>

የመጨረሻችን ያድርግልን . . . ! (አሳፍ ሀይሉ)

የመጨረሻችን ያድርግልን . . . !

አሳፍ ሀይሉ

(የአማራና ትግራይ ትብብርና አንድነት – የኢትዮጵያ ተስፋ!)
የአማራው ህዝብ ከትግራዩ ወንድም ህዝብ ጋር ወደ መጠነ-ሰፊ ሕዝባዊ ጦርነት እንዲገባ የተደረገበት ሸፍጥና ደባ ለኢትዮጵያ መፃዔ ውድቀትና ፍፃሜ ትልቁን መጋረጃ የቀደደ አሳዛኝ ትርዒት ነበር። አሁንም ነው።
በታሪክ ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር በደምና አጥንት የመሠረቱ፣ በእጅግ አስቸጋሪ የታሪክ ውጣውረዶች ውስጥ አልፈው ሀገራቸውን ያቆዩ፣ ሁለት ተመሣሣይ ባህል፣ እምነት፣ መልክና አስተሳሰብ ያላቸው ወንድማማች ህዝቦች፣ ከየራሳቸው ማህፀን በበቀሉ ጉግማንጉጎች አጋፋሪነት እየተጨፋጨፉ ይገኛሉ።
ለዚህ ጦርነት ብዙ ታሪካዊ ምክንያቶችና ቁርሾዎችን መደርደር ይቻላል። እውነታም አላቸው። ነገር ግን በሠላምና በጥበብ ሁለቱን ሕዝቦች አስማምቶና አቻችሎ ሀገርን በሠላም መምራት ሲቻል፣ እርስበርስ ተዋግተው እንዲጨራረሱና፣ ኢትዮጵያ ጠባቂዋን አማራውን ወይም ትግሬውን ቀኝ እጇን እንድታጣ ለማድረግ የተሄደበት ውጫዊና ሀገርበቀል ደባ ያሳዝናል። ያንገበግባል።
ይህንን መገንዘብ ያቃተውና በቁስሉ ላይ በርበሬ እየነሰነሱ ከወንድሙ ጋር ሲያጋድሉት “ሆ” እያለ ለመሞትና ለመግደል የሚጎርፈው ንፁሃን ሀገሩን-ወዳድ ኢትዮጵያዊ ወጣት የገባበት መቅሰፍትና መጠፋፋት እጅግ ያሳዝናል በእውነት።
የአማራውም ሆነ የትግራዩ ወጣት ትውልድ፣ የተነገረውንና የተሰበከውን የጉግማንጉጎች ዲስኩር አምኖ ያለችውን አንድ ሀብት – አንዲት ህይወቱን ከወገኑ ጋር በመጨፋጨፍ የሚሰዋ ግራ የተጋባ፣ እና ላገሩ የጠቀመ በመሠለው ጎራ ተሰልፎ እርስበርስ የሚተላለቅ ያልታደለ ትውልድ ነው። ራሱን በራሱ በፈቃደኝነት እያወደመ ያለ፣ ሊታዘንበት ሳይሆን ሊታዘንለት የሚገባ የገፈቱ ቀማሽ ሕዝብ ነው።
በእርግጥ አማራው ታሪካዊ ግፍ የተፈራረቀበት ሕዝብ መሆኑ አይካድም። ትናንት አማራውን በማግለል፣ በስመ “ደርግ” እና በስመ “ኢህአፓ”፣ በስመ “የኢትዮጵያ ሠራዊት” በመጨፍጨፍ፣ ኃይልና ሀብት በማሳጣት፣ በገዛ ሀገሩና ወገኑ በስማ-በለው በጠላትነት እንዲፈረጅ በመሥራት፣ ወዘተ. በአማራው ሕዝብ ላይ የተፈፀሙበት ግፎች ተነግረው አያልቁም።
በአማራው ሕዝብ ላይ የደረሰበት ውድቀትና መከራ ግማሹ በፖለቲካና በሀገር ሽፋን ተከድኖ ያለነጋሪ ተሸፍኖ ቀርቷል። አሁንም ድረስ የአማራው ሕዝብ አከርካሪ መሠበር የአማራው ሕዝብ ጉዳት ብቻ መስሎ የሚታያቸው፣ የአማራውን መፃዔ ሞትና ቀብር በደስታ የሚጠባበቁ ጠላቶችና ነሆለሎች አልጠፉም።
አማራው ሲሰበር ኢትዮጵያም ናት አብራ የምትሰበረው። ይህ አመክንዮ ግን ለአማራው ብቻ የሚሠራ አመክንዮ አይደለም። ለትግሬውም ይሠራል። ትግሬውም ሲሰበር ትግሬው ብቻ አይደለም የሚሰበረው፣ ኢትዮጵያም ናት አብራ ተሰባሪዋ።
የውጪ ጠላት የማይደፍረን አንዳችን ከሌላኛችን ጋር ተባልተን፣ አንዳችን ሌላኛችንን ሰባብረን ስናስቀር አይደለም። አንዳችን ለሌላኛችን አለኝታ ሆነን መድረስ ስንችል፣ አንዳችን ለሌላኛችን መቆም ስንችል፣ መቆርቆር መደረብ ስንችል ብቻ ነው።
ዛሬ ትግሬ-ወያኔ.. አማራ-ምናምን.. እያልን አንዳችን የሌላኛችንን አቅም አድቅቀን እርስበርስ ከምድረ-ገፅ ለመጠፋፋት እየሠራን ያለው ራስን-የማውደም አሳዛኝ ተግባር ለጠላቶቻችን ሠርግና ምላሻቸው ነው።
ግብፅ ከእንግዲህ የሚተባበርባት ትግሬና አማራ እንደማይኖር ታውቃለችና ደስ ይላታል። ሱዳን ከእንግዲህ በጋራ ሆ ብሎ የሚነሳባት ትግሬና አማራ ስለሌለ ደስታውን አትችለውም።
ኤርትራ (የሀበሻ ልጆች በተመሣሣይየውድመት አዙሪት ገንጥለው የመሠረቷት ሀገር መሆኗ እንደተጠበቀ ሆኖ) አማራውና ትግሬው በጋራ ተባብረው ከፊቷ እንዳይቆሙባት ለማድረግ በመቻሏ ደስታዋ ሰማይ-ጠቀስ መሆኑ አያጠያይቅም።
የውጪ ጠላት ብቻም አይደለም በእኛ መገዳደልና መጨራረስ ጮቤ የሚረግጠው። በኢትዮጵያ ትልቅነትና የተባበረ ኃይል ፍራቻ የሚያድርባቸውን እንደ ጂቡቲ ያሉትን የቅርብና የሩቅ ጎረቤቶቻችን ብቻም አይደሉም።
ከሀገር ውስጥም ሆነው ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር አፍርሰን በየዘራችን መንግሥት እንመሠርታለን በማለት ለዓመታት ክፋትና ሞትን ሲጎነጉኑ የኖሩ ኢትዮጵያን ማየት የሚያንገፈግፋቸውን የራሳችንን ዘረኞችም ጮቤ ያስረግጣቸዋል።
ዛሬ ትግሬውን ነጥሎ በማውደም ኢትዮጵያዊነት ያረበበበትን አንድ አስኳል ከጥቅም ውጭ ማድረግና ማውደም የቻለ ኃይል፣ ነገና ከነገ ወዲያ ደግሞ ሌላኛውን የኢትዮጵያ አስኳል አማራውን ለብቻው ያለ አጋር ነጥሎ ለመምታት ትልቅ የቤት-ሥራው  ተቃለለለት ማለት ነው።
አሁን የኢትዮጵያ ቀኝ እጅና መከታ የሆነውን ትግራይን ሕዝብ ለማውደም የሄድንበት የጥፋትና የጠላትነት ርቀት፣ በዚሁ ሳቢያ ከሁሉም ዘርና ወገን ያረገፍነው ወጣት ወገናችን፣ ያወደምነው ሀብትና ንብረት፣ የከሰከስነው አንጡረ ሀብት፣ የዘራነው ጥላቻና የመለያየት ቁርሾ ሁሉ ባጠቃላይ ሲታይ እጅግ ልብ ሰባሪ ነው።
አንድ ጉልበተኛ የኢትዮጵያ ጠላት ሀገራችንን ሊወርር ቢመጣ 20 እና 30 ዓመት ተዋግቶ ለማድረስ የሚፈልገውን ውድመት ነው በዚህ አጭር ጊዜ በራሳችን ላይ ያደረስነው። የምናደርሰውም። ኢትዮጵያን ለማዳን ወገንን እየገደሉ አይደለም መፍትሄው። ኢትዮጵያን ለማሳደግ ወገንን ከወገን እያፋጁ አይደለም መንገዱ።
ሥራዬ ብለን የያዝነው አንድ አይንን እየወጉ ሌላኛውን አይን ለማዳን መሞከርን ነው። የያዝነው አንድ እጅን እየቆረጡ ሌላኛውን እጅ ለማጠንከር ማለምን ነው። የተያያዝነው ሳንባን ቆርጠው እያወጡ፣ ልብን ለመደገፍ የመሞከር ያህል የሚቆጠር የሞኝ ሥራን ነው።
የቱንም ያህል ወገንን በማውደምና በመቆራረጥ ሥራችን ጀግንነትና ጀብደኝነት ቢሰማንም፣ የመጨረሻ ውጤቱ ግን የሀገር መራቆት ነው። የወገን ሞት ነው። የትውልድ ክስረት ነው።
እየሠራን ያለነው ጀብዱና እየፈፀምን ያለው ተጋድሎ በጥልቅ ሲታይ ለሀገራችን በምንም መልኩ የሚበጅ አይደለም። እንወዳታለን የምንላትን ሀገር ለውጭና ለሀገርውስጥ ጠላቶቿ አሳስተን አውድመን ጉልበት አሳጥተን የማስረከብ ሥራን ነው።
ባጠቃላይ አነጋገር (መረረንም ጣፈጠንም)፦ አሁን በሀገር ስም እየሠራን ያለነው ሥራ፣ ጠላት ሲመኘው የኖረውን ራሳችንን የማውደምና የማዳከም የቤትሥራ ነው።
በሌላ በኩል ግፍ የሚባልም ነገር አለ። ብርቃችንም አይደለምና በሚገባ እናውቀዋለን። ብዙዎቻችን ግፍን እንቃወማለን። ግን የግፍ ተባባሪዎችና አስፈፃሚዎችም ሆነን ደግሞ እንገኛለን። በዚህም የተነሳ ተረኛ ግፍን ማስተናገድ እንጂ፣ ግፍን ከምድራችን ማስቀረት እንቢ ያለን ሕዝቦች ሆነናል።
በበኩሌ ትናንትም ሆነ ዛሬ የአማራን ሕዝብ ነጥሎ፣ የጎረቤት ሀገር ሠራዊት ሳይቀር ሁሉም ባንድ ላይ ተባብሮ ቢዘምትበት፣ መንግሥት ተብዬው በአውሮፕላን ቦምብ ቢጨረግደው፣ የአማራ ሕዝብ የሚተዳደርበት ባጀት ቢቋረጥበት፣ ባንኩ፣ ስልኩ፣ መብራቱ፣ መድኃኒቱና እህሉ ሳይቀር ቢዘጋበት፣ ..
አሊያም የአማራ ሕዝብ ከመንግሥታዊ ከለላና ሽፋን ቢገለል፣ ይበጀኛል ያለው ድርጅት አሸባሪ ተብሎ ቢሳደድ፣ ልጆቹ በየገቡበት እንደጠላት ቢለቀሙና ቢጋዙ፣ ስማቸውና ክብራቸው ቢገፈፍ፣ ሀብት-ንብረታቸው ቢጠፋ፣ ከሰውነት በታች የወረደ ጥላቻ ቢለጠፍባቸው..
በምሬት የምቃወመውንና የምንጨረጨረውን (እና ስቃወም የኖርኩትን) ያህል: –
አሁንም በትግራይ ሕዝብ ላይ እየተደረገበት ያሉት ነገሮች እነዚሁ ስለሆኑ አምርሬ እቃወማለሁ!!
ትግሬ አይደለሁም። መሆንም አይጠበቅብኝም። ኢትዮጵያዊ ነኝ። በኢትዮጵያዊነቴ የማምን ንጥር ያልኩ አማራ ነኝ። ነገር ግን በራሳችንም ሆነ በማንም ላይ ቢደረግ የማንወደውን ለምን በትግራይ ሕዝብ ላይ ለማድረግ ቆርጠን እንደተነሳን ሲበዛ ይገርመኛል።
ደጋግሜ እንደምናገረው፣ ወያኔዎቹን ከእኔ በላይ አምርሮ የተቸም ያብጠለጠለም የሚኖር አይመስለኝም። ነገር ግን በዚህ ደረጃ “የጋራ ጠላት” አድርጎ ሁሉም ተባብሮ በአንድ ብሔርና በአንድ ኢትዮጵያዊ ኃይል ላይ ከወገን እንዳልተፈጠረ የውጪ ጠላት ሲረባረብ ስመለከት እጅግ ተሸማቅቄያለሁ።
በግሌ ማንኛውንም ግፍ የማልቀበለውን ያህል፣ በትግራይ ላይ የዘነበው ጥላቻና መከራም ያስደነግጠኛል። ያንጨረጭረኛል። የቀደመ ሥራቸውና እንከናቸው (ከሌሎችም ጋር የፈፀሙት ቢሆን) እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እንደ ሕዝብ ግን ለተረኛው ገዢ አንንበረክክም በማለት ያሳዩት ቁርጠኝነት፣ አልበገርም ባይነታቸው ይበልጥ እንዳከብራቸው አድርጎኛል።
ብናውቅበት ኖሮ አሁን ከኛ ጋር የሚጋደለውና እያወደምነው ያለነው ሕዝብ ላገራችን ተጨማሪ ኃይልና አለኝታ በሆነ ነበር! ነገር ግን ዛሬ በስክነት ለመነጋገርና ለማስተዋል ጀብዱ፣ ቂምበቀልና ጥላቻ አናውዞናልና፣ ስለ ሠላም፣ ስለ ወንድማማችነት፣ ስለ አንድ ሀገር ልጅነት ስለ እርቅና ይቅርታ የምናውቃቸው ሁሉ ነገሮች ጠፍተውናል።
ይህ የጥላቻ አዙሪት በመጨረሻ የሚያወድመው ሀገርን ነው። ቤተሰብን ነው። ነፍሳቸው ከአፈር የተቀላቀሉ ለሀገሪቱ ስንት ነገር ሊሠሩ የሚችሉ በዚህኛው ወይም በዚያኛው ጎራ የተሰለፉ ወጣት ዜጎቻችንን ነው የሚነጥቀን።
ይህን ሁሉ ማሰብ አንገት ያስደፋል። መጨረሻችንን ያሳምርልን ማለትም ትልቅ ምርቃት ነው። ይሄን ጦርነት የመጨረሻችን ያድርግልን ማለትም ተዓምርን እንደመመኘት ነው።
አንድዬ ይሁነን።
Filed in: Amharic