>
5:26 pm - Wednesday September 17, 0442

የሂውማን ራይትስ ዎች የሀሰት ሪፖርት ሲጋለጥ...!!! (ውብሸት ሙላት)

የሂውማን ራይትስ ዎች የሀሰት ሪፖርት ሲጋለጥ…!!!

ውብሸት ሙላት


ሂውማን ራይትስ ዎች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትናንት ታህሳስ 07/2014 በወልቃይት ጠገዴ አካባቢ በጋራ ሰራነው ያሉትን ሪፖርት አቅርበዋል። ሪፖርቱ የወልቃይት ጠገዴ ሲቲት ሁመራ ዞን ሦስት ከተሞች በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ተፈፀመ ያሉትን የሰብዓዊ መብት ሪፖርት የሚጠቅስ ነው። ሪፖርቱን የአይን እማኝ ያሏቸውንና ከእስር ቤት አመለጡ ያሏቸውን ሰዎች በስልክ አነጋግረው እና ከሳተላይት የተወሰደ ያሉትን ምስል ዋቢ አድርገው የተሰራ እንደሆነ ይገልፃል።

የሪፖርቱ ይዘት ጠቅለል ብሎ ሲታይ የትግራይ ተወላጆች ከሁመራ፣ ራውያን እና አደባይ ከተሰኙ የዞኑ ከተሞች ተጭነው ወደማዕከላዊ ትግራይ እንደተወሰዱ፣ ባልና ሚስት ተለያይቶ ቤተሰብ እንዲበተን መደረጉን፣ በእስር ቤት ውስጥ ሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈፀም፣ የትግራይ ተወላጆች መገደላቸውንና ጥቃት እንደደረሰባቸው በማተት በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ ጫና ሊያርፍ እንደሚገባ የሚወተውት ነው።

የሪፖርቱ ገመና ሲጋለጥ…

ሁለቱ ድርጅቶች በጥምረት ያወጡት ሪፖርት የመረጃ አሰባሰብ ሥነ-ዘዴው በራሱ ተዓሚነትን የሚያሳጣ ነው፡፡ በሪፖርቱ ላይ የተካተቱ መረጃዎች በሙሉ የተሰበሰቡት በስልክ እንደሆነ በሪፖርቱ ላይ ተመላክቷል፡፡ በሪፖርቱ ላይ መረዳት እንደሚቻለው ‹‹ወደ ትግራይ ከሄዱት››፣ ‹‹ወደ ሱዳን ሸሹ›› ከሚሏቸውና ወልቃይት ጠገዴ ውስጥ ካሉትና ‹‹የአይን እማኝ›› ናቸው ከተባሉት ጋር የስልክ ምልልስ በማድረግ የተጠናቀረ ሪፖርት ነው። አብዛኛው የወልቃይት ጠገዴ በተለይም በሪፖርቱ የተጠቀሱት ሁመራ፣ ራውያን እና አደባይ አካባቢዎች ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ካለው የፀጥታ ችግር አንፃር ስልክ የሚሰራባቸው አይደሉም።

መረጃው የተሰበሰበው ወደ ትግራይ ተወስደዋል ከተባሉት ጋር ከሆነም፣ ሁለቱ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ውስጥ የስልክ አገልግሎት ተቋረጠ በመሆኑ ግንኙነት ማድረግ እንደማይቻል እርግጥ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ሂውማን ራይትስ ዎች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል በትግራይ የስልክና መሰል አገልግሎቶች ሊከፈቱ ይገባል በሚል ተደጋጋሚ መግለጫ ያወጡ በመሆኑ የሚታወስ ነው። ይህን መሰል የመግለጫ ይዘቶችን ያስተጋቡት ሁለቱ ድርጅቶች አሁን ላይ መረጃ በስልክ ሰበሰብን በሚል ሪፖርት ማውጣታቸው ተዓማኒነቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል፡፡

በሌላ በኩል ወደ ሱዳን ተሻገሩ ካሉት ጋር የስልክ ግንኙት ተደርጎ መረጃው የተሰበሰበ ከሆነ፣ ይህ መረጃ በስደተኛ ስም ከተቀመጠው፣ የጥቅምት 30/2013 የማይካድራ ጭፍጨፋን ከትግራይ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጋር ሆኖ ከመራው ‹ሳምሪ› ከተሰኘው ኢ-መደበኛ አደረጃጀት ላይ እንደሆነ እናምናለን፡፡

ከዓለማቀፍ ሕግ በሚቃረን መልኩ በሱዳን የስደተኛ ካምፖች ውስጥ አሸባሪው ህወሓት ንጹሃን የአማራ ተወላጆችን ለመጨፍጨፍ የተጠቀመባቸው የትግራይ ልዩ ኃይል፣ የሚሊሻና የኢ-መደበኛ አደረጃጀት አባላት በስደተኛ ስም እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በሱዳን በኩል ስደተኛ ካምፕ ያሉትን እነዚህን ኃይሎች የሸብር ስልጠና በመስጠት በአማራ ክልል በቋራ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ በኩል በንጹሃን፣ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እና በመሰረተ ልማት ላይ ጥቃት እንዲከፍቱ ስምሪት ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

የስደተኞች ካፕም ውስጥ ገብተው መታወቂያ (Refugee ID Card) የተሰጣቸው ነገር ግን አሸባሪው ህወሓት ለጥፋት ተልዕኮ ወደኢትዮጵያ አስርጎ አስገብቷቸው በውጊያ የተማረኩ ምርኮኞች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ በተመሳሳይ ትግራይ ውስጥ ተፈናቃይ ካምፕ የነበሩ ወጣቶች በጦርነቱ ተሳታፊ መሆናቸው በተደጋጋሚ ተጋልጧል። በስደተኛና ተፈናቃይ ስም ከእነዚህ ኃይሎች ለሰብዓዊ መብት ተቋማቱ የአሸባሪው ህወሓት ሰዎች መልምለው በመስጠትም ሆነ በስልክ በማገናኘት ከአሸባሪው ቡድን ትዕዛዝና ተፅዕኖ ውጭ የሚሰራ ሊሆን እንደማይችል ግልፅ ነው።

በሪፖርቱ የመረጃ ምንጭነት የተጠቀሱት ግለሰቦች በሙሉ በስልክ ያነጋገሯቸው ቢሆኑም የአይን እማኝ እያሉ ተጠቅሰዋል። ከአሸባሪው ህወሓት የተለመደ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ፣ ከአሁን ቀደም ሲለቀቁ ከከረሙት የሐሰት መረጃዎች፣ በሪፖርቱ በየመስመሩ ከሚጣረሱት እውነታዎች አንፃር በስልክ አነጋገርናቸው ያሏቸው ሰዎች የአይን እማኝ እንዳልሆኑ መገመት አይከብድም። በሪፖርቱ ላይ በቁጥር የሚጠቅሷቸውን ሰዎች ‹የአይን እማኝ› ብለው የተጠቀሱትን ስለማነጋገራቸው እርግጠኛ ሆነው አይነግሩንም።

በሁለቱ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ጥምረት በወጣው ሪፖርት ላይ 31 የአይን እማኞችን አነጋገርን ይበሉ እንጅ፣ ሪፖርቱ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች በጥንቃቄ ሲቆጠሩ ከ70 በላይ የሚሆኑ ናቸው። ከዚህ የእውነታ መጣረስ በተጨማሪ በስልክ አነጋገርናቸው የሚሏቸው ሰዎች ከአካባቢው የተፈናቀሉ ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ የሚያስችል አሳማኝ ማስረጃ በሪፖርቱ ላይ አልተካተተም።

የሁለቱ ድርጅቶች ጥምር ሪፖርት በስልክ ያነጋገራቸውን ሰዎች በምንጭነት ከመጥቀሱ በተጨማሪ የሳተላይት ምስልን ትንተናን መውሰዱን ይገልፃል። ከዚህም አንደኛው የተወሰኑ መኪኖችን ቁጥር እየጠቀሰ ከአንዱ የአካባቢው ክፍል ወደሌላኛው መንቀሳቀሱን ያትታል። ይህን ጉዳዩን ተፈፀመ የሚሉት በሕዳር ወር አጋማሽ ነው። በመሰረቱ አካባቢው ሰሊጥን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎችን አምራች በመሆኑ በተጠቀሰው ጊዜ ከአካባቢው አንድ ክፍል ወደሌላኛው ክፍል ብቻ ሳይሆን ከአማራ ክልል ብሎም ከኢትዮጵያ ክፍሎች ሰብል ለመሰብሰብ በርካታ ቁጥር ያለው ሰራተኛ የሚንቀሳቀስበት፣ ሰሊጥና ሌሎች ሰብሎችን ከአንዱ ክፍል ወደሌላኛው የሚያጓጉዙባቸው የጭነት መኪኖች፣ እንዲሁም አሁን ባለው ‹‹ዘመቻ ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት›› ምክንያት የፀጥታ ኃይሎች ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ሁኔታ አለ፡፡ በመሆኑም አካባቢው በሪፖርቱ የተጠቀሱት ብቻ ሳይሆኑ በርካታ መኪናዎች ሲንቀሳቀሱ የሚውሉበት በመሆኑ የሳተላይት ምስል ተብሎ የተጠቀሰው ሪፖርቱን ታማኝ ለማድረግ የተኼደበት ርቀት እንጅ ተጨባጭ ማስረጃ ሊሆን አይችልም።

በተሰመሳሳይ አንደኛ ደረጃ ጥቁር አስፓልት የሆነውን የአደባይ ከተማ አስፓልት ጨምሮ መንገዶች ላይ የተለየ ምልክትና ፍርስራሽ እንዳለ ለማስመሰል የተሄደበት ርቀት አካባቢውን ለማያውቁት ያወናብድ ካልሆነ በስተቀር ተጨባጭነት የሌለው ሪፖርት ነው።

የሁለቱ ተቋማት ሪፖርት በሌላ ምንጭነት የሚጠቅሰው OCHA የተባለው ድርጅት የራሱን ሪፖርት በራሱ የሚቃረን መረጃ አውጥቷል። ሪፖርቱ ይህን ድርጅት ጠቅሶ በወልቃይት ጠገዴ ይኖሩ የነበሩ 1.2 ሚሊዮን የትግራይ ተወላጆች መፈናቀላቸውን ያገልፃል። ይሁንና OCHA እ.አ.አ. በ 17/08/ 2017፣ ‹‹ETHIOPIA TIGRAY REGION: KEY AREAS AND POPULATION›› በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት በወልቃይትና አካባቢው የሚኖረውን አጠቃላይ ሕዝብ ቁጥር 467,890 ብሎ መረጃ አቅርቧል። የሁለቱ ድርጅት ሪፖርት በሐሰት የተቀነባበረ መሆኑን የሚያሳየው OCHA ምንጭ አድርጎ 1.2 ሚሊዮን ሕዝብ ተፈናቀለ ሲል OCHA አጠቃላይ የአካባቢውን ሕዝብ፣ በአራት ዓመት ልዩነት ሦስት እጥፍ አሳድጎታል፡፡

በአካባቢው ነባር ነዋሪ የሆነውን የአማራ ተወላጅ የትግራይ ተወላጅ እንደሆኑ አድርጎ መረጃ በማዛባት በአካባቢው 1.2 ሚሊየን የትግራይ ተወላጅ እንደተፈናቀለ ሪፖርት አውጥቷል፡፡ ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ይህን የተዛባ መረጃ በምንጭነት መጠቀማቸው ሪፖርቱ በሀቅ ላይ ያልተመሰረተ ያደርገዋል፡፡ በሌላ በኩል አሸባሪው ህወሓት በአገዛዝ ዘመኑ የአካባቢው ሕዝብ በአጠቃላይ 420,000 ሺህ መሆኑን የሚገልፅ ማስረጃ ከሁመራ ማዘጋጃ ቤት ተገንቷል። ይህ በአካባቢው ተፈናቀለ የሚባለው ሦስት እጥፍ የሕዝብ ብዛት የፈጠራ ድረሰት ስለመሆኑ ያስረግጣል፡፡

የሁለቱ ድርጅቶች ሪፖርት በተደጋጋሚ ፋኖ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅሟል በሚል ይገልፃል። ይሁንና አካባቢው መደበኛ አደረጃጀት ያላቸው የአማራ ክልልና የፌደራል ፀጥታ ኃይሎች ያሉበትና የዜጎችን ደሕንነት የሚጠብቁበት ከመሆኑም በተጨማሪ በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ፋኖ የለም፡፡ ይህም ፋኖ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅሟል ተብሎ የቀረበበት ሆን ተብሎ በሐሰት የቀረበ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ሪፖርቱ ፋኖን የጦር መሳሪያ የታጠቀ መሆኑን ከገለፀ በኋላ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ተፈፀመ የሚለው በስለታማ መሳርያና በዱላ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ፋኖ በ‹ዘመቻ ለኀብረ-ብሄራዊ አንድነት› የህልውና ዘመቻ በተለያዩ ግንባሮች በተሰለፈበት ሁኔታ የፖሊስና የሚሊሻን ሚና ወስዶ የአካባቢን ፀጥታ የሚያስከብር አድርጎ የተወሰደበት፣ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ የሚፈልጉ አካላት ፍላጎትና ሌሎች አካላትን ለማወናበድ የተሰራ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

በሪፖርቱ አንደኛው ክፍል የአይን እማኝ ሆኖ የቀረ ግለሰብ ሦስት ሆነው ሲሄዱ እንደተያዘ ጠቅሶ፣ ጓደኛውን እንደገደሉት ይናገራል። እሱ እንዴት እንዳመለጠ እንኳን አሳማኝ አይደለም። ይህ የሪፖርቱ ክፍል ማሕበራዊ ሚዲያ ተሳታፊዎች የአሸባሪው ቡድንና አጋዥ ተቋማቱ የሚያዘጋጁትን ሐሰት ለመግለፅ “አባቴን ገደሉት። ከዛም እኔን ገድለውኝ ሄዱ” በሚል የሐሰት ሪፖርቶቻቸውን ለማጋለጥ የሚቀባበሉትን ቀልድ መሰል እውነት የሚያስታውስ ነው።

በሁለቱ ድርጅቶች ሪፖርት መሰረት 200 ያህል የትግራይ ተወላጆች ሦስት በአራት በሆነ ክፍል ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ይጠቅሳል። የተጠቀሰው የክፍል ስፋት ለ200 ሰዎች ቀርቶ ለ20 ሰው የሚበቃ እንዳልሆነ ይታወቃል። እስር ውስጥ ያሉ ሰዎች ከታሰሩበት ሐምሌ ጀምሮ ለሦስትና አራት ወራት ምግብ እንዳልቀረበላቸው፣ ሽንት ቤት መጠቀም እንደማይችሉ ተደርጎ የቀረበውም ውግንናው ለእውነት ብቻ የሆነ ማንም ሰው ይህ መረጃ፣ በሐሰት የተቀነባበረ እንጅ እውነት ሊሆን የማይችል በቀላሉ ይረዳዋል፡፡ በሌላ በኩል እስር ቤቶቹን ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸው አድርገው ካቀረቡ በኋላ ሪፖርቱን ታማኝ ለማድረግ ግን ከእስር ያመለጡ ብለው በእማኝነት አቅርበዋል።

በተመሳሳይ ለሪፖርቱ እማኝ የተባለ አንድ አርሶ አደር፣ ከ30 እስከ 40 የሚሆኑ የታጠቁ ሰዎች ጎረቤቱ ቤት ገብተው ጎረቤቱን በመጥረቢያ፣ በፈራድና በዱላ እንደደበደቡት ይናገራል። ይህ ሰው ‹ተደብቄ ነው ›እያለ፣ በፍርሃት ስሜት ሆኖም የሰዎቹን ቁጥር ብቻ ሳይሆን፣ የራሱ ቤት ሆኖ ጎረቤቱ ቤት ውስጥ ገብተው ‹በምን አይነት የስለት መሳርያ እንደሚመቱት አይቻለሁ› ብሎ ነገረን ብለው ለማሳመን መጣራቸው አይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ እንደማለት ነው።

በተጨማሪም ከ30 እስከ 40 የሆኑ ታጣቂዎች መሳርያ ይዘው ጎረቤቱን በጦር መሳርያ ሳይሆን በስለት መሳርያ አጠቁት ከሚለው ቀልድ ባሻገር፣ እነዚህ ሁሉ ሰዎች የደበደቡትን ሰው እየጎተቱ እንደወሰዱትም እማኝ የተባለው ነግሮናል ብለው በሪፖርታቸው ላይ ያቀርቡልናል።

በሪፖርቱ እማኝ ከተባለው መካከል አንደኛው ዘመዱን ለመጨረሻ ጊዜ የደወለችለት በመኪና እየጫኗት እንደሆነ በሪፖርቱ ላይ ተገልፆል። በአንድ በኩል ሪፖርቱ ሁኔታውን እጅግ አስፈሪ፣ አንድን ሰው 30 እና 40 ታጣቂ የከበበው አድርጎ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዘመዱ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈፅሙት ከበዋትና በመኪና እየጫኗት ተበደልኩ የምትለውን በስልክ ዘርዝራ የምትነግርበት አጋጣሚ ሊኖር አይችልም። ተፈናቀሉ የተባሉትን ሰዎች አፈናቃይ የተባሉት በመኪና ጭነው ማዕከላዊ ትግራይ እንዳደረሱ ተደርጎ የቀረበው የሪፖርቱ ክፍልም አካባቢውንና በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ግምት ውስጥ ካለማስገባት የመጣ ተራ ቅጥፈት ያደርገዋል።

የሪፖርቱ አላማ ምንድን ነው?

1) ከቀደመው የሐሰት ሪፖርት የቀጠለ ነው፤

በሰብዓዊ መብት ስም አሸባሪውን ህወሓት ለማዳን ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል። በተለይ ሂውማን ራይትስ ዎች የተባለው ድርጅት አሸባሪው ቡድን የፈፀማቸውን በርካታ ወንጀሎች ወደጎን በማለት የአሸባሪውን የሐሰት መረጃ ይዞ ሲያቀርብ መቆየቱ የሚታወስ ነው። በተመሳሳይ ሌሎች ድርጅቶች ከአሁንም ቀደም መሰል የሐሰት ሪፖርት ሲያወጡ ቆይተዋል። ይሁንና ሪፖርቶቹ በሐሰት መረጃ የተሞሉ በመሆናቸው በእነዚህ ድርጅቶች የታሰበው ዓላማ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ቀደም ሲል ሲወጡ በነበሩ የሐሰት ሪፖርቶች መሰረት አድርጎ በአሜሪካ መንግስት ሪዞሉሽን ሊጠቃለሉ የነበሩ ጭብጦች እንዲሰረዙ መደረጉ ይታወቃል።

ከወራት በፊት ቢ.ቢ.ሲ. በወልቃይት ጠገዴ አካባቢ ተመሳሳይ የሐሰት ሪፖርት መስራቱ የሚታወቅ ነው። ጣቢያው አንድ የሁመራ ሆስፒታል ባለሙያ የነበረና ከማይካድራ ጨፍጫፊዎች ጋር የሸሸን የአሸባሪው ቡድን ደጋፊ በማነጋገር ብቻ የሐሰት ሪፖርት ማቅረቡ ይታወቃል። እማኝ የተባለው ይህ ግለሰብ የትግራይ ተወላጆች ለቀናት ተከዜ ወንዝ ላይ እንደተጣሉ አድርጎ በማቅረብ፣ ነገር ግን ለቀናት ውሃ ውስጥ የቆየን አስከሬን የእጁ ንቅሳት ላይ የትግሬ ስም ነው በሚል በማስረጃነት ለማቅረብ ሲሞክር ተስተውሏል። የሂውማን ራይትስ ዎች እና የአምነስቲ የትናንት ሪፖርትም ከአሁን ቀደም ሚዲያዎች በተናጠል ያቀረቡትን የተቀነባበረ የሐሰት ሪፖርት በሰብዓዊ መብት ሪፖርት ለማሳደግ የጣረ ነው።

2) ከአሸባሪው ቡድን ጋር ቅርርብ ካላቸው ግለሰቦች ጋር የተገናኘ ነው፤

Laetitia Bader የአፍሪካ ቀንድ ሂውማን ራይትስ ዎች ዳይሬክተር ስትሆን፤ ግለሰቧ ሱዳን ድረስ በመሄድ ማይካድራ ላይ ጭፍጨፋ ፈፅመው በሱዳን የመሸጉ ወንጀለኞችን አግኝታ እንደማስረጃ በማድረግ የኢትዮጵያን መንግሥት ስትወቅስ የቆየች ነች። ከአሸባሪው ቡድን አክቲቪስቶች በባሰ የአሸባሪውን መረጃ መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያን መንግሥት ስትወቅስ የምትውል ግለሰብ በመሆኗ፣ ከአቋሟ በመነሳት የአሸባሪው ቡድን የሐሰት መረጃን እንደ እውነት ወስዳ በተመሳሳይ ዓላማ እየሰራች ስለመሆኑ መጠራጠር አይቻልም። በተመሳሳይ የሂውማን ራይትስ ዎች ዋና ዳይሬክተር የሆነው ኬኔት ሮት እያንዳንዱን የኢትዮጵያ መንግስት እንቅስቃሴ በአሸባሪው ህወሓት የተሳሳተ መረጃና አተያይ አንፃር በመተቸት የሚታወቅ መሆኑ ሪፖርቱ የአሸባሪውን ህወሓት የፖለቲካ ፍላጎት ለማስጠበቅ የወጣ ለመሆኑ ያመላክታል።

3) አሸባሪው ቡድን ጫና ውስጥ ሲገባ ትኩረት ለመቀነስ የወጣ ነው፤
በሰብዓዊ መብት ሪፖርት ስም የሚሰሩ የሐሰት ሪፖርቶች አሸባሪው ቡድን ጫና ውስጥ ሲገባ ተደጋግመው ተሰርተዋል። አሸባሪው ቡድን ቦታዎችን በጦር ወረራው ወደፊት ገፍቶ ወሳኝ የሚባሉ ከተሞችንና ቦታዎች ያዝኩ ሲል ስልጣን ለመያዝ አቅም እንዳለው በማስመሰል ሲያቀርቡ የሚስተዋሉት ተቋማት፣ በአንፃሩ የሽብር ቡድኑ ጫና ውስጥ ሲገባ በተደጋጋሚ የሐሰት ሪፖርት አውጥተው ለመታደግ ጥረዋል። በተመሳሳይ አሸባሪው ቡድን እየተመታ ባለበት በዚህ ወቅት የፈፀማቸው ውድመቶችና ጭፍጨፋዎች በይፋ እየታዩ ይገኛሉ። አሸባሪው ቡድን ጫና ውስጥ ከመግባቱም ባሻገር የፈፀማቸው በደሎችም እያጋለጡት መሆኑን የተረዱት አጋዥ ተቋማቱ ሽንፈትና ወንጀሉን ለመሸፋፈን የሐሰት ሪፖርት በማዘጋጀት ላይ ተጠምደዋል። በተለይም እንደ ሂውማን ራይትስ ዎች ያሉት የአሸባሪውን በርካታ ወንጀሎች እንዲሁ አልፈዋል። ይህኛውን የሐሰት ሪፖርት ለማቅረብ ሲሉ ለይምሰል ብቻ በርካታ ጊዜ የሆነውንና ዓለም ያወቀውን፣ አሸባሪ ቡድኑ በአማራ ክልል የፈፀመውን የቆቦ እና የጭና ጭፍጨፋ ለይምሰል አቅርበዋል።

4) ለሌሎች ጫናዎች ግብዓት እንዲሆን ታስቦ የተሰራ ነው፤

በሁለቱ ድርጅቶች ጥምረት በስልክ አነጋገርን በሚል እርስ በርሱ የሚጋጭና ታማኝነት የሌለው ሪፖርት የቀረበበት ዋነኛው ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ለሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጫናዎች ግብዓት እንዲሆን ታስቦበት የተሰራ ነው። ባለፉት ጊዜያት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሰደር ያለሙት የአውሮፓ ሕብረት እና የተመድ ስብሰባዎች ውጤታማ አልሆኑም። ለዛሬም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ የተቀጠረ ስብሰባ እንዳለ የሚታወቅ ነው። አሸባሪው ቡድን ከ50 በላይ ለሚሆኑ አገራት አደራድሩኝ ብሎ ልምና ጀምሯል። አሁን ደግሞ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የኢትዮጵያ ግዛት አካል ወደሆነው ወደ ትግራይ እንዳይገቡብኝ በማለት ላይ ይገኛል፡፡ ትናንት የወጣው የሁለቱ ድርጅቶች ሪፖርት ኢትዮጵያ ላይ ያለ አግባብ የሚደረገውን ጫና ታሳቢ በማድረግና ለእነዚህ ጫናዎች ግብዓት ለመሆን እንዳሰበ በመግቢያውም በማጠቃለያውም በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ ጫና እንዲደረግ መወትወቱ አላማውን ግልፅ ያደርገዋል።

Filed in: Amharic