>
5:13 pm - Wednesday April 18, 7691

ለቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግስቱ  ኃ/ማሪያም በፓርላማ ምህረት  ይደረግለት!! (መስፍን ተስፋዬ)

ለቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግስቱ
 ኃ/ማሪያም በፓርላማ ምህረት  ይደረግለት!!
መስፍን ተስፋዬ

…እርግጥ ነው በመንግስቱ ዘመን ብወለድም ስለመንግስቱ ብዙ የማውቀው ነገር የለም። ስለመንግስቱ ኃ/ማሪያም ግን በጆሮዬ ብዙ እየሠማው አድጌያለው። ከሠማሁዋቸው ታሪኮች..ካነበብኳቸው ድርሳናቶች በይበልጥ ደግሞ በዚህ የመረጃ ዘመን ኮ/ል መንግስቱ ያደረጉዋቸው ንግግሮች በኢንተርኔት የመረጃ መረብ የተለያዩ ዩቲዩቦች ከተለቀቁ ቪዲዮች ስለመንግስቱ የሠማሁትን፣ያነበብኩትን፣ያዳመጥኳቸውን ብሎም በአብዮታዊ ዲሞክራሲ በመንግስት የሥራ ኃላፊነት ከወሰድኳቸው ስልጠናዎች አንፃር እንዲሁም አሁን ሀገሪቱ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታዎች አንፃር ስለዚህ ሰው ሳልወድ በግድ እንዳስብ አድርጎኛል። በተለይም ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/አብይ ሀገር ጥለው እንዲኮበልሉና በሚኒስትሮቻችን መካከል መከፋፈልን ለመፍጠር የተሸረበው ከባድ ፓለቲካዊ ሴራና ዶ/ር አብይ በኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማሪያም ላይ የተሠራውን ሴራ ሲያጋልጡ ስለዚህ ሰው ሳልፈልገው ደጋግሜ እንዳስበው አድርጎኛል።  …መንግስቱ ኃ/ማሪያምን  እንደጭራቅ ስሎ ራሱን ቅዱስ ሲያደርግ የነበረው የወያኔ መንግስት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈፀመው የባንዳነት ዘመንና የሠራው ሴራን ማሠላሠል፣ማነፃፀርና ማብላላት ስጀምር በተለይም “የእኔን ሞት አታዩም ሞታችሁን ግን አያለው” በማለት ከ2 አስርታት ዓመታት በፊት የተናገረው ንግግር በተለይም በስልጣኑ ዘመን መጨረሻ ስለወያኔዎች የተናገራቸው ንግግሮችን ደጋግሜ ሳዳምጥ ከወያኔ አሁናዊ ወራዳ ተግባራትና ከፈፀማቸው ግፎችና ጭካኔዎች አንፃር የመንግስቱ የዋህነት ጎልቶ እንዲታየኝ አድርጓል። በእኔ አመለካከትና እምነት መንግስቱ ኃ/ማሪያም ፃድቅ ነው ብዬ ባላምንም ሠራቸው የተባሉት ስህተቶች ሁሉ ኢትዮጵያን በጭፍን ፍቅር ማፍቀሩ እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዛሬው ወያኔያዊ ሴራና ግፍ ለማዳን እንደነበር ሀቁን መገንዘብ አያዳግትም። ..ከሁሉም የሚገርመኝ ነገር ግን ስለወያኔ የተናገራቸው ንግግሮችን ሳዳምጣቸው ወያኔዎችንና ሴራቸውን ገና ከጥንስሱ ገብቶት እንደነበረ መረዳት ከማስቻሉም በላይ የትንቢት ቃል ይመስል ንግግሮቹ እውነት መሆናቸው የዚህን ሰው እውነተኛ ስብዕናና ማንነት እንድረዳው አድርጎኛል።
…የቀድሞው ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይህን ሰው ” ሰው በላው መንግስቱ ” ብለው ሲጠሩት በኢቲቪ የሠማው ቢሆንም ስለመንግስቱ ሁለት ምስክርነቶችን በተለያዩ ጊዜ መስጠታቸውን አስታውሳለው። አንደኛው መንግስቱ ጨካኝ ቢሆንም ለአፍሪካ ጥቁር ሕዝቦች ከቅኝ ግዛት መላቀቅ ያደረጋቸው አስተዋፅኦች እና መንግስቱ ሀገሩን ያልዘረፈ ልበ ንፁህ እና እጀንፁህ መሆኑን የመሠከሩበት አጋጣሚ ናቸው።
 መንግስቱ በብዙ ፓለቲካዊ ችግር ስትታመስ የነበረችን ሀገር በብዙ ቀውስ የመራ ጠንካራ መሪ እንደነበር ከሚያመላክቱ ተጨማሪ እውነታዎች የኢትዮ ሶማሌን ጦርነት በአይቀጡ ቅጣት ድል መንሳቱና መሀይምነትን ለማጥፋት መሠረተ ትምህርት በሚል ፕሮግራም አያሌ አያቶቻችን ማንበብና መፃፍ እንዲችሉ ማድረጉ በጉልህ የሚጠቀሱ በጎ ስራዎቹ ናቸው።
ኮ/ል መንግስቱ በአሜሪካ የስለላ ድርጅት የረቀቀ ሴራ የሚወዳት ሀገሩን ለቆ ዘመኑን በስደት ቢያሳልፍም የልቡን ገራገርነት ያየው አምላክ ጠላቶቹ ወያኔዎች ሲዋረዱና በሞትና በሕግ ቅጣት ሲማቅቁ በቁሙ እንዲያይና ከ30 ዓመታት በኋላ የልቡ እውነትን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲረዳለት
የሠማዩ አምላክ ዕድሜና ጤና ሰጥቶት በዙምባቤ ምድር ሆኖ ሁሉን እያየ ይገኛል።
…በምክንያት የሚያምንና በይቅርታ ታላቅነት የሚያምን ኢትዮጵያዊ ሁሉ መንግስቱ ኃ/ማሪያምን ከወያኔ በላይ ሊጠላው አይችልም። መንግስቱ በኢትዮጵያ ፍቅር ታውሮ ሲሆን ወያኔ ግን ቃላት በማይገልፁት ሴራ፣ዘረኝነት፣ተንኮል፣ባንዳነት ፣ ሌብነትና የስልጣን ጥም  ለባዳዎች ባሪያ ሆኖ ከመሆኑም በላይ በወያኔ ዘመን የተፈፀሙ በደሎች ከይቅርታ በላይ በሆነ ክፋት ራሱን አዘጋጅቶ ነው። ..እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንዲሉ የመንግስቱ ኃ/ማሪያም እውነት ስለወጣ ብሄራዊ የምህረት አዋጅ ታውጆለት የሽምግልና ዘመኑ በሚወዳት ኢትዮጵያ ሀገሩ እንዲሆን እንፍቀድለት።
Filed in: Amharic