>
5:29 pm - Sunday October 10, 1751

"ህዝባችን በአሸባሪው  ጉዳት የደረሰባቸውንና  የተፈናቀሉ ዜጎችን  ማቋቋም፤ ተቋማትን መገንባቱ ለነገ አይባልም...!!!" (ክርስቲያን ታደለ)

“ህዝባችን በአሸባሪው  ጉዳት የደረሰባቸውንና  የተፈናቀሉ ዜጎችን  ማቋቋም፤ ተቋማትን መገንባቱ ለነገ አይባልም…!!!”

ክርስቲያን ታደለ


“የፌዴራል መንግሥቱም ለሁለቱ ክልሎች ልዩ የመልሶ ማቋቋሚያ የድጎማ በጀት መመደብ አለበት…!!!”

መላው ኢትዮጵያውያን በአሸባሪው ሕወሓት ጉዳት የደረሰባቸውና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀደመ ሕይወታቸው ለመመለስና የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ርብርብ ማድረግ እንደሚኖርባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ጥሪ አቀረቡ፡፡ የፌዴራል መንግሥቱም ለሁለቱ ክልሎች ልዩ የመልሶ ማቋቋሚያ የድጎማ በጀት መመደብ እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

አቶ ክርስቲያን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአፋርና አማራ ክልሎች በፈጸመው ወረራ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ በርካታ ተቋማትም ወድመዋል፡፡ እነዚህ የተፈናቀሉና በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎችና የወደሙ ተቋማት መልሶ ለማቋቋምና ለመገንባት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲረባረቡ ጠይቀዋል።

የጦር ሜዳው አፋርና አማራ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች ይሁን እንጂ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር የሚካሄደው ጦርነት ኢትዮጵያን ለማዳን የሚደረግ ፍልሚያ ነው ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በፈጸመው ወረራ ተፈናቅለው በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ቀደመ ሕይወታቸው ለመመለስና በአሸባሪው የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ሂደት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ተሳትፎ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በሁሉም ግንባሮች ባደረጉት ያላሰለሰ ትግል ድሎች እየተመዘገቡ መሆኑን አመልክተው፤ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገራት የሚኖሩ ወገኖች ኢትዮጵያን አሸናፊ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይነትም መላው ኢትዮጵያውያንና የክልል መንግሥታት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለማቋቋምና የወደሙ ተቋማት በመገንባት ሂደት የባለሙያ ፣ ቁሳቁስና የተለያዩ ግብአቶችን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የፌዴራል መንግሥቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አፋርና አማራ ክልሎች ልዩ የመልሶ ማቋቋም የድጎማ በጀት መመደብ እንዳለበት የጠቆሙት አቶ ክርስቲያን፤ የመልሶ ማቋቋሚያ ልዩ ፈንድ በመክፈት በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓይነትም ሆነ በገንዘብ ድጋፍ የማሰባሰብ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ መንቀሳቀስ እንዳለበትም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ብትፈተንም በእርግጠኝነት በድል እንደምትሻገረው እስካሁን ያገኘናቸው ድሎች ያረጋግጡልናል ያሉት አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ የሽብር ቡድኑን ለአገር አንድነትና ለሕዝብም ደህንነት ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ላይ ማድረስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያውያን በመረዳዳትና ችግርን በጋራ የመሻገር እሴትን በመላበስ በአሸባሪው ሕወሓት ውድመትና ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ በመገንባት ሂደት ሁሉም ሊሳተፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

እንደ አቶ ክርስቲያን ገለጻ፤ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የብሔርና የታሪክ አረዳድ ልዩነት ቢኖረንም በአገራችን ከመጡብን አንድ ሆነን መነሳት እንደምንችል ለጠላትም ለወዳጅም ያሳየንበት ነው። በኢትዮጵያዊ መረዳዳትና ችግርን በጋራ የመሻገር እሴት መሰረትም አሁንም ይበልጥ መረዳዳት ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን ያልተገባ የውጭ ተጽዕኖ ለመቀነስ ሁነኛው አማራጭ ቡድኑን እስከ መጨረሻው ማስወገድ ነው ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ የአገራችንን ህልውና ለማረጋገጥና ሕዝባችንን ከውርደት ለመታደግ መላው ኢትዮጵየውያን የጀመሩትን ሁሉን አቀፍ ትግል አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

Filed in: Amharic