን እያሰለጠነና እያበረታታ በሚጓዝበት ወቅት ላይ ቲም ለማ ከተፍ አለ፡፡ የህወሓት ፖለቲካዊ ፍልስፍና ሁሉን አቀፍ፣ ዘለቄታዊነቱ አስተማማኝነቱ እና ያለምንም ወታደራዊ ጫና ራሱን ችሎ መቆም እንደሚችል የሚፈተንበት ወቅት ላይ ተደረሰ፤ ፍልስፍናውም ፈተናውን ወደቀና በመሳሪያ ወደ ሥልጣን የመጣው ህወሓት በድንጋይ ውርወራ ወደቀና ወደ መቀሌ ተሰበሰበ፡፡ መቀሌ ግን ጠበበችው፡፡
ጌም ኦቨር
ይካኣሎ ብድግ አለ፡፡ እውነትም ጌም ኦቨር ሆነ፤ የኢትዮጵያውያንንም ቀልብ ተቆጣጠረ፤ አዲስ መንግስትም ለውጥም በኢትዮጵያ ሰማያት ስር ታየ፤ ሁኔታውን በከፍተኛ ትኩረት ይከታተል የነበረው ይካአሎ የጠ/ሚ አብይን መመረጥ በከፍተኛ ደረጃ አወደሰ፤ አዲሱ የዶ/ር አብይ አሕመድ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት ተቀብዬ ተግባራዊ አደርጋለሁ አለ፤ አብይ አሕመድን የያዘው አውሮፕላን አሥመራ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ይካአሎና ጓዶቹ በደስታ ፈነደቁ፡፡ “አቢቹና ኢሱ” የወቅቱ ርዕሰ ዜናዎች ሆኑ፤ አብይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልመትን ሲቀበሉ ህወሓትን ደበረው አይገልጸውም በሚባል ደረጃ ማጉረምረም ጀመረ፤ ከድርጅቱ መዋቅር ውጭ ሆነው የሚያገለግሉት ነባር ታጋዮቹ የሁለቱን መሪዎች ፍቅር ማጠልሸት ጀመሩ፤ “ስምምነቱ አየር ላይ ነው፤ ኢትዮጵያን ሊጎዳ ይችላል፤ ዝርዝሩን አናውቀውም፤” የሚሉ ስሞታዎችን ማሰማት ቀጠሉ፤ ይካአሎና አጋሮቹ ኢትዮጵያ መምጣት እና መመላለስ ጀምረዋል፤ ህወሓት ግን ደብሮታል፤ ቀስ በቀስ “ደርጊ መጺኡ፣ የኃይለሥላሴ የልጅ ልጆች መጡ፤” እያሉ ሲያጉረመርሙ ለይካኣሎ ለዘመናት ሲናፍቀው የነበረውን ሁኔታ እየተመለከተ ይዝናናበት ጀመር፡፡
ከእለት ወደ እለት የጠ/ሚ አብይ አሕመድና የህወሓቶች ግኑኙነት እየሻከረ መሄድ ጀመረ፤ የስምምነቱን ጭብጥ በጽሁፍ ማየት ያልቻሉት ህወሓቶች ጥርጣሬያቸውን መግለጽ ጀመሩ፡፡ ታሪክ ተለወጠ፤ ህወሓት ከፈላጭ ቆራጭነት ወደ ትዕዛዝ ተቀባይነት ወረደና አልዋጥለት አለ፡፡
ጠጅ ካሰከረው ሥልጣን ያሰከረው
ነገሮች ፈጠኑ፤ ህወሓት የክተት እና መክት ዘመቻውን በይፋ ያጧጡፈው ጀመር፤ ኢትዮጵያና ኤርትራም ህወሓት በአደባባይ ለሚናገረውና ለደገሰው ክፋት ምላሽ ለመስጠት በሚሥጥር መዘጋጀት ጀመሩ፤ ህወሓት በአሸናፊነት እንደሚወጣው እርግጠኛ ወደሆነበት ጦርነት ለመግባት ሕዝቡን አዘጋጀ፤ መሃል አገር ያሉትንም “አገራችሁ ግቡ” እያለ እርግጠኛነቱ ላልታወቀ አገር ምስረታ ብዙዎችን አፈናቀለ፤ ኢትዮጵያውያን የአብይ አሕመድን የጫጉላ ጊዜ ሳይጨርሱ ያፈነገጠው ህወሓት የማዕከላዊ መንግስትን ውሳኔዎችና የምክር ቤት አዋጆችን በግልጽ መቃወም ጀመረ፡፡ ጠጅ ካሰከረው ሥልጣን ያሰከረው ሆነና ነገሩ በፈጠራቸው መደበኛና ዲጂታል ሚዲያዎቹ ግልጽ ተቃዉሞዎቹንና ማመጹን ማሰማት ጀመረ፡፡ ይካአሎም በንቃትና በዝግጁነት ራሱን አዘጋጅቶ ጠበቀ፡፡
ህወሓት ጥቅምት 24፣ 2012 ዓ.ም. ሰሜን ዕዝ ሰራዊት አባሎች ላይ አሳፋሪና አሰቃቂ የክህደት ጥቃቶች ፈጸመ፡፡ 27 አመታት እድል የሰጡት ኢትዮጵያውያንን አስደነገጠ፤ ማምለጫ የሌላቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደኤርትራ ድንበር ሸሹ፤ ይካአሎና ጓዶቹ በርህራሄና የክህደት ፍላጻ በወጋው ሓዘን ስሜት ተቀብለው አስፈላጊውን እንክብካቤ አደረጉ፡፡ የመከላከያው አባላት የክህደት ቀስት የፈጠረባቸውን ቁስል ይዘው ህወሓትን ለመቅበር ወደ ጦርነት ተመለሱ፡፡ የህወሓት ጦርነት በይፋ ታወጀ፤ በማግስቱ ማይካድራ ላይ ከ1,500 በላይ ንጹሃን ዜጎች ላይ የዘር ማጥፋት ድርጊት ፈጸመ፤ ይካአሎ በግርምት ለሚጠብቀው የቤት ሥራ ተጠንቅቆ ቆመ፡፡ የህወሓት ሚሳይሎች ወደ ኤርትራ ከተሞች ተተኮሱ፡፡
ህወሓት እያለ ኤርትራም ኢትዮጵያም ሰላም እንደማያገኙ ግልጽ ሆነና ይካአሎ ከሃያ ሶስት አመታት በኋላ ወደ ጦርነት ተመለሰ፤ የመጀመሪያው የመልስ ጦርነት ላይ አሜሪካና ወዳጆቿ ኤርትራ አጸፋዊ እርምጃ አለመውሰዷን አደነቁ፤ ይካአሎ ግን በነሱ አድናቆት የሚሸነገል አይደለምና ለማይቀረው ጦርነት ወገቡን ጠበቅ አደረገ፤ የኤርትራ ወታደሮች ድምጻቸውን አጥፍተው በጦርነቱ ውስጥ ከህወሓት ሰዎች ጠርቶ ያላለቀውን እና ከ80 ከመቶ በላይ የሚሆነውን ሰራዊቷን ወታደራዊና የጦር መሳሪያ አቅም ካጣችው ከኢትዮጵያ ጎን ተሰለፉ፡፡
ለዘመናት ቆሽታቸው ሲያር የነበሩት የወልቃይትና ራያ ሕዝቦችም ከመንግስት ጎን ተሰልፈው መግቢያ መውጫውን ዘጉበት፤ ህወሓት ያልጠበቀው ዱብ እዳ ሆነበትና ከተሞችን ለቅቆ በየተራራው መሸገ፤ በአስራ ሰባት ቀናት ጦርነት ቁርጭምጭሚቱ ደቀቀ፤ እየተንፏቀቀ ለአሜሪካና ወዳጆቹ ድረሱልኝ አለ፡፡ ሱዳኖች በታሪካቸው አድርገውት የማያውቁትን ጀብድ ሞከሩ፤ ወደኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው ገቡ፤ አላማቸው ለህወሓት መውጫ መግቢያ ቀዳዳ ለመፍጠር ነበር፤ ግን አልቻሉም፤ አሜሪካም ምንም ሳትሆን ኢትዮጵያን የወረረችውን ሱዳንን ዝም ብላ ሚሳይሎች የተተኮሱባትን ኤርትራን በጦርነቱ ውስጥ መሳተፍ አጥብቃ ተቃወመች፤ ተላላኪዋን እንዳጣችም ግልጽ ሆነ፡፡ ይካአሎ ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጎን ቆሞ መዋጋቱን ቀጠለ፡፡ ታሪክ ተለወጠ፤ ባድመ ለኛ ተፈርዳለች ብለው ውሸት በአደባባይ የተናገሩት ስዩም መስፍንና የህወሓት መስራች ጓዶቻቸው ፍጻሚያቸውን በተከዜ በረሃ ላይ ተገናኙ፡፡ ማንም አያሸንፈኝም ብሎ ለዘመናት ራሱን አግዝፎ የኖረውና ብቻውን ተዋግቶ የማያውቀው ህወሓት ውርደትን ተከናነበ፤
 ለኢትዮጵያ መልካም ለኤርትራ መልካም 
ኢትዮጵያን ከመፍረስ እየታደገ ባለበት ወቅት አገርን ከድተው ለማፍረስ ቆርጠውና ወስነው የሚዋጉት የህወሓት ፕሮፖጋንዲስቶች ይካአሎን የኢትዮጵያ ጠላት ነው የሚለውን ስም ማጥፋት ዘመቻቸውን አጠናከሩ፤ ጠላቷ ናችሁ ለተባሉባት አገር የክፉ ቀን ደራሽ ሆኖ የኤርትራም ህልውና ሥጋት የሆነውን ወያኔን አከርካሪውን የመስበሩን ተልእኮ ገፋበት፤ በርግጥ ኤርትራውያን ራሳቸውን ለማሰተዳደር እንጂ ይባል እንደነበረው በአረብ ፔትሮ ዶላር የሰከሩ የኢትዮጵያ ጠላቶች አለመሆናቸው ተረጋገጠ፡፡ በኢትዮጵያ ሃብት አለቅጥ የበለጸገውና የሰከረው ህወሓት ግን ከመቅበዝበዝ አልዳነም፡፡
የማናውቀው እቀባ እና የምናውቀው ሽንፈት የለንም፤” 
ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ የህወሓት አመራሮች ቴድሮስ አድሃኖምን ጨምሮ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻውን አጠናክረው ገፉበት፤ ድርጅታቸውም ከወደቀበት አዘቅት አዲስ ስልት ይዞ መጣ፤ የምዕራባውያንን መንግሰታት ትብብር ማግኘት፣ ሚዲያዎቻቸውን በገንዘብ መግዛትና የሃሰት ዜናዎችን እንዲያስተጋቡለት ማድረግ፣ የኢትዮጵያንና የኤርትራን መንግስታት በዘር ማጥፋት ወንጀል ማሳጣትና የመልሶ ማጥቃት ውጊያ ከፍቶ ወደ አዲስ አበባ ገብቶ መንግስትን መለወጥና ኢትዮጵያን መበተን አላማው እንደሆነ በግልጽ አውጆ ተንቀሳቀሰ፤ ይካአሎ ሳቅ ብሎ ቁርጠኛነቱን ጨመረ፤ ህወሓት ወደ ማሃል አገር ገሰገሰ፤ ይካአሎም በግልጽ ተናገረ፤ ወያኔ ደሴ ከደረሰ እኔ መቀሌ ነኝ አለ፡፡ ወያኔ ሰሜን ሸዋ ደረሰ፤ ይካአሎም ሥራውን አጠናክሮ ቀጠለ፤
ለአለም አቀፉ ጫና የማትንበረከከው ኤርትራ “የማናውቀው እቀባ እና የምናውቀው ሽንፈት የለንም፤” ብላ ከኢትዮጵያ ጎን በግልጽ ቆመች፤ አሜሪካም በኢትዮጵያና ኤርትራ ባለሥልጣኖች ላይ የጉዞ እቀባን አደረገችና እንደምትቀጥልበት አስጠነቀቀች፤ የኢኮኖሚ እቀባዎች ተደረጉ፤ እርዳታዎች ተቀነሱ፤ አጎዋ ተዘጋ፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ ግን የጀመሩትን ዘመቻ አጠናክረው ቀጠሉ፤ ይካአሎም ጨክኖና አምርሮ ተዋጋ፤ ህወሓት በገሰገሰ ቁጥር የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁርጠኛነት እየባሰና እየጨከነ ሄደ፡፡ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውና በቂ ሥልጠና ባልወሰዱ ወጣቶችና አዛውንቶች የተሞላውን ሰራዊቱን እያስጨረሰ የጭካኔ ጦርነቱን የቀጠለበት ህወሓት በቃህ ተባለ፤ ወደ አዲስ አበባ የሚገሰግሰው የህወሓት ባቡር ወደ ኋላ መመለስ ቢፈልግም እንኳን መቀሌ ከአሜሪካ የራቀች ገነት ሆነች፤ ይካአሎ በተለያዩ የማሃል አገር ቦታዎች ውስጥ ገብቶ መከላከያን መደገፉን ቀጠለ፡፡
መከላከያ ሰራዊትም በውስጡ የተሰገሰጉትን የህወሓትን ሰርጎገቦችንና ባንዳዎችን አጽድቶ ስውር መረቦችን በጣጥሶ ዘመቻውን አጠናክሮ ቀጠለ፤ አዲስ የአመራር ስሌት ይዘው የመጡት ጠ/ሚ አብይ አሕመድ የህወሓትን ግብአተ መሬት ለማረጋገጥ ቤተሰባቸውንና ሥልጣናቸውን ትተው ወደ ግንባር ዘመቱ፤ አመራራቸው ውጤት አመጣ፤ አሜሪካና ወዳጆቿ የአቋም መለሳለስ አሳዩ፤ ኢትዮጵያ አሸነፈች፤ ይካአሎም ታሪካዊ ውለታውን ተወጣ፤ ይካአሎ የኢትዮጵያ ጠላት ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያን መጉዳት የሚችልበት ታሪካዊ አጋጣሚ ከመቼውም በላይ በፊቱ ነበረ፤ ነገር ግን የይካአሎ ጠላት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን ለምንም የማይታመነውና በክህደት ታሪክ ገጾቹ የነተቡት ህወሓት መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል፤ ይካአሎ ወደ ኢትዮጵያም ከሰላሳ አመት በኋላ የተመለሰውም የዚህን ክፉ ጠላት ግብዓተ-መሬት እውን ለማድረግ ነው፤ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያንም ደስተኞች ናቸው፡፡ በተለያዩ የአለም ከተሞችና አደባባዮች #No More ብለው ጎን ለጎን የነአሜሪካን እና ወዳጆቿን ጫና ለማስወገድ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን አብረው ቆሙ፡፡
የአለም መንፈስ ተለወጠ፤ አፍሪካም #No More አለች፤ ህወሓት ለክፋት የጀመረው ዘመቻ ተገልብጦ ጠላቶቹን አንድ አድርጎ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የበለጠ ለሃገሩ ጨክኖና ቆርጦ እንዲቆም፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ለበለጠ የጋራ ጥቅምና አብሮ ማደግ እንዲተባበሩ ግኑኙነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያደረገ ውጤት ይዞ መጣ፤ የምዕራባውያኑ አለኝታዎቹም “ሥራው ያውጣው” ብለው እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን መሰብሰብ ጀመሩ፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ ላይ ሆነው አለምን አሸንፈው፣ የአፍሪካውያንን መንፈስ አነሳስተው፣ ለማንም የማይንበረከኩ ኩሩ ሕዝቦች መሆናቸውን አረጋግጠው ከፍ አሉ፤ ይካአሎ ከሰላሳ አመታት በኋላ ወደኢትዮጵያ ተመልሶ የመጣው ለዚህ ስኬታማ ተልዕኮ ነው፡፡
 እውን ይሄ አደባባይ 
የዚህን ጽሁፍ የማሰሪያ አርትኦት የሰራሁት የዋይልድ ኮፊ በረንዳ ላይ ቁጭ ብዬ በኮፊ አረቢካ የተቀመረውን ማኪያቶ ፉት እያልኩ ወደ ቀድሞው ጋዜቦ አደባባይ አቅጣጫ እየተመለከትኩና እየሰላሰልኩ ነበር፤ አይኖቼ አደባባዩ ላይ ከንቲባ ታከለ ኡማ በአሜሪካ ዋና ከተማ ስም የከተማዋን ከንቲባ ጋብዘው “ዋሽንግተን ዲሲ አደባባይ” ብለው የሰየሙት መካከሉ ላይ የተተከለውን እና እንደ አሜሪካና ኢትዮጵያ ግኑኙነት የተገጣጠበውን የላሜራ ሓውልት ላይ ተክዬ ነበር፤ በድንገት አንድ ጥያቄ ወደ አእምሮዬ መጣ፤ “እውን ይሄ አደባባይ አገራችንን በገሃድ ልታፈርስ ከጠላቶቻችን ጎን ቆማ አዲስ አበባ ልትያዝ ነው፣ ዜጎቼ ውጡ፣ እያለች መንግስት ግልበጣ ለማድረግ እቀባ በእቀባ ባሰቃየችን አሜሪካ ዋና ከተማ ስም ነው ወይስ ኢትዮጵያን ለመታደግ ውድ ህይወታቸውን ላስረከቡት ይካአሎና የትግል ጓዶቹ ነው?” አልኩኝ፡፡ ህወሓት የፍልስፍና ልዩነት ሳይሆን አገር የማፍረስ አጀንዳውን ይዞ ተግቶ ሲሰራ ይህን ለመቀልበስ ደግሞ ውድ ህይወቱን ላቀረበው ይካአሎ (የኤርትራ ታጋይ የክብር መጠሪያ) የኔ ሁለት ሽህ የሚሆኑ ቃላት ይበዙበት ይሆን? በፍጹም፤ እኛ እውቅና ካልሰጠነው ማን ይሰጠዋል? ዛሬ ካልሰጠነው መቼ እንሰጠዋለን?
ለይካአሎ ልባዊ ምስጋናዬን እያቀረብኩ ጽሁፌን በዚሁ እዘጋለሁ፤
“ሓዬ መንእስይ አርክቦ ጅግና
ባና ናጽነት በሪሁ ነሆ ወሊዑ ፋና፡፡”
እያለ ይካአሎ ዘመቻውን አጠናከረ፤
Filed in: Amharic