>

"ታሥራለች…  ህዝቡ ገቢ ተደርጋለች…  ብልፅግና-ኢህአዴግ ....!!!" (ዘመድኩን በቀለ)

“ታሥራለች…  ህዝቡ
ገቢ ተደርጋለች…  ብልፅግና-ኢህአዴግ ….!!!”
ዘመድኩን በቀለ

*…. እስክንድር ነጋ የታከለ ኡማ የግል እስረኛ ነው!
• ታምራት ነገራ የሽመልስ አብዲሳ የግል እስረኛ ነው!
• መዓዛ መሀመድ የማን የግል እስረኛ ትሆን???
… ለህዝቡ የታሠረችው… ለአገዛዙ ደግሞ ገቢ የተደረገችው በብሔር ዐማራ ናት። በሙያ ጋዜጠኛ። ትናንት የጋዜጠኛ ታምራት ነገራን ዜና እስር በገለፅንበት አንቀጽ ታሜ ብሔሩ ኦሮሞ ነው እንዳልነው ማለት ነው። ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ኦሮሞነቱና ፕሮቴስታንት መሆኑ በኦሮሙማው መንግሥት ከመታሰር አላዳነውም። የወለጋ ኦሮሞ መሆኑ አንድ ወንጀል ሆኖ የታምራት ነገራን ወንጀል ከፍ የሚያደርግበት ደግሞ ሻአቢያን መንቀፉ፣ ህወሓትን አምርሮ መጥላቱ፣ የክልል፣ የብሔርና የዘር ፖለቲካው በሕግ ይፍረስ ማለቱ በዚያ ላይ ንፁሕ ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ፣ ያውም የእምዬ ምኒሊክ ወዳጅ መሆኑ ነው። በሾተላዩ የዋለልኝ የልጅ ልጆች፣ በህወሓት ወያኔ አልጋ ወራሾች ዘንድ ፕሮቴስታንትና እስላም፣ ኦሮሞ መሆንህ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ካልክ አያድንህም። እናም ትንታጉ ታምራት ነገራ ታሰረ፣ የደረሰበትም አልታወቀም ባልነው መሠረት ትንታጓ ጋዜጠኛ መዓዛ መሀመድም የታምራት ነገራ ዕጣ ፈንታ ዛሬ ደርሷታል መባልን ሰምተናል።
…መዐዛ መሀመድ ጋዜጠኛ እና መምህርት ናት። ያውም ደፋር፣ ቆራጥ፣ ያመነችበትን ሃሳብ እስከጥግ ድረስ የምትወስድ ጀግኒት ጋዜጠኛ እና መምህርት ናት። የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከተሰየመ ጊዜ ጀምሮ ከዚያም በፊት በህወሓት ኢህአዴግ ላይ ታደርግ የነበረውን ትግል ሳታቋርጥ ገፍታ የቀጠለች ጀግኒት ናት። ፅናትን፣ ትእግስትን፣ አስሬ ለክቶ አንዴ መቁረጥን፣ ደግሞም አደበተ ርትዕት ሆና ድፍረትን፣ መከራ ቻይነትን፣ የታደለች ኢትዮጵያዊት ሴት ናት። የቤተሰብ መበተንን፣ መዋከብን እስከ ሞት ድረስ የሚያደርሰውን የህይወት ማጣትን ጭምር በሚጠይቀው የሃገሬ የጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ እንደዘመኑ ሴቶች ብልጭልጩ ዓለም ሳይስባት ሙያዋን ለህዝብ ጥቅም ያዋለችም ጋዜጠኛ ናት።
…መዐዛ መሐመድ በወለጋ ለታፈኑ የዐማራ ልጆች ብቻዋን ከጥቂት ጓደኞቿ ጋር ሰልፍ ለመውጣት እስከመጠየቅ የደረሰች፣ የልጆቻቸውን ዱካ አጥተው በሃዘን በትካዜ የተቆራመዱ የዐማራ እናቶችን ገጠር ድረስ በመሄድ ቤተሰቡን በማጽናት የተንከራተተች፣  የአዝማሪ ሃጫሉን ሞት ተከትሎ በምሥራቅ ኦሮሚያ በዐማሮች ላይ የደረሰውን የዘር ማጥፋት ፍጅት ከቦታው ድረስ  በመሄድ በድፍረት የዘገበች። በባሌ፣ በሃረርጌ፣ በአሩሲ፣ ሻሸመኔ፣ በዝዋይ፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን ያጽናናች። መተከል፣ ደረስ የሄደች፣ ማይካድራ የተገኘች፣ አጣዬ ቆሬ ሜዳ ሰሜን ሸዋን ያካለለች፣ ስደተኞቹ አሉበት ቦተባለ ሥፍራ ሁሉ ድረስ እየሄደች እንደ ወገን አይዞኝ፣ እንደ እናትነት፣ እንደ ሴትነት ደግሞ አብራ እያለቀሰች፣ መንግሥትን በመገሰጽ፣ ህዝብን በማስተባበር በመላ ኢትዮጵያ በመዟዟር ሙያዊ ግዴታዋን ለህዝብ ጥቅም ስትፈጽም የነበረች ጀግኒት ጋዜጠኛ እና መምህርት ናት።
…የግንቦት ሰባት አንደኛው ክንፍ በሆነው በዓባይ ሚድያ ላይ ትሠራ በነበረ ወቅት ከሙያዊ ሥነ መግባር ውጪ የሚዲያው ባለቤቶች መንግሥትን የሚተች ነገር እንዳታንጸባርቅ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣትም አሻፈረኝ በማለት በአቋሟ በመቀጠሏ ከሚዲያው እንድትሰናበት አስድርጓታል። ብርቱዋ መዓዛ ወዲያው ነበር ከገዛደኞቿ ጋር “ሮሀ” የሚባል ሚድያ ወደ ማቋቋም የገባችው። ሃሳቧን በፌስቡክ በመግለጿና፣ በዚህ ጦርነት “ዐማራው ሆን ተብሎ እንዲወድም ተደርጓል” በማለቷ “የኢዜማ፣ የኦነግ፣ እና የብልጽግና ካድሬዎች ባደረጉባት የትታሰርልን ዘመቻ ምክንያት “ሀገር ወዳዱ፣ ኢትዮጵያን አሻጋሪው” የዐቢይ አሕመድ መንግሥት የመለስ ዜናዊን ሌጋሲ ለማስቀጠል ሲል በዛሬው ዕለት ጋዜጠኛ መዓዛ መሀመድን ወደ ዘብጥያ ወርውሯታል። ዐቢይ አሕመድ ከሚያወድሱት በቀር የሚተቹትን ወደ ወኅኒ በመወርወር ላይ ነው። ላሜ ቦራ ዳያስፖራውም ዐቢይ ከህወሓት ጋር የሚዋጋለት ስለሚመስለው ጮጋ ብሏል። በዚህ መሠረት የአቦይ መለስ ዜናዊ የቁርጥ ልጅ ኦቦ ዶክቶር ዐቢይ ዐሕመድ …
• ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ~ ዐማራ ኢትዮጵያዊ የሆነ
• ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ~ ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ የሆነ
• ጋዜጠኛ መዓዛ መሀመድ ~ዐማራ ኢትዮጵያዊ የሆነች
ጋዜጠኞችን ሰብስቦ ወደ ዘብጥያ ወርውሯል። በኢትዮጵያ ከመዓዛ በኋላ የዐማራን ሞት፣ ስደት፣ መፈናቀል የሚናገር ላይታይ ነው ማለት ነው። የታገቱትና መድረሻቸው የጠፋው የወለጋ ደምቢዶሎው የዐማራ ተማሪዎችን ጉዳይ አንሥቶ የሚጠይቅ ደፋር ላይኖር ነው ማለት ነው?
• እስክንድር ነጋ የታከለ ኡማ የግል እስረኛ ነው።
• ታምራት ነገራ የሽመልስ አብዲሳ የግል እስረኛ ነው።
• መዓዛ መሀመድ የማን የግል እስረኛ ትሆን?
… ማነህ ባለ ሣምንት?  ገቢ የምትሆን በብልጽግና መንግሥት? ገምቱ እስቲ…
Filed in: Amharic